የታዛ ድምፆች

ዕውቀትና ልምድ ለተተኪው ትውልድ

በ ለጠቀው እሑድ በቀጠሮው ወጣቱ ደራሲ የማስታወሻ ደብተሩን ጨብጦ ወደ አንጋፋው ቤት ሲያመራ በግንባሩ ላይ የተሳለው ፈገግታ ካለፈው እሑድ ይበልጡን የጐላ ነበር። የፈገግታው መንስዔ በወጣቱና በቅርብ ጓደኛው በአቶ መንታዬ መኻል ሌሊት የሚደረገው ውይይትና ጭውውት ነው።

አንጋፋው ዘንድ በመመላለስ ወጣቱ የሚቀስመውን ዕውቀት አቶ መንታዬም መደገፉን አበክሮ አስገንዝቦታል። ጨመር አድርጎም እንደ ልማዱ አንድ የታወቀ የጥንት ብሂል በመጥቀስ፤ መጠየቅ/ ያደርጋል ሊቅ፤ ተከብሮ/ያደርጋል ደንቆሮ፤ ብሎ ነበርና ወጣቱም ከተከብሮ አደጋ ዘንድሮ ያላቀቀውን ‹‹የአርባ ቀን እድሉን›› ማመስገኑ አልቀረም።

በነገራችን ላይ ይህ ጥንታዊ ብሂል በአራት ሐረጎች ስንኝ የተቀናበረ ሆኖ አንደኛው የሰንጎ መገን ንዑስ ሐረግ፣ ሁለተኛውና ሶስተኛው የቡሄ በሉ፣ አራተኛው ደግሞ የወል ሐረግ መሆኑን ወጣቱ እስከ መለየት ደርሶ ነበር በግል ኪነ ጥበብ ዕውቀቱ።

ወጣቱ ከአንጋፋው ቤት ደርሶ የውጪውን ቆርቆሮ በር እንዳንኳኳ ወይዘሪት ገረድ መዝጊያውን ገርበብ አድርጋ፤ ‹‹ዛሬ ጋሼን ጥቂት እንደ ማመም ብሏቸው ካልጋ አልወረዱም›› አለችው።

‹‹ምነው? ምን ነካቸው?››

‹‹አይ ምንም አይደል እመሙ እንኳን ደንበኛቸው ነው፤ በክረምት በክረምት ከዝናቡና ከቅዝቃዜው ጋር ነው የሚመጣው፤ ሪህ አለባቸው።››

‹‹ከታመሙ ምን ይደረጋል? ሲሻላቸው እመጣለሁ›› ብሎ ሊመለስ ሲቃጣ፣ ገረዲቱ የአሳዳሪዋን ትእዛዝ ነገረችው።

‹‹ያ ወጣት በቀጠሮው የመጣ እንደሆን በቀጥታ እመኝታ ቤቴ ይግባ፤ አትከልክይው ብለዋል። እንዲያውም ወንበርና ትንሿን ጠረጴዛ አግቢለት ብለውኝ ከሳሎን ወደ መኝታ ቤት ወስጃለሁ›› ብላ እየመራች አስገባችው።

***

አንጋፋው ከበስተጀርባው ትራሶች ከምሮ ተደግፎ፣ በጋቢው ተጀቡኖ፣ ቀና ብሎ ተጋድሞ ነበር። ወጣቱ እንደገባና ከወንበር ዐረፍ እንዳለ ከዝጌር ሰላምታ በኋላ በሌላ ወሬ ጊዜ ሳያባክኑ ባለፈው ቀን ወደ ጀመሩት የቁም ነገር ጨዋታ አመሩ። ባለፈው እሑድ ውይይታቸውን ያቆሙት ወጣቱ የደራሲ ትውልድ ስለ ግእዝ ቅኔ ቴክኒክ በመጠኑም ቢሆን ጥቂት ማወቅ አለበት በሚለው ምዕራፍ ላይ ስለነበር ከዚያው ጀመሩ።

