አድባራተ ጥበብ

የሀገራችን ፊልሞች በ“ሦስተኛው ሲኒማ” ጽንሰ ሃሳብ መመዘኛ ሲታዩ

ሦስተኛው ሲኒማ (Third Cinema) በስያሜ ደረጃ (Toward a Third Cinema) በሚል ማኒፌስቶ በአርጀንቲናውያኑ ፈርናንዶ ሶላኖና ኦክታቪዮ ጌቲኖ መቀንቀን የጀመረና ለታዳጊ ሀገሮች ተገቢ ይሆናል ተብሎ የታመነበት የፊልም ስራ ንቅናቄ ነው። ይኸው የፊልም ጽንሰ ሃሳብ በሚዳስሳቸው ርዕሰ ጉዳዮችም ቢሆን አንደኛውን ዓለም ከሚወክለው የ‹‹ሆሊውድ ፊልም››ም ሆነ ሁለተኛውን ዓለም ከሚወክለው ‹‹አርት ሲኒማ›› በዓይነቱ ለየት ያለ ነው።

የዚህም መነሻ የሦስተኛውን ዓለም የፊልም ተመልካች ታሳቢ ተደርገው የሚሰሩ ፊልሞች የይዘት ልዩነት ሊኖራቸው ይገባል የሚለው እሳቤ ነው። በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ዓለምን ከተቆጣጠሩትና ገበያንና አዝናኝነትን ቀዳሚ ዓላማቸው ካደረጉ የሆሊውድ ፊልሞች (Commercial and entertainment films) በይዘት ልዩነት ሊኖራቸው ይገባል የሚል ነው።

የሆሊውድ ፊልሞች ለታዳጊ ሀገራት ተመልካች እምብዛም ማኅበራዊ ፋይዳ የሌላቸው ናቸው። ሰዎችን በቴክኖሎጂ ምጥቀት፣ በሚያስገርሙ ድርጊቶችና ተአማኒነት በሌላቸው ሰብዓዊ ያልሆኑ ታሪኮች በማጀብ ተመልካችን ለመሳብና የአንድን  ሀገር የበላይነት ለማረጋገጥ አልፎ ተርፎም የባህል ወረራን ለማስፋፋት ያለሙ ናቸው። በስነ ውበታዊ ልህቀታቸውም ቢሆን ከአርት ሲኒማ ጋር ሲነፃፀሩ እምብዛም ናቸው። ለዚህም ማሳያ ባሳለፍነው ዓመት (2016 እ.አ.አ) የኦስካርን የሽልማት ዘርፎች በብዛት በመውሰድ ሌሎች ፊልሞች ያልተስተካከሏቸውን “The Revenant” እና “Mad Max: Fury Road”ን ማየት ይቻላል። እነኚህ ፊልሞች በተለያዩ ዘርፈ ብዙ ማኅበራዊ ችግሮች ውስጥ ለሚኖር የታዳጊ ሀገር ተመልካች ከማዝናናትና ከማስደመም ያለፈ ምንም ማኅበራዊ ፋይዳ የላቸውም። ይህም ፊልም በሦስተኛው ዓለም ሊኖረው የሚገባውን ሚና በጥያቄ ውስጥ ያስገባል።

