አጭር ልብወለድ

ዓዳንደር

የመንደሯን ስም ዓዳንደር ይሉታል። ትክክለኛ ስሙ ዓዲ ዳንደር ነው። አጥሮ ሲነገር ግን ዓዳንደር ይሆናል። የኮሸሽላ አገር ወይም ኮሸሽላ የበዛበት አካባቢ ማለት ነው፤ በትግርኛ ቋንቋ።ሆኖም በአሁኑ ጊዜ ብዙም ኮሸሽላ የለ። የአገሩ አህዮች በጣም ስለሚወዱት በልተው ጨርሰውታል። ስሙ ግን የነበረውን ለማስታወስ እንዳለ አለ።

የዓዳንደር መንደር የምትገኘው በትግራይ ክፍለ ሀገር፣ በራያና ዓዘቦ አውራጃ፣ በእንዳመኾኒ ወረዳ ልዩ ስሙ ጽበት በሚባል አካባቢ ውስጥ ነው። ማይጨው ከተማ ሆነው ወደ ሰሜን ሲመለከቱ ደጋው አካባቢ በሩቁ ይታያል።የመሬቱ አቀማመጥ ደረጃ በደረጃ እያደገ ሄዶ በመጨረሻ በሰማይ ጠቀሱና በጉም ለባሹ በደባር ተራራ ይደመደማል።ዓዳንደር በደባር ተራራ ጥግ ከሚገኙ መንደሮች አንዷ ነች።

ወደ ዓዳንደር ለመሄድ ከማይጨው ከሆነ የምትነሱት በአስባሾ አርጋችሁ ነው የምትሄዱት። አስባሾ የከተማይቱ “ቢያሳ” ነው። አስባሾ ስትደርሱ ወደ ግራ ትጠመዘዙና ትንሽ እንደሄዳችሁ ከተማዋን በዳር በኩል ዳስሶ የሚሄደውን ቓጥን ገረብ (1) ታገኛላችሁ። ወንዙን ተምቦጫርቃችሁ ትሻገራላችሁ። ካስፈለገም እጃችሁን፣ እግራችሁን ተጣጥባችሁ ከወንዙ ወደ ላይ ራመድ ብላችሁ በእፍኛችሁ ኩል ከመሰለ ቀዝቃዛ የደጋ ውሃ ጠጥታችሁ ጥማችሁን ታረካላችሁ። ያገሬው ሰው እንደዚያ ነው የሚያደርገው።

ቓጥን ገረብን ተሻግራችሁትንሽ እንደተጓዛችሁ ዓዲ ጠበብቲ (2) የምትባለውን ትንሽ መንደር ታገኛላችሁ።የሸክላና የብረት ዕቃ ሠሪዎች መንደር ነች። መንገደኞች ያቺን መንደር የሚያቋርጡት በፍርሃት ነው።በተለይ ሕፃናት በእናቶቻቸው ወይም በአባቶቻቸው ነጠላ ውስጥ ተደብቀው ነው የሚያልፉት።

ዓዲ ጠበብቲን እንዳለፋችሁ እኔ ነኝ ጎበዝ ተጓዥ የሚለውን ሁሉ የሚፈታተንና በየጊዜው እያስቆመ ቁና ቁና የሚያስተነፍስ ረጅም ዳገት ያጋጥማችኋል። ዳገቱን እንደምንም አሸንፋችሁ ከአፋፉ ብቅ ስትሉ ተፈጥሮ በዳገቱ የበደለችውን ያህል ለመካስ ያሰበች ይመስል በመሃሉ የሚጎርፍ ወንዝ ሰንጥቆት የሚያልፍ ለጥ ያለው የአፋጀ ለምለም ሜዳ ይቀበላችኋል።