‹‹በጀ›› አለ አንጋፋው ‹‹ከግእዝ ቅኔ ቅርሳችን ምን ትምህርት እናገኛለን? ስለ ግጥም ድርሰት መሰረታዊ ባሕርይ?››

ቅኔ የሥነ ድርሰት አረቄ፣ የነጠረ፣ የተቀመመ፣ የተመጠነ በዚያም ላይ የረቀቀ፣ የጠለቀ፣ የመጠቀ ነገር መሆኑን ጠቀሰ። አያይዞም በጣም ከታወቁት ጥንታዊ የግእዝ ቅኔያት ለወጣቱ እጅግ የማይጸንኑትን እየመረጠ በቃል ከያዛቸው ጥቂቶቹን አነበበለት። እርሱ ሲያነብ ወጣቱ በደብተር ይጽፋቸው ጀመር።

የግእዝ ቋንቋ አነባበቡ ራሱ የተለየ ጠባይ እንዳለው ይኸውም በሚነሳው፣ በሚወድቀውና በሚናበበው ቀለም የሚታወቅ መሆኑን አንጋፋው በምሳሌ አስረዳ። ከዚሁ ጋር በግእዝ ቅኔ ሚዛን በየዘውጉና በየቤቱ በየሐረጉ የሚቆጠረው ተነሺው ወይም ወዳቂው ቀለም መሆኑን ወጣቱ ከደብተሩ ባሠፈራቸው ቅኔያት ምሳሌነት አንጋፋው አስረዳ።

የግእዝ ቅኔ በቴክኒኩ፣ ማለትም በምሥጢር አገላለፁ በጣም ከፍ ካለ መራቀቅ ደረጃ የደረሰ የሥነ ግጥም ዘርፍ መሆኑን ለወጣቱ በተጨባጭ አሳየው። ለአርአያና ምሳሌነታቸው አንብቦ ተርጉሞ አመሳጥሮ፣ ተርኮና አትቶ፣ ከተነተናቸው ቅኔያት መካከል የክፍለ ዮሐንስ፣ የዐቃቤ ሰዓት ካብቴ፣ የራስ ወልደ ገብርኤል ይገኛሉ። በተለይ፡-

‹‹እረኝነት ይሻል ከመሆን ካህን…›› ብሎ አንጋፋው የተረጐመውን የክፍለ ዮሐንስን መወድስ ቅኔ በደንብ አብራርቶ በፈታለት ጊዜ የወጣቱ ልብ እንደ እምቦሳ ፈነደቀ። እንዲሁም፣

‹‹ዓለም እጊዜዋ ድረስ በዝንጋታ ገመድ ትጐትተናለች›› ብሎ የተረጐመውን የራስ ወልደ ገብርኤልን ቅኔ በሰማ ጊዜ ወጣቱ ምንም እንኳን በዚህ መወድስ መልእክት ባይስማማ፣ ባቀራረቡ ኪነ-ጥበብ ከመደሰቱ የተነሳ የግእዝ ቅኔ ፍቅር እንደ ብራቅ ብልጭ ብሎ ከልቡ ዘው አለና ገባ።

ከዚህ በኋላማ ምኑ ይጠየቃል? አንጋፋና ወጣት ሰምና ወርቅ ሆኑ። አስተማሪው አንድ ተማሪው አንድ ብቻ የሆነበት ሰው ያላወቀው የቅኔ ትምህርት ቤት ተሟሟቀ፣ ደራ። ወጣቱን የያዘው ዐይነ ጥላ ተገፈፈ። ባለማወቅ በዝና ይጠላው የነበረውን የደብተራ ጥበብ አፈቀረው። ከመውደዱ የተነሳ እንደ ክፍለ ዮሐንስ ያለ ቅኔ በግእዝ ሳይሆን በአማርኛ ቋንቋ፣ በሃይማኖታዊ ሳይሆን በዓለማዊ ተራማጅ ርእስ አዲስ ለመግጠም ጓጓ፤ ይህንኑ ለአንጋፋው ገለጠለት።