በሌላ ጽንፍ አርት ሲኒማ (Art cinema) በዋናነት በአውሮፓ ፊልም ሰሪዎች የሚዘወተር፣ የህዝቡን የእውቀት ልዕልና በሚገልጽ መልኩ በግለሰቦች ጥልቅ ማኅበራዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳዮች ላይ የሚመሠረት፣ የሆሊውድን ንግድን መሠረት ያደረገና አንድ አይነት መዋቅር የሚከተል የፊልም ዘዬ የሚቃወም፣ ኢ-ዘልማዳዊ የሆኑ የአተራረክ ስልቶችን የሚከተል፣ ለፊልም ሰሪው የፈጠራ ነጻነት የሚሰጥ፣ የስነ ውበት ደረጃውም ከፍ ያለና በአብዛኛው የፊልም ፌስቲቫሎችን ታሳቢ ተደርጎ የሚሰራ የፊልም አይነት ነው። እኒህን መሰል ፊልሞች በትምህርት ተቋማት በተለይም በምሁራን ዓለም አቀፍ ተወዳጅነት አላቸው። በዚህ ዘርፍ በ1916 (እ.አ.አ) በአሜሪካዊው ግሪፍዝ የተሰራው ‹‹Intolerance›› እና ኋላ ላይ የመጣው የካርል ቲዮዶር ድራየር ‹‹The Passion of Joan of Arc›› (1965 እ.አ.አ) በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። የይዘታቸውን ጥንካሬ ለመጠበቅና የግለሰቦችን የተናጠል የስነ ውበት ዋጋ (Aesthetic value) ከፍ ለማድረግ ሲባል፣ የአተራረክ  ስልታቸው ከዘልማዳዊው ልብ አንጠልጣይ የታሪክ ፍሰት ወጣ ያለ ነው። ላቅ ያሉ የስነ ውበት ተምሳሌቶችን የሚጠቀሙ መሆናቸውም በእውቀት ባልዳበሩ የታዳጊ ሀገራት የፊልም ተመልካቾች በተለይም በሆሊውድ ፊልም በተቀረፀው ወጣት ዘንድ ተወዳጅነት የላቸውም። በአውሮፓ የፊልም ተመልካች ዘንድም ቢሆን እነኚህና ሌሎች የሀገራቸው ፊልሞች ከሆሊውድ ፊልም ያነስ ተቀባይነት ነው ያላቸው። ለዚህም ማሳያ የሀገር ውስጥ የፊልም ሽፋን በእንግሊዝ (30 በመቶ) በፈረንሳይ ደግሞ (20 በመቶ) መሆኑን መጥቀስ ይቻላል።

ወደ ዋናው ርዕሰ ጉዳይ ስንመለስ፣ የሦስተኛው ዓለም ሲኒማ አቅጣጫ ፈር በያዘ መልኩ ከመጀመሩ በፊትም በዚህ ዘርፍ ሊመደቡ የሚችሉ ፊልሞች ተሰርተዋል። ይህ የሦስተኛ ዓለም ሲኒማ አብዮት ከአንደኛው- ማለትም ከሆሊውድ ፊልም እና ከሁለተኛው- ማለትም ከአርት ሲኒማ ለየት ባለ መልኩ የራሱ የስነ ውበትና የርዕሰ ጉዳይ ደረጃ መገለጫዎች አለው። እነኚህ መገለጫዎችም በሦስተኛው ዓለም ሀገሮች ማለትም በአፍሪካ፣ በእስያ እና በላቲን አሜሪካ የሚገኙ ፊልም ሰሪዎች የሥራዎቻቸውን ጭብጥ፣ የሚኖሩበትን ማኅበረሰብ በማይወክሉ፣ በምዕራባዊ ባህል በተጥለቀለቁ፣ አዝናኝነትንና ንግድን ብቻ መሠረት ያደረጉ ፊልሞችን በመስራት ከሚጠመዱ ይልቅ የማኅበረሰቡን ችግሮች ነቅሰው የሚያወጡ ፊልሞችን መስራት ይገባቸዋል የሚል ነው።

የሦስተኛው ዓለም ሲኒማ ጽንሰ ሃሳብ አቀንቃኞች፣ ኢትዮጵያዊውን ፕሮፌሰር ተሾመ ኃይለ ገብርኤልን ጨምሮ፣ የታዳጊ ሀገሮች የፊልም ርዕሰ ጉዳዮች ሊሆኑ ይገባሉ ከሚሏቸው መካከል የሚከተሉት ይገኙባቸዋል። ሥልጣንን ያለ አግባብ ከሚይዙና ከሚጠቀሙ አካላት ጋር የሚደረግ ትግልን የሚዳስሱ፣ ቅኝ ግዛትን የሚቀናቀኑ፣ የፍትህ እጦትን የሚያሳዩ፣ የመደብ፣ የሃይማኖት፣ የእምነትና የጾታ ጭቆናዎችን የሚፋለሙ፣ ማኅበረሰቡ ፍትህን በመሻትም ሆነ ማንነቱን ለማስጠበቅ የሚያደርገውን ትግል የሚደግፉ፣ ምዕራባዊ የባህል ወረራን የሚቀናቀኑ፣ የድህነትን መንስዔና መፍትሄዎቹን እንዲሁም የዝቅተኛውን ኅብረተሰብ ችግሮች የሚያንፀባርቁ፣ ስደትንና ያለፈውን ታሪክ ከዛሬው ሕይወት ጋር አጣጥመው በማንሳት በማኅረሰቡ መካከል ውይይት የሚፈጥሩና ነገን የሚተነብዩ፣ ለችግሮቻችን መንስዔ የሆኑ ባለስልጣናትን፣ ሥርዓቱን፣ ግለሰቦችንና መንግሥታዊ አካላትን እንደየጥፋታቸው ተጠያቂ የሚያደርጉ፣ አልፎ ተርፎም የአስተማሪነት ሚና ያላቸውና ለውይይት መንስዔ የሚሆኑ፣ መልስ ከመስጠት ይልቅ ጥያቄዎችን የሚያነሱ፣ ማኅበረሰቡን ለማንቃት የሚያስችሉ የለውጥ ሃሳቦችን የሚያንሸራሽሩ ወዘተ. ናቸው።