አፋጀ በተራራዎች የተከበበ ሰፊ መስክ ነው። ያገሩ ከብት ሁሉ በዓመቱ ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ ተሰማርቶ የሚውለው እዚህ መስክ ነው። ኢትዮጵያን ከሰሜን ወደ ደቡብ ከሚያቋርጡ ቓፍላዮች(3)፣ የጥንት የነጋዴ መንገዶች አንዱ በዚህ መስክ በኩል አቋርጦ ስለሚሄድ ቓፍላይ በየጊዜው ሲያልፍ እዚህ ያድራል።ውሃውና ግጦሹ ያመቻል። ነጋዴው ከኩሉም፣ ከማተቡም፣ ከእጣንና ከርቤውም፣ ከቅመማቅመሙም ቆነጣጥሮ በመያዝ በየተራራው ጥጋጥግ ባሉት መንደሮች እየዞረ በልዋጭ የበሰለ ምግብና በቀላሉ ሊበስል የሚችል እንደ ስንዴ፣ አተር፣ ባቄላና ሽንብራ የመሳሰለ ጥራጥሬ ሰብስቦ ይሄዳል።

የሜዳው የተለመደ ስም ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩላችሁ “ፋ” ሳይጠብቅ “አፋጀ” ቢባልም፤ በድሮ ጊዜ በዚህ ቦታ ላይ ከፍተኛ ጦርነት ተካሂዶ ብዙ ህዝብ ያለቀበት ቦታ ነበር ብለው ሽማግሌዎች ሲናገሩ ሰምቻለሁ።

የአፋጀንም ወንዝ ሲሻገሩ እጅና እግርን መለቃለቅ፣ከውሃውም ጎንጨት ማድረግ አለ። የአገሩን ውሃ መቅመስ ደምብ ነው። ከአካባቢው ጋር የቀረበ አካላዊና መንፈሳዊ ግንኙነት ይፈጥራል።

የአፋጀ ሜዳ እንዳለቀ ሌላ አንቱ የተባለ ዳገት ይመጣል። ይኸኛው የዓዳንደር ዳገት ነው። ዳገቱን ተያይዛችሁ ረዘም ላለ ጊዜ እንደተጓዛችሁ በስተቀኝ በኩል የዓዳንደርን መንደር በቅርቡ ታያላችሁ። የዳገቱ መንገድ ግን አላለቀም። በግራ የዮሐንስን ቤተስኪያን አልፎ ወደ ሸማት ይሄዳል። በፊት ለፊት ደባር ተራራ ጫፍ ስር እስኪደርስ ድረስ ይቀጥላል። እኔና እናንተ ግን በስተቀኝ ወደ ዓዳንደር መንደር ጎራ እንላለን። የምነግራችሁ አጭር ታሪክ የሚጀምረውና የሚያልቀው እዚህች መንደር ውስጥ ነው።

የዓዳንደር መንደር ያረፈበት ቦታ በምዕራብ በኩል ተዳፋት ይሆንና ከጫፉ ላይ ደልደል ያለ ሆኖ በስተምሥራቅ በኩል ግን ጭው ያለ ገደል ነው።የሰውም ሆነ የከብት መውጪያና መግቢያ በአንድ አቅጣጫ ማለትም በተዳፋቱ በኩል ብቻ ነው።

ዓዳንደር የአራት ቤተሰብ መንደር ነች። ጋጣውና በረቱ ሳይቆጠር ቤቶቹ አራት ብቻ ናቸው። ከፊት ለፊት ጎልቶ የሚታየው ቤት የቓሺ ማዕረጉ ቤት ነው።ቓሺ (4) ማዕረጉ የዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ናቸው።የቤተ ክርስቲያን የማደሪያ መሬትና የርስት መሬት እያረሱ፤ ልጆቻቸውንም እያሳረሱ ይኖራሉ።