‹‹ምን ይመስልዎታል የኔታ? የኔታ እንድልዎት ይፈቀድልኝ እንግዲህ እና ምን ይመስልዎታል? የአማርኛውን ቅኔ በግእዙ ቅኔ መልክና ሥርዓት፣ በግእዝ ቅኔ ኪነ-ጥበብ ብንደርሰው? ግሩም አይመስልዎትም?››

አንጋፋው ለመልሱ መንደርደሪያ ከአንድ ከታወቀ ቅኔ ጠቀሰ፡-

‹‹እሳት አራዳ ኮኛክ እሷው ተቃጥላ፣ አጋየቻት ባቢሎንን ገላ›› ተብሎልሃል። ስለ መጠጥ ጐጂነት ባለ ቅኔው ደራሴ ተውኔት ዮፍታሔ ንጉሤ ናቸው።››

ይህ አጋጣሚ በጣም ነው ያስገረመው ወጣቱን።

‹‹ተሞክሯል ካሁን በፊት!›› አለ በመደነቅ ።

‹‹መሞከር ተሞክሯል። ይህን ዓይነት ሌላ ሌላም የግእዝ አማርኛ ቅኔ የግእዝ ኦሮምኛ ቅኔም አልጠፋም። ቢሞከርም ግን፣ ሙከራው ሙሉ በሙሉ አልተሳካም።›› አለና አንጋፋው እንደምሳሌ የሚቀጥለውን የግእዝ – ኦሮምኛ መወድስ መደምደሚያ ቤቶች ጠቀሰ።

‹‹ማሎ ማሎ ጎፍታ ኪያ

መና ፈርዳ ፉደቴ አህያ››

የቅኔው ምሥጢር፣ ለተማረ የሚገባውን ሹመት ያልተማረ ወሰደው በማለት፣ ባለ ቅኔው አለቃ ዘወልዴ ለዳግማዊ አጼ ምኒልክ ያቀረቡት ሳቅ አዘል አቤቱታ መሆኑን እግረ መንገዱን ጠቆመው።

በአንጋፋው አስተያየት ግን ከላይ የተጠቀሱት አይነት የግእዝ አማርኛና  የግእዝ ኦሮምኛ ቅኔያት ከስንኛቸው ቅንብር አንፃር ግዕዝ ናቸው እንጂ አማርኛ ወይም ኦሮምኛ አይደሉም። ስላይደሉ በዚሁ በቅይጥነታቸው ምክንያት ጉራማይሌ የሚል ቅጽል ተሰጥቷቸዋል። አብዛኞቹ የግእዝ ቃላት ጣልቃ ያስገባሉ እንጂ መሳ ለመሳ በአማርኛ ወይ በኦሮምኛ ወይ በትግርኛ ብቻ የተደረሱ አይደሉም። ዋና ጉድለታቸው ግን ለአማርኛ ወይንም ለሌሎቹ ቋንቋዎቻችን ዜማና ሚዛን እንግዳ የሆነውን የግእዝ አነባበብ ምት (ሪትም) በቋንቋዎቹ ላይ መጫናቸው ነው።

‹‹ስለዚህ፣›› አለ አንጋፋው ወጣቱን ተኩሮ እያስተዋለ፤ ‹‹ አንተ እንዳሳሰብከው የአማርኛን ቅኔ በግእዙ ቅኔ ኪነ ጥበብ ሥርዓት በግእዝ ዘውገ ቅኔያት አምሳያ ግን በአማርኛ ዜማና ሚዛን ለመድረስ ቢሞከር፤ ይህ በተለያዩት ያማርኛ ግጥም ሐረጎች ቅንብርና ስብጥር ቢከናወን ለአማርኛ ግጥም ተጨማሪ እመርታ ነበር የምንለግሰው፤››