ከርዕሰ ጉዳይ ዳሰሳ መለያቸው በተጨማሪ የሦስተኛው ዓለም ፊልም አቀንቃኞች የሥራዎቻቸውን ተዓማኒነት ለማጉላትም ሆነ ወጪዎችን ለመቀነስ ፊልሞች ዝነኛ ባልሆኑ ተዋንያን ሊሰሩ እንደሚገባ ይመክራሉ። ይህም በተመልካች ዘንድ ፊልምነታቸው ተዘንግቶ ለእውነት የቀረቡ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።

በአሰራር ሂደትም ቢሆን፣ ይህ የሲኒማ ዘርፍ የራሱ መገለጫዎች አሉት። ለማኅበረሰቡ ቅርብ የሆኑ ችግሮችን ማንሳቱ እስካልቀረ ድረስ እንደየ ፊልሞቹ ይዘትና ዓይነት እውነተኛ የሆኑና የተቀረጹ ምስሎችን፣ ድምጾችን፣ ዶኩመንተሪ ግብዓቶችን ከሌሎች ፊልሞች በጎላ መልኩ ሊጠቀም ይችላል። ለምሳሌ አንድ ፍትህን ባጣ ገፀባህሪ ላይ የተሰራ ፊልም ከዚያ  በፊት የነበሩ የፍትህ ጉድለቶችን የሚያሣዩ እውነተኛ ምስሎችን ሊጠቀም ይችላል። በዚህም ምክንያት የሦስተኛው ዓለም ሲኒማ ከምስል ጥራት ይልቅ በይዘት ጥራት፣ ከአዝናኝነትና ከቴክኒካዊ አስደማሚነት ይልቅ መልዕክቱን ለተመልካች በማስተላለፍ ላይ ያተኩራል። በመሆኑም፣ የሦስተኛው ዓለም ሲኒማ ጥራቱን እንደ ሆሊውድ በቴክኖሎጂ ለማቅረብ ከመሞከር ይልቅ የይዘት ልህቀትን ማረጋገጥ ላይ ማተኮርን ይመርጣል።

ለማሳያነት ያህልም የአርጀንቲናዊው ፈርናንዶ ሶላኖን ፊልም ‹‹The Hour of the Furnaces›› (1968)፣ የጀሚል ዴህላቪን ‹‹Towers of Silence›› (1975)፣ የእውቁን አፍሪካዊ ኦስማን ሲምቤንን ‹‹Mandabi›› (1969)፣ ‹‹Borom Sarret›› (‹‹The Wagoner››፣ 1963)፣ እና ‹‹Xala›› (1975) የጊሎ ፖንቴ ኮርቮን ‹‹The Battle of Algiers›› (1967)፤ እና የኢራናዊው መጂድ ማጂዲን ‹‹The Song of Sparrows›› (2008)፤ በሀገራት ደረጃ ደግሞ በተሻለ ሁናቴ የሚገኙትን የኢራን፣ የአልጄሪያ፣ የፓኪስታን፣ የብራዚል፣ የቺሊና የቦሊቪያ ፊልሞች መጥቀስ ይቻላል።

