የታዛ ድምፆች

ዘይኑ ‘ፑሸር’

ሙሉ ስሜ ዘይኑ ሙዘይር ነው። ጓደኞቼ ‘ፑሸር’ ይሉኛል። አሜሪካ እንደመጣሁ እንደማንኛውም ሰው ወፈርኩ። የሰውነቴ መፋፋት ግን ካገሩ ብርድና እንግሊዝኛ ሊታደገኝ ስላልቻለ ስራ ሳላገኝ ጥቂት ሰነበትኩ። ቤተሰባዊ የቴሌቪዢን ሾው ከፍቶልኝ ወደስራ የሚሄደው አጎቴ ሲመለስ ነፃ ትግል እያየሁ በላብ ተጠምቄ ይደርሳል። በዚህ ሁኔታ ጥቂት ከታገሰኝ በኋላ ከነፃ ትግል ነፃ የቋንቋ ትምህርት እንድከታተል ወሰነ።

በሄድንበት ትምህርት ቤት ውስጥ እንደኔ በእንግሊዝኛ እዳ የተያዙ በርካታ ወገኖቼና ሌሎች ዜጎችን በማየቴ ተፅናናሁ። ትምህርቱ በደረጃ የተከፈለ ሲሆን ምደባ የሚወሰነው በመግቢያው ፈተና ውጤት መሰረት ነው።

ከአጎቴ ጋር ከምዝገባው ቢሮ ስንደርስ በሰላምታ የተቀበለችን ፈረንጅ ምን እንደምንፈልግ ጠየቀችን። እኔን ለማስመዝገብ እንደመጣ ሲነግራት በከፊልም ቢሆን የተረዳሁት እኔው ራሴ ነበርኩ።

ፈረንጇ ሁለታችንም በየተራ እያየች ተመዝጋቢው ማን እንደሆነ በድጋሚ ጠየቀች። አጎቴ ከኔ እኩል በመቆጠሩ የተሰማውን ንዴትና እሱን ለመሸፈን የፈጠረውን ፈገግታ እያፈራረቀ ‘ሂ’ ሲል እንደሌባ ወደኔ ጠቆመ። ቢሮዋ ውስጥ እንደቆምን ሴትዮዋ ጠረጴዛው ላይ የነበረ ስቴፕለር አንስታ “What is this in English?” ስትል ግን ካጎቴ ጋር ተፋጠጥን። መልሱን ቢያውቀው እንኳን መናገር አይችልም።

ፊቱ ላይ ያየሁት መረበሽ ደግሞ ስቴፕለር በህይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት ቃል እስኪመስለኝ አስደነገጠኝ። ወዲያው እጇ ላይ ወዳለውና ለጊዜው ምንነቱን ልገልፀው ወዳልቻልኩት ግዑዝ ነገር አተኩሬ እያየሁ ድንገተኛ ቃል ካፌ ሲወጣ ተሰማኝ :- “ፑሽ …ፑሽሽሽ… ፑ..ፑሸር..”። መልሴ ልክ እንዳልነበር እኔው ራሴ ምናልባት አጎቴም ጭምር እርግጠኞች ነበርን።

በዚህ ሁኔታ የጀማሪ ደረጃ ውስጥ ተመድቤ መማር ግድ አለኝ። ከምዝገባ ስንወጣ አጎቴ ቀላል ጥያቄ በመሳቴ አልወቀሰኝም። አንድም ቃል ሳንነጋገር ቤት ደረስን። እሱም በልቡ ስቴፕለር በእንግሊዝኛ ምን እንደሆነ ሲያሰላስል የነበረ ይመስለኛል። ከልጅነት እስከዕውቀት የማውቀው ስቴፕለር ራሱ እንግሊዝኛ መሆኑን ልብ ያልኩት ብዙ ሳልቆይ ቢሆንም ታሪኩን በየዋህነት ያጫወትኳቸው ጓደኞቼ ግን ዛሬም ድረስ ‘ፑሸር’ እያሉ ይጠሩኛል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top