‹‹ብቻ ምን ያደርጋል? ማን ያደርገዋል? ቀላል ሥራ አይደለም ሳይሆን፤ ያደክማል አያደክምም? ሳይሆን፤ ጥያቄው ይቻላል ወይ? ነው›› አለ ወጣቱ ወኔው ተናውጦ። ‹‹ለእርስዎ ለራስዎ የሚቻል ይመስልዎታል ወይ?››

አንጋፋው አልመለሰም። ዓይኑን ሳይከድን የቀን ሕልም እንደሚያይ ሁሉ በሐሳብ ሩቅ አገር የሄደ ነበር የሚመስለው።

ወጣቱ መልሱን ለመስማት ቸኩሏል። ‹‹ይቻላል፣ አይቻልም?››

‹‹አዎ፤›› አለ አንጋፋው በርጋታና በዝግታ ‹‹መቻል ይቻላል። የሚቻል ይመስለኛል። ግን ራሴ አልሞከርኩትም። እስክታነሳው ድረስ፤ በዚህ ነገር በምር አላሰብኩበትም››

‹‹ከተቻለማ አንጀምረውም?›› አለ ደቀ መዝሙር። ‹‹እርስዎ በግእዙ ቅኔ መንገድ ይመሩኛል፤ እኔ በግእዙ አምሳያ ግን በአማርኛ ስንኝ ሚዛንና ዜማ እያንዳንዱን ቅኔ ዘውግ እያስመሰልኩ ግጥሙን እገጥማለሁ። መጀመሪያ ለምስጢሩ ጥልቀት ይህን ያህል መጨነቅ ያለብኝ አይመስለኝም፤ ለጊዜው ምን መሰለዎት አሳቤ?››

‹‹ይህን ስትል አሁን ትዝ አለችኝ። አንዲት ሁለት ቤት ያማርኛ ቅኔ። እስካሁን ረስቻት ኖሬ ድንገት ውል አትለኝም! የጥንት ግጥም ናት፣ የደብተራ የፍቅር ግጥም፤

‘እፀ በለስ በልቶ አዳም ከንፈርሽ፣ መድኀኔዓለም ልቤ ተሰቀለልሽ’ ድንቅ አይደለችም? ቋንቋው አማርኛ መንገዱ የግእዝ ቅኔ፣ ዘውገ ግጥሙ የወል። ዋናው ነገር ግን የስንኙ ሚዛንና ዜማ የአማርኛ እንጂ የግዕዝ አለመሆኑ ነው። እንዲህ ነው አንተም መግጠም ያለብህ። ግን የወል ቤት ብቻውን ስለሚሰለች ከቡሄ በሉና ከሰንጎ መገንም ሐረጎች ብትደባልቅበት አይከፋም››

‹‹መቼ እንጀምር?›› አለ ወጣቱ ቸኩሎ።

‹‹ለዛሬ በዚሁ እናብቃ። መታመሜንም አልረሳው! ሳምንት በምር አስጀምርሃለሁ›› አለ አንጋፋው ነቃ ነቃ ፈገግ ፈገግ እያለ። ‹‹አንተን ሳስተምር ራሴም እተማሪ ቤት እገባለሁ››

ወጣቱ ብድግ አለና ደብተሩን አጠፈ። እስክሪፕቶውን ከደረት ኪሱ ሻጠ።

‹‹ብቻ አንድ ነገር አለ የማይረሳ። በእኛ ተማሪ ቤት ተማሪው ሁለት ቢሆንም አስተማሪው አንድ ብቻ ነው!›› አለ በፈገግታ።

አዛውንቱ በድምፅ አልባ ሳቅ ፊቱን ሸበሸበ፣ ‹‹በል ደህና ዋል!››

‹‹ደህና ይዋሉ! ለእግርዎ ይጠንቀቁለት…›› እጅ እንደመንሳት ብሎ ወጣና ሄደ ወጣቱ።

አንጋፋው በፈገግታ ራሱን ላይ ታች ነቀነቀ።

‹‹የልጅነት ነገር፤ የጉርምስና መጀመሪያ ሊያስተምረኝ ነበር የመጣው። ኋላ ሲሰክን ተማሪዬ ሆነ። አሁን ደግሞ በመጨረሻ አስተማሪዬም ሆነ፤ እርሱ ግን አላወቀውም። አለቻ! ወጣትነቷ፤ እኔም በእርሱ ዕድሜ እንደርሱ ሳልሆን እቀራለሁ?››