ይህን መለኪያ ይዘን ወደ ሀገራችን ስንመጣ የትላንት ታሪካችንን ጠባሳ ጥልቅ በሆነ መልኩ የሚያሳየንን የኃይሌ ገሪማን “ጤዛ” እናገኛለን። ሆኖም ግን በእኔ እምነት “ጤዛ”ም ቢሆን፣ በዚህ መስፈርት ሲለካ የአተራረክ ቅለት (narrative simplicity) ይጎድለዋል። ይህም ማለት የሦስተኛው ዓለም ሲኒማ ዓላማው ከማዝናናቱ ጎን ለጎን ማስተማር እስከሆነ ድረስ ተመልካቹም ከሌላው ዓለም ጋር ሲነጻጸር ነገሮችን የመረዳት ችሎታው ዝቅ ያለ በመሆኑ ፊልሞች ውስብስብ ችግሮችን በቀላል የአተራረክ ስልት ማቅረብ አለባቸው የሚል ነው። ይህ ግን “ጤዛ”ን ለመንቀፍ አይደለም። “ጤዛ” “ጤዛ” ነው። አሁንም ድረስ በሀገራችን ታሪክ እንደ ጤዛ አንዴ ብቻ ጠዋት ላይ የሚመጣ፣ የመጣም ነው።

ነገር ግን አብዛኞቹ የሀገራችን ፊልሞች የሦስተኛውን ሲኒማ አቅጣጫ የሣቱ ናቸው። ብዙ ጊዜ የሀገራችን ፊልም ሰሪዎች ለሀገራችን ፊልም እድገት መቀጨጭ ምክንያት የሚያደርጉት የፊልም ቴክኖሎጂ አለመኖርንና የምጣኔ ሀብትን ጉዳይ ነው። ሆኖም ግን ለአፍሪካም ሆነ ለሌሎች ታዳጊ ሀገራት የፊልም እድገት ረሃብና ችግር ጥልቅ የሆነ ሂሳዊ ምልከታ ያላቸው፣ በእውቀት የዳበሩ ሃሳቦችን ፊልም የሚያደርጉ ባለሙያዎች አለመበራከታቸው ነው።

ጥሩ ሀገርኛ ሃሳቦች በጥልቀት እስከቀረቡ ድረስ ተመልካቹ ለፊልም ቴክኒካዊ ጥራት የሚሰጠው ትኩረት እምብዛም ሊሆን ይችላል። ምናልባት ለዛም ይሆናል በተጠቀሙበት ቴክኖሎጂና በሲኒማቶግራፊ ደረጃቸው ወይም ባፈሰሱት የገንዘብ መጠን ሣይሆን ባነሱት ርዕሰ ጉዳይ ጥልቀትና አስፈላጊነት እነ ‹‹Casablanca›› (1942)፣ እና ‹‹Birth of a Nation›› (1915) ዓይነት ፊልሞች ዘመን ተሻጋሪ የሆኑት።

እዚህ ላይ መነሳት ካለባቸው ነገሮች አንደኛው የሦስተኛው ዓለም ሲኒማ የሚኖርበትን ማኅበረሰብ ሁኔታ የሚያንጸባርቅ መሆን አለበት የሚለው አስተሳሰብ እኛን በእጅጉ ይመለከተናል። በእውነቱ ፊልሞቻችን ምን ያህሉን የማኅበረሰብ አባላት የሚወክሉ ናቸው? የሚያነሷቸው ርዕሰ ጉዳዮችስ ጥልቀት ምን ያህል ነው? ምንም እንኳን እነዚህን ጥያቄዎች በአግባቡ ለመመለስ ሳይንሳዊ ጥናት የሚያስፈልግ ቢሆንም፣ ባለን ቅኝት ከጥቂት ፊልሞች በስተቀር አብዛኞቹ የሦስተኛውን ዓለም ሲኒማ ጽንሰ ሃሳብ የማያሟሉ፣ የሚያነሷቸው ጉዳዮች በተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች የተጠላለፈውንና በአብዛኛው በሳር ጎጆ ውስጥ የሚኖረውን የኢትዮጵያ ህዝብ አኗኗር የማያሳዩ ናቸው።