ከቓሺ ማዕረጉ ቤት በስተኋላ ያለው ቤት የአያ ኻሕሳይ ነው። አያ ኻሕሳይ ብርቱ ገበሬ ነው። ሚስቱ ስንዳዮትባላለች። ሕሉፍ የሚባል የ13 ዓመት ልጅ አላቸው፤ ጎበዝ እረኛ ነው። ጠቋር የሚባል ድፍን ጥቁር ውሻ አለው። ጠቋር አንዳንድ ቀን ከሕሉፍ ጋር ከብትሲጠብቅ በረሃ ይውላል። አብዛኛውን ጊዜ ግን መንደር ጠባቂ ነው። ማታማታ ሕሉፍ ከብቶቹን እየነዳና እየዘፋፈነ ሲመጣ ሲሰማው እየሮጠ ሄዶ መሃል መንገድ ላይ ይቀበለውና አጅቦት መንደር ይገባል።

ከቓሺ ማዕረጉ ቤት በስተምሥራቅ ያለው ቤት የአደይ ኪዳን ነው። አደይ ኪዳን የ50 ዓመት ባልቴት ናቸው። ባላቸው ከዛሬ አስር ዓመት በፊት ጋዝ (5) ወርደው ሌሎች ጓደኞቻቸው ገድለው፤ ከብት ዘርፈው ሲመለሱ እሳቸው በዚያው ቀሩ። የሚኖሩት ትዳር ይዘው ጎጆ የወጡ ልጆቻቸው እየረዷቸው ነው። ሌላ ባል አላገባም ብለው ብቻቸውን ይኖራሉ።

ከተጠቀሱት ሶስት ቤቶች ለብቻው ፈንጠር ያለና ወደ ገደሉ ቀረብ ብሎ የቆመው ቤት የአያ አድሓና ነው። የዛሬ አስር አመት ከአደይ ኪዳን ባል ጋር ለጋዝ ጠልጣል ወርደው በህይወት ከተመለሱት ሰዎች አንዱ ነበሩ። ሆኖም ለጊዜው በህይወት ይመለሱ እንጂ በዛ በቆላ አገር በንዳድ ማለትም በወባ ተነድፈው ኖሮ እንደተመለሱ ታመው ወዲያው ሞቱ። አራት ልጆች ትተው ነው የሞቱት። አባታቸው ሲሞቱ ልጆቹ ገብሩ አስራ ስ ሌላ ባል
አላገባም ብለው ብቻቸውን ይኖራሉ።

ምንት ዓመት፣ መረሳ አስራ አምስት ዓመት፣ ሥላስ አስር ዓመት፣ ሐድሽ ደግሞ አራት ዓመት ነበሩ። እናታቸው አደይ አለማሽ በልጆቻቸው እየተረዱ ይቀበለውና አጅቦት
መንደር ይገባል።

ቤተሰቡን ማስተዳደር ቀጥለው ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሁለቱ ትላልቅ ወንዶች ልጆች በተከታታይ ትዳር ያዙላቸው። አሁን አደይ አለማሽ እንደ አደይ ኪዳን ትዳር በያዙ ልጆቻቸውና በዘመዶቻቸው እየተረዱ ይኖራሉ። የመጨረሻ ልጃቸው ሓድሽ አሁን አስራ አራት አመቱ ነው። የእናቱን ከብት ይጠብቃል፣ለእርሻም ደረስኩ እያለ ነው።

አባቷ ሲሞቱ የአስራ አራት አመት የነበረችው ሥላስ ዛሬ ሃያ አምስት ዓመት ሊሞላት ትንሽ የቀራት ወጣት ሴት ነች። እናቷና ዘመዶቻቸው የሀብታም ልጅ ነው በማለት ባራኪ ለተባለ አመለጥፉ ባል ድረዋት ከአራት ዓመት በኋላ አመሉ ስለአስመረራት የአንድ ዓመት ህፃን ይዛ ወደ እናቷ መጣች። ከመጣች ስድስት ወር ያህል ሆኗታል። ከባሏ ጋር ትፋታ አትፋታ፤ ካልተፋቱ ጉዳዩ በሽማግሌ የሚታይ መሆኑ ወይም አለመሆኑ የታወቀ ነገር የለም። ቤተሰቡ ሁኔታውን ድፍን አድርጎ ነው የያዘው።