***

ተማሪና አስተማሪ የአማርኛን ቅኔ በግእዝ ቅኔ አምሳያ የመቁጠሩን ልምምድ ሲጀምሩ፣ ሊከተሉ ያሰቡት በግዕዝ ቅኔ ተማሪ ቤት የሚሰራበትን ዘዴ ነው እንጂ የይዘቱን ሃይማኖታዊነት አይደለም።

በመጀመሪያ ርእሰ ጉዳዩ ተራማጅና ዓለማዊ መሆን ስላለበት ይመረጥና ታሪኩ ወይም ሁኔታው ይብራራል። ከጥንት ግእዝ ቅኔያት መኻል በኪነ ጥበብ ረገድ አግባብ ያላቸው በመምህሩ ይነበባሉ፤ ይተነተናሉ። ቀጥሎ ተማሪው ብቻውን ፀጥ ባለ ቦታ ሆኖ የመጀመሪያ ቅኔውን ለመቁጥር (ለመግጠም) ይሞክራል።

በቅኔ ቤት ተማሪው የሚጀምረው በሁለት ቤት ቅኔ ነው። ያንን ብቻ በተለያየ ርእሰ ነገር ሲቆጥርና ለአስተማሪው ሲነግር አስተማሪም ግምቱን እርማቱንና ምዘናውን ሲለግስ ይሰነብታሉ። ተማሪው ሁለት ቤቷን ቅኔ በደንቡ በሥነ ሥርዓቱ መቁጥር መቻሉን ባየ ጊዜ አስተማሪው ወደሚቀጥለው የሦስት ቤት ቅኔ ክፍል እንዲዛወር ይፈቅድለታል። በዚህ ሲሰለጥን ወደ አምስት ቤት፣ ከዚያ ወደ ስድስት፣ ወደ ሰባት፣ ወደ ስምንት፣ ወደ ዘጠኝ፣ ከዚያም ወደ መጨረሻው ደረጃ ወደ አሥራ አንድ ቤት ቅኔ እንዲዘዋወር ይፈቅድለታል። በዚያ በመጨረሻው ደረጃ ሆኖ ከሁለት እስከ አሥራ አንድ ቤት ቅኔ እየቆጠረ በቂ ጊዜ ካሳለፈ በኋላ አስተማሪው ተማሪው መብሰሉን አይቶ ይመርቀዋል፣ በጉባኤ ያስቃኘዋል፤ ማለትም በቃህ ደረስክ ይለዋል። ተማሪም በደስታ መምህሩን ይሰናበታል። የምስክር ብራና ወይም ዲፕሎማ የሚሉት ነገር የለም፤ ቅኔ ነው ምስክር በቅኔ ቤት።

እርግጥ እንደ አዲስ አበባ ባለች ዘመናዊ መዲና የቢሮ ወይም ሌላ ስራ እየሰራ የሚተዳደር ወጣት ደራሲ የጥንቶቹን የቅኔ ተማሪዎች የመሰለ የትምህርት ፕሮግራም መከተል እንደሚያዳግተው እሙን ነው። ስለዚህ አንጋፋው ለደቀመዝሙሩ ከዘመኑ ጋር የተጣጣመ ፕሮግራም ነው ያዘጋጀለት። በዚሁ መሰረት ወጣቱ በየሁለቱ ቀን አንድ ቅኔ እንዲቆጥር፣ ማለትም በስድስት ቀን ሦስት ቅኔ እንዲቆጥር፣ በሰባተኛው ቀን እሑድ በሳምንቱ የቆጠረውን ይዞ ወደ አስተማሪው ዘንድ እንዲመጣ፣ እንዲያሰማና የመምህሩን ማረሚያ ማስተካከያና ግምገማ እንዲቀበል ነው የተወሰነው። ወጣቱ እንዲጠይቅ፣ እንዲጠያየቅ እንዲከራከርም ተፈቅዶለታል።