ለምዕራቡ ዓለም የባህል ወረራ ሰለባ በሆኑ ጥቂት የማኅበረሰቡ አባላት ዙሪያ የሚያጠነጥኑ፣ በየሰፈሩ በሚሰባሰቡ የራሳቸውን፣ የሀገሪቱንና የማኅበረሰቡን ታሪክና ባህል ጠንቅቀው በማያውቁ፣ በትምህርትም ይሁን በልምድ አስፈላጊውን እውቀት ባልሸመቱ፣ በፍላጎት ብቻ በሚሰሩ ወጣቶች ተነሳሽነት በፒያሳና በቦሌ ካፌዎች ውስጥ የሚያልቁ ፊልሞች ናቸው።

በእርግጥ አሁን አሁን ከዚህ ትችት ለማምለጥ በሚመስል መልኩ ሀገሬን ሀገሬን የሚሉ ገፀባህሪያትንና የገጠሩን ሰው የሞራል ሰብዕና የዋህ አስመስሎ የማቅረብ ሙከራዎች ይንጸባረቃሉ። ግን እነሱም ቢሆኑ በስሜትና በፕሮፖጋንዳ ላይ ላዩን ካልሆነ በስተቀር የማኅበረሰቡን ሥነልቦና እና ማኅበራዊ ማንነት በጥልቀት የሚገልጹ አይደሉም። በዚህም ምክንያት ጎጆ ውስጥ የሚኖርና ጎጃም አዘነን የለበሰ ገፀባህሪ በፊልም ውስጥ ማካተት ብቻውን አፍን ሞልቶ ሀገራዊ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥን ፊልም ሰራሁ ሊያስብል አይችልም።

ስለዚህም፣ የፊልሞቻችን መጠነ ርዕይ በአንድ መንደር እስከተወሰነና ባለ- ሀገሩን እስካልወከለ ድረስ፣ ለሁሉም ፊልሞች ኢትዮጵያዊ የሚል ዜግነት መስጠቱ ራሱ አግባብ አይሆንም። ሆኖም የተሻሉ ፊልሞችን ለመስራት የሚጥሩ ግለሰቦች እንዳሉ መካድ አይቻልም። ያ ግን ሀገራዊ የፊልም ስራ ባህላችን ሆኖ ሊጠቀስ አይችልም።

በእርግጥ በአፍሪካ የሦስተኛውን ዓለም ጽንሰ ሃሳብ የሚከተሉ በተለይም የማኅበረሰቡን ችግሮች በቀጥታ የሚዳስሱ ፊልሞች ሲሰሩ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ሥርዓቱን ተጠያቂ ማድረጋቸው አይቀርም። በርካታ የአኅጉሪቷ መሪዎች ደግሞ ይህን በይሁንታ የመቀበልና ራስን የመገምገም ዲሞክራሲያዊ ልዕልና ላይ አለመድረሳቸው ለፊልም ስራው ተጠቃሽ ተግዳሮት ነው። በሀገራችንም እየሆነ ያለው ይኸው ነው። የኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት በአንቀጽ 29 ሳንሱርን ሙሉ በሙሉ ያስወገደ ቢሆንም፣ ፊልሞቻችን እንኳን ሥርዓቱን በቀጥታ የመተቸት ዕድል ሊሰጣቸው ተሸናፊ የሆነ የፖሊስ ገፀባህሪን መሳል ራሱ ውጉዝ ነው ይባላል።

ያም ሆኖ ግን አንዳንድ ፊልም ሰሪዎች እንደሞከሩት ቀጥተኛ ባልሆነና ፖለቲካውን ወደ ጎን በተወ መንገድ ገፀ ባህሪያትን በስነ ምግባር ማዕቀፍ ውስጥ እያስገቡ ሥርዓቱን  መተቸትና ጨቋኝ አካልን መታገል ይቻላል። አንዳንዴም እንደ ፕሬሱ ሁሉ ሲኒማውም ራሱን መስዋዕት ለማድረግ የተዘጋጀ የምስል ጥበብ አብዮተኛ ያሻዋል። ከዚህም ባሻገር ከመንግሥት ጋር ምንም ቁርኝት የሌላቸው፣ በዘልማድ አብረውን የኖሩና ፊልም መሆን የሚችሉ ብዙ ማኅበራዊ ችግሮች፣ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶች፣ የእሳት ዳር ተረቶች፣ ስነ ቃሎች፣ አፈ ታሪኮችና ቅኔዎች አሉን። ግን እስካሁን በፊልሞቻችን አልተወለዱም።