የሥላስ እናት በወጣትነታቸው አገር ያደነቃቸው የጠይም ቆንጆ ነበሩ። ሥላስም በእናቷ የወጣች ጠይም ውብ ሆናለች። ከቁመቷ ዘለግ ብላ ሰውነቷ ተመጥኖ ሞላ ያለ ነው። የባላገሩን ስድ ቀሚስ ለብሳ ወገቧን በእስበሱ መቀነት ሸብ ስታደርገው ዳሌዋን፣ ሽንጧንና ጡቶቿን አስተባብሮ የሚፈጠረው የሰውነት ቅርፅ የአይን ሲሳይ ነው። በቀጭን ሹርባ የተሰራችው ረጅም ፀጉሯ ትከሻዋ ላይ ከአረፈ በኋላ ግራና ቀኝ በጆሮዋ ስር ወደ ፊት ዘምበል ብሎ ከአንገቷ ጋር ይጫወታል። ፈገግ ስትል በንቅሳት ከታጀበውና የወይራ መፋቂያ ከዋለበት ልቅም ያለው ጥርሷ እንዲሁም ከአይኖቿና ከአጠቃላይ ውብ ፊቷ የሚፈልቀው ውጋገን እኒያ ጎጃሞች እንደሚሉት ራት ያስበላል። በአጭሩ ሥላስ ከደባር ምላሽ የተፈጥሮ ንጥረ ነገራት ተለቅማ፣ በዘር በሰንሰለት ምስጢር ተቀምማ፣ በፍቅር ቋንቋ ተተርጉማ፣ ባገር ልማድ ባገር ባህል ታርማ የበቀለች የዓዳንደር ቆንጆ ፍሬ ነች። ባል አግብታ ከመሄዷ በፊ አበባ
ውበቷና የአፍላ ሴትነት ግርማዋ ደመቀ።

ት ልቡን ያልማረከችውና ያ የሀብታም ገበሬ ልጅ ሲወስዳት ያልቀና ያገር ኮበሌ አልነበረም።

ከአራት ዓመት ያህል በኋላ ወደ እናቷ ቤት ስትመለስ ምንም እንኳን በኑሮዋ የገጠማት ብስጭት መንፈሷን ትንሽ ሰበር ያደረገው ቢሆንም የቅድመ ጋብቻ ውበቷ በሙሉ ሴትነት አፍላ ግርማ ይበልጥ ዳብሯል። በተለያ ባለፉት ስድስት ወራት ልጄ ተጎዳችብኝ ብለው የተቆጩት እናት ክብደት ያለው ስራ እንዳትሰራ ከልክለው ምርጥ ምርጡን እየመገቡ ከልጇ ጋር ተንከባክበው ስለያዟት በፊቷ ላይ ይታይ የነበረው የመከፋት ጭጋግ ጠፍቶ ፍንድስድሱ እንደወጣ የመስከረም አበባ ውበቷና የአፍላ ሴትነት ግርማዋ ደመቀ።

የዓዳንደር ሰዎች በአካባቢው ባሉ መንደሮች ውስጥ ከሚኖሩት ሰዎች ጋር አብዛኛውን ጊዜ የመገናኘት ዕድል የሚያጋጥማቸው ቤተስኪያን ለመሳም ሲሄዱ ነው።ሥላስ ከባሏ ጋር ተጣልታ እናቷ ቤት መምጣቷን አገሬው ከሰማ ቆይቷል፤ቤተስኪያንም ደጋግማ ታይታለች።

በአገር ቤት፡ ወንድ በሌለበት በእናት ቤት የምትኖር ሴት፤ ያውም ቆንጆ ወጣት ሴት ያገሬውን ወንድ ፈተና ውስጥ ታስገባለች። የሥላስን ውበት ያዩና ያለችበትን ሁኔታ አውቀው የተመኟት ያላገቡም ሆኑ ያገቡ ወንዶች ብዙ ናቸው። ከእነዚህ አንዱ ባለ ትዳርና የአንድ ልጅ አባት የሆነው የቅርብ ጎረቤቷ አያ ካሕሳይ ነበር።