በዚህ መንገድ አንጋፋውና ወጣት በቅኔ ሲጓዙ አያሌ ሳምንታት ብዙ ወራት አለፉ። በዚህ ጊዜ ውስጥ ወጣቱ ጥቂት ግን ምርጥ የግእዝ ቅኔያትን በቃሉ አጠና፤ ከአነባበባቸው እስካፈታታቸው አሳምሮ ዐወቀ። እንዲሁም ከታወቁት የአማርኛ ባህላዊና ዘመናዊ ግጥሞችና ቅኔያት ምርጥ ምርጦቹን በቃል ያዘ።

በተጨማሪ ከእንግሊዝኛውና ከፈረንሳይኛው የታወቁ ጥንታዊና ዘመናዊ ቅኔያትን በቃል አጠና። የስንኛቸውን እሰካክና አቀነባበር፣ የምሥጢራቸውን አፈታት፣ የሰዋሰዋቸውን አገባብ ጭምር በአንጋፋው እየታገዘ ለመረዳትና ለመገንዘብ በቃ። እርግጥ በውጭ ቋንቋ በውጭ ባህል የተደረሰ ቅኔን በደንብ መረዳት ከባድ ስራ ነው። ቢሆንም ወጣቱ ሳይሰለች ሽንጡን ገትሮ አንጋፋው የሰጠውን የቤት ሥራ ባለማስተጓጎል ተወጣ።

***

ብሎ ብሎ የወጣቱ መመረቂያ ጊዜ ደረሰ። ቀኑ ሲቃረብ አንጋፋው እጁን ፀፍቶ ገረዲቱን ጠራ። ከተፍ አለች።

‹‹አቤት! ጠሩኝ እንዴ?››

ከኪሱ ገንዘብ አውጥቶ ሰጣት።

‹‹የወር አስቤዛ እኮ አላለቀም፤ ገንዘብ አለ›› አለች።

‹‹አለማለቁን አላጣሁትም። የዛሬ አሥራ አምስት ቀን እሑድ ምሳ የሚጋበዙ ሁለት እንግዶች አሉኝ። አንዱ የምታውቂው ነው ወጣቱ። ሌላው አንድ የኔው ቢጤ ሸበቶ ነው። እሱንም ታውቂዋለሽ።››

‹‹ወጣቱ ደሞ ምሳ ተጋባዥ የሆነው ከመቼ ጀምሮ ነው?›› አለች እንደመቀለድ፤ ‹‹ይኸው እዚሁ ቤት ሲመላለስ ድፍን ዓመቱ። ሲጋበዝ ነው እንዴ ምሳ እሚበላው፤ እንዲያው እግር ሲጥለው ነው እንጂ?››

አንጋፋው እንደ መሳቅ አለ። ‹‹እስካሁን ተማሪ ነበር፣ ቀላዋጭ፣ ዘኬ ለቃሚ፣ አሁን ደቀ መዝሙር ነው። ከእንግዲህ የሟያ ጓደኛዬ ሆኗል። ታናሽ ወንድሜ። ግብዣው ለእርሱ ክብር ነው – ለመመረቂያው።››

‹‹እሺ አሁን ምን ይሰራ ነው የሚሉት ለግብዣው?››

‹‹ገንዘቡን ሰጥቻለሁ። ጠላ ጥመቂ፣ ዳቦ ድፊ፣ ዶሮ ሥሪ፣ የምርቃቱን በዓል የምናከብረው በባህላዊ ሥነ ሥርዓት ስለሆነ የዕለቱ ዕለት እኔ እጀጠባብና ሱሪዬን ለብሼ ጃኖ እደርባለሁ። አንቺም ያገር ባህል ቀሚስ እንድትለብሺ።