ይህም ማለት ፊልምን ለማኅበራዊ ለውጥ ከመጠቀም ይልቅ እንደ ቅንጦትና መዝናኛ ዘርፍ ብቻ መመልከት ያመጣው አባዜ ነው። በአሁኑ ወቅት በሀገራችን በዓመት ውስጥ ቢያንስ አንድ መቶ ፊልሞች ይሰራሉ። ሆኖም አብዛኞቹ ከማሳቅ ያለፈ ምንም የቤት ስራ የማይሰጡና ተመልካቹ እንዲያስብ የማያደርጉ ቧልቶች ናቸው። እውን ግን ይህቺ ሀገር በአያሌ ማኅበራዊ ችግሮች ተጠላልፋ ቧልት ብቻ ያማራት እመቤት ናት? የሚለው የሁላችንም ጥያቄ ነው። አዎ እንድንስቅ ብቻ ሣይሆን እንድናስብ የሚያደርጉ፣ መልስ የሚሰጡ ብቻ ሳይሆኑ ብዙ ጥያቄዎችን የሚያነሱ፣ ራሳችንን እንድንገመግም የሚያደርጉ፣ ከሲኒማ ቤት ስንወጣ የሚያወያዩና መፍትሄ የሚያፈላልጉ ፊልሞች ያስፈልጉናል። ተመልካቹም መራብ ያለበት የፊልም ቡፌ ይሄ ነው።

በኔ እምነት ማኅበራዊ ለውጥን የሚያቀነቅኑ ፊልሞችን ለመስራት ጥልቅ እይታ ያላቸውን ፊልም ሰሪዎችና በተመሳሳይ ደረጃ የሚገኙ ተመልካቾችንም መፍጠር ያስፈልጋል። በሀገራችን ስለ ጥበቡ ያለው ግንዛቤ በፊልም ሰሪውም ሆነ በተመልካቹ ዘንድ የተዛባ ነው። በእርግጥ አኅጉራችን በእውቀት ገና ያልዳበረችና የአስተሳሰብ ልህቀትን ያላረጋገጠች መሆኗ እውነት ነው። በፊልሙም ዘርፍ ያለው ችግር ተመሳሳይ ነው። ፊልም ሰሪው ምን አይነት ችግሮች አሉብን? የኛ ታሪክ ምንድን ነው? ምን ብንሰራ ነው ማኅበራዊ ፋይዳ የሚኖረው? ብሎ ራሱን ሲጠይቅ እምብዛም አይታይም። ፊልም ሰሪዎቻችንን ምርጥ ሀገራዊ ሃሳቦችን ከማፍለቅ ይልቅ ምርጥ የፊልም እቃዎችን ከዱባይ ማስመጣት ነው የሚያስጨንቃቸው። 

መፍትሄው ይህን ሊያሳካ የሚችል የፊልም ትምህርት ሥርዓት መዘርጋት እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ። ሆኖም ትምህርቱ በሚሰጥባቸው አንዳንድ ታዳጊ ሀገራትም ቢሆን ትኩረቱ ጥልቅ የሆኑ ሀገርኛ ሃሳቦችን በፊልም ማቅረብ በሚችሉበት መንገድ ላይ ሳይሆን በቴክኒካዊ የአሰራር ሂደቱ ላይ ነው።

በእርግጥ በዘልማዳዊው የትምህርት አሰጣጥም ይሁን በሌላ መልኩ ጥልቅ ዕይታ ያላቸው ፊልም ሰሪዎችን ማፍራት አንገብጋቢ ነው። በመሆኑም ትምህርት ቤት ገብተውም ይሁን ራሳቸውን አስተምረው ፊልም የሚሰሩ ባለሙያዎች ጥበቡ በሀገራችን ሊኖረው የሚገባውን ሚና ለመለየት ለቴክኒካዊ እውቀት ከሚሰጡት ትኩረት ጎን ለጎን፣ በጥናትና በእውቀት፣ በሀገር ባህልና በማንነት የዳበሩ ይዘቶችን በፊልም ለመስራት መትጋት ያስፈልጋል።