አያ ካሕሳይ ሥላስን ደፍሮ ጠይቋት አይሆንም ብላ ፊት ስለነሳችው የወንድነት ስሜቱ ተነክቶበት ቂም ይዟል የሚል ወሬ በሰፈሩ ይወራል። እውነቱ ግን አልታወቀም።

አንድ ቀን ሌሊት ወንድሟሐድሽ ሆዱን አሞት ሲያስታውከውና ሲያስቀምጠው ስለአደረ ጧት ከብት ጥበቃ ሊወጣ አልቻለም። የከብቶቹን ነገር ምን ማድረግ እንደሚሻል ምክክር ተደርጎ ሥላስ እኔ ይዤያቸው እወጣለሁ አለች። ስለዚህ ሞቅ ሲል በዚያውም የሚታጠብ የራሷንና የልጇን ጨርቃጨርቅ ለማጠብ ጠቅልላ ይዛ ከብቶቹን እየነዳች ወደ ማይሐዊ (6) ሄደች። ሰዓት ሲደርስ የምትቀምሳት በርበሬ የተነሰነሰባት ግማሽ ቕጻ (7) አጥፋ በነጠላዋ ውስጥ ይዛለች።

ማይሐዊ ከመንደሩ በስተምሥራቅ ሁለት ኪሎሜትር ያህል ርቆ የሚገኝ ወንዝ ነው። የወንዙ ግራና ቀኝ ደናም ሲሆን አካባቢው ሜዳማ ስለሆነ ብዙ እርሻዎች አሉ። ጊዜው የበጋ መገባደጃ አካባቢ ነው። ገበሬዎች መሬታቸውን እያረሱ ለክረምት ዝሪት ይዘጋጃሉ። ሥላስ ከብቶቹ በወንዙ አካባቢ እንዲለቃቅሙ ትታ የያዘችውን ልብሳልብስ ልታንጨፈጭፍ ወደ ውሃው አመራች።

የበጋዋ ፀሐይ መሬቱን ማጋል ጀምራለች። ጊዜው ለልብስ አጠባ ያመቸ ነው። ደረቁ አየር እርጥቡን ጨርቅ በአንድ አፍታ ያደርቀዋል። ሥላስ መጀመሪያ ነጠላዋን ታጥባለች፤ ነጠላዋ ሲደርቅላት እሱን አሸርጣ የለበሰችውን ቀሚስ አውልቃ ታጥባለች። ከዚያ የልጇና ሌሎች ጨርቃ ጨርቆች ይቀጥላሉ። ከዚያም አንድ ሰዋራ ቦታ ፈልጋ ሰውነቷን ትታጠባለች። ማን ያውቃል። ምንም በረሃ ቢሆን ሰው አያየኝም አይባልም። ከዚያም አመሻሽ ላይ ቀስ እያለች ከብቶቿን እያስለቀመች በጊዜ ወደ ሰፈሯ መቃረብ ትጀምራለች። እንዲህ እያለች ስታስብ እየተፍለቀለቀ ከሚወርደው ውሃ ጋ ደረሰች።

ጊዜ አለፈ። መሸትሸት ሲል አደይ አለማሽ ልጃቸው ስትመጣ የምትቀምሰውን መክሰስ አዘጋጅተው ይጠብቃሉ። ሆኖም ትመጣለች ብለው ባሰቡበት ጊዜ አልመጣችም። ከመንደሩ አፋፍ ላይ ሆነው የማይሐዊን አካባቢ በአይናቸው ቃኙ። ሥላስ ከብቶቹን እያስለቀመች ቀስበቀስ ወደ መንደሩ ስትቃረብ ለማየት ነበር ብቅ ያሉት። ከብቶቹን በሩቁ ያያሉ፤ የእነሱ መሆናቸውን ግን ለይተው ለማወቅ አልቻሉም። የሰው ምልክትም አልታያቸውም።