‹‹ኩታስ አያስፈልግም?››

አልመለሰም።

‹‹ትእዛዝዎ ይፈጸማል›› ብላ በመቻኮል ወጣች።

ዕለቱ ዕለተ ሰንበት ነበርና ገረድ እንደ ወጣች ወዲያው ወጣቱ ደራሲ ገባ። ከተለመደው ሰላምታና ቀላል ጨዋታ በኋላ ጉባኤው በምር ተጀመረ።

‹‹እንግዲህ›› አለ አንጋፋው ‹‹በቅኔ ተማሪ ቤት ሥርዓት የመመረቂያህ ቀን ተቃርቧል። የዛሬ አሥራ አምስት ቀን እሑድ መጥተህ ከእኔና ከአንድ ቅኔ አዋቂ የሥነ ድርሰት አፍቃሪ ጓደኛዬ ጋር ምሳ ትበላለህ።››

‹‹ብቻ አንድ ነገር አለ የማይረሳ። በእኛ ተማሪ ቤት ተማሪው
ሁለት ቢሆንም አስተማሪው አንድ ብቻ ነው!››

‹‹ጥሪውን በደስታ ተቀብያለሁ›› አለ ወጣቱ በፈገግታ።

‹‹በበኩሌ የተቻለኝን ላንተ አድርጌ አለሁ። የራሴኑ መምህራን ውለታ ለመክፈል፣ ብድራቸውን ለመመለስ ተጣጥሬአለሁ። ከዚህ በኋላ በራስህ ነው መቀጠል። ‘መማር አሁንም መማር’ ተብሎ የለ? ‘ትምህርት እስከ ዕለተ ሞት’ ይባል የለ?››

ወጣቱ በአዛውንቱ አነጋገር መነካቱ አልቀረም። ቢሆንም የባለወረታነቱን ጥልቅ ስሜት በጨዋታ ሸፈነው እንጂ በጉልህ እንዲታይበት አልፈለገም።

‹‹ትዝ ይልዎታል? የዛሬ ዓመት መጀመሪያ እርስዎ ዘንድ በመጣሁ ዕለት ሺ ግጥም እንዲያነቡና ሐሳብዎን እንዲነግሩኝ ነበር ወጥሬ የያዝኩዎ። እርስዎ ግን ከስንፍና ይመስለኛል አሥሩን ብቻ ነው ያነበቡት።››

‹‹አዎንና፣ አዎ።››

‹‹አንብበውስ? ፍርድዎን እስካሁን አልሰጡም።››

‹‹ፍርዱን ላንተው ነው ለራስህ የተውኩልህ። የኔ ፈንታ ያለኝን ልምድና ጥቂትም ዕውቀት ለተከታዩ ትውልድ ማስተላለፍ ነው። ስጠየቅ ምክር ነው የምሰጥ፣ ፍርድ አይደለም።››

‹‹እኔ ደግሞ እልህ ይዞኝ ግጥሞቼን ሁሉ ‘ሀ’ ብዬ አንድ ባንድ ሰሞኑን አነበብኳቸው። ለአንዳንዶቹ ፈረድኩላቸው፤ ባንዳንዶቹ ፈረድኩባቸው፤ ከሺው ስንት እንደተረፉኝ ያውቃሉ?›› አለ ወጣቱ ቁጥራቸውን መናገር እያዳገተው።

‹‹አውቃለሁ፣ ቁጥሩን አትንገረኝ:: ያለፈው እሑድ የሰጠኸኝን አዲሱን ግጥምህን ግን በጣም ነው የወደድኩልህ። ዘመናዊ ያማርኛ ቅኔ ነው የተቀኘኸው።››

አንጋፋው በቃል አልተናገረም። ራሱን ብቻ ላይና ታች በዝግታ ነቀነቀ – በአዎንታ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top