ይህም ፍላጎትና ቆራጥነቱ ካለ የምንኖርበትን ማኅበረሰብ በጥልቀት በማየት፣ በማጥናትና በማንበብ፣ እንዲሁም የተለያዩ የመረጃ ምንጮችን በመጠቀም ሁለገብ እውቀትን ማዳበር ወይም ሚናን መለየት ያስፈልጋል ያ ሲሆን የምጣኔ ሃብታችን መሰናክሎች እንዳሉ ሆነው ከማኅበራዊ ችግሮቻችን በተጨማሪ ያልተነኩት ታሪኮቻችን አስተማሪ በሆነ መልኩ መቅረብ ይጀምራሉ። ባህሎቻችንም ለይስሙላ ሳይሆን ጥልቅ በሆነ መልኩ ፊልም መሆን ይጀምራሉ።

ፊልም ሰሪው ተመልካቹን ከገባበት የፊልም ግንዛቤ ለማውጣት ተመልካቹ የሚፈልገውን ሳይሆን የሚያስፈልገውን ፊልም መስራት መቻል አለበት። ፊልም ማለት ኮሚዲ ነው ብሎ ተመልካቹን ያስተማረው ፊልም ሰሪው ራሱ ስለሆነ ለኛ ፊልም ማለት እኛን የሚያሳየን፣ ችግሮቻችንን የሚቀርፍ፣ ታሪካችንን የሚዳስስ፣ ማንነታችንን የሚያንጸባርቅ ነው ብሎ ግንዛቤውን ማቅናት ያለበትም ፊልም ሰሪው ራሱ ነው።

መንግስትም በፊናው በንጉሱ ዘመን ሥነ ምግባርን የሚጥሱ የምሽት ጭፈራ ቤቶች እንዳይበራከቱ በሚል ሰበብ በሙዚቃ ላይ በመጣል የጀመረውን የሥነ ጥበብ ስራዎች የታክስ መጠን በመገምገም፣ በአሁኑ ወቅት በፊልሞችና በፊልም መስሪያ ቁሳቁሶች ላይ የተጫነውን ከፍተኛ የታክስ መጠን ሊቀንስ ይገባል። እንደ ፊልም ኮርፖሬሽን ያሉ ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው ፊልሞችን መስራት የሚችሉ ተቋማትን ከመዝጋት ይልቅ ማስፋፋት፣ የፊልም ሥርዓተ ትምህርት እንዲዳብር ማድረግ፣ ከሁሉም በላይ የፊልም ሰሪውን ሕገ- መንግስታዊና የፈጠራ ነፃነት ማክበር አለበት።

ይህ ሲሆን በሦስተኛው ዓለም የሲኒማ አብዮት ማዕቀፍ ውስጥ ሊመደቡ የሚችሉ ፊልሞች መሰራት ይጀምራሉ። እኛን እኛን የሚሸቱ፣ ስለ እኛ የሚናገሩ፣ ታሪካችንን፣ ባህላችንን፣ የሞራል እሴቶቻችንን፣ ማኅበራዊ ማንነታችንና፣ ስነ ልቦናዊ መገለጫዎቻችንን የሚዳስሱ ፊልሞች ሲሰሩ ረዣዥም ሰልፎችን በየሲኒማ ቤቶቻችን ደጃፍ ላይ መመልከት እንችላለን።

በ‹‹ሂሩት፣ አባቷ ማነው››፣ በ‹‹ጉማ›› እና በ‹‹አስቴር›› ተጀምሮ ከዓመታት በኋላ በ‹‹የበረዶ ዘመን››፣ በ‹‹ጉዲፈቻ›› እና በ‹‹ቀዝቃዛ ወላፈን›› ያንሰራራው የሀገራችን የፊልም ኢንዱስትሪ ዛሬ ላይ በ‹‹ቃና›› መምጣት የተደናገጠ ይመስላል። ስለሆነም፣ እንደ አሸን የፈላውን የፊልም ኢንዱስትሪ ስኬቶችና ውድቀቶች በመገምገምና የቅርጽና የቴክኒክ ብቻ ሳይሆን የይዘትም ማሻሻያ በማድረግ ወደፊት የሚራመድበትን የተሻለ መንገድ መፍጠር ያስፈልጋል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top