ድስት ጥደው ስለነበር ቶሎ ወደ ቤት ተመለሱ። የሚሆነውን አደራርገው ድስቱን ካወረዱ በኋላ ልጃቸው ወደ መንደሩ ተቃርባ እንደሆን ለማየት ተመልሰው ወጡ። ከብቶቹ በእርግጥ የእነሱ ናቸው። ወደ መንደሩ ተቃርበዋል። ሥላስ ግን በአጠገባቸው አትታይም። በአገሩ አጠራር ስልት “ሥላስ ይው!” እያሉ ተጣሩ። የአካባቢው ገደልና ሸንተረር ጥሪያቸውን እያስተጋባ ደግመው ደጋግመው ተጣሩ። ግን ከልጃቸው መልስ አላገኙም። ልባቸው መስጋት እየጀመረ ወደ ቤት ተመልሰው ገቡ።

ምሽቱ ተፋጠነና ለዓይን መያዝ ጀመረ። ከብቶቹ በደመ ነብስ ተከታትለው ወደ ቤት መጡ። ሥላስ ግን አብራ አልመጣችም። የአደይ አለማሽ ስጋት ወደ መደናገጥ ተለወጠ። ከብቶቹን ወደ በረት አስገብተው ከዘጉ በኋላ ነጠላቸውን ደርበው ከብቶቹ በመጡበት መንገድ እየሄዱ ልጃቸውን መጥራት ጀመሩ። ብዙ ሄዱ። መጨለም ሲጀምርና የልጃቸውን ምልክት ሲያጡ ነገሩ አስፈርቷቸው አፋፍ ላይ ሆነው ኡኡታቸውን ለቀቁት። ኡኡታውን ሰምተው ከየመንደሩ የደረሱ ወንዶች የሥላስን ከከብቶች ጋር ወጥታ አለመመለስ ሲረዱ ተደናግጠው በችቦ እሳት ብርሃን ዋለችበት የተባለውን አካባቢ ማሰሱን ተያያዙት።ማይሐዊን ተሻግሮ በላጎ በሚባለው አከባቢ የሚኖሩት ሁለቱ የሥላስ ወንድሞችም ሰው ተልኮባቸው፣ ያተጣልታው የመጣች ባሏም ጭምር fመጥቶ ፍለጋው ቀጠለ። ሥላስ ግን አልተገኘችም።

ዕንቆቅልሹ አልፈታ አለ። የልጇ አባትወስዷታል እንዳይባል እሱም ከፈላጊዎች አንዱ ነው።ጎርፍ ወሰዳት እንዳይባል ወንዙ ይህን ያህል ሃይለኛ አይደለም። ሰው የሚያሰጥም ጥልቀት ያለው ውሃም የለው። በቀን አውሬ በላት እንዳይባል በዚያ አካባቢ የታወቀ አደገኛ አውሬ የለም። ያለው ጅብ ነው፤ ያገሩ ጅብ ደግሞ እንኳን በቀን ሌሊትም ሰው አይተናኮልም። ጎረምሶች ወስደው እቤታቸው ደብቀዋት ይሆን? እንደዚያ ቢሆን አገር እንደዚያ ሲረበሽ ዝም አይሉም። መንገደኞች አፍነው ወስደዋት ይሆን? ማን ያውቃል፣ሥላስን ያየ ዓይን ልቡ ብዙ ይመኛል።

እኩለ ሌሊት ሆነ፤ የችቦው እሳት እየጠፋ አስቸገረ። ሰውም ተዳከመ። በጨለማ መደናበሩ ዋጋ ቢስ መሆኑን በመረዳት ፍለጋውን ሲነጋ ለመቀጠል ሰው ተሰማምቶ ወደየቤቱ ተመለሰ።

የሥላስ ወንድሞችና የልጇ አባት እንዲሁም አያ ካሕሳይ አደይ አለማሽን ደግፈው ወደ ቤታቸው ወሰዷቸው። በአካልም በመንፈስም ደክመዋል። ብቸኛ ሴት ልጃቸው ክፉ ቢደርስባት ሃዘኑን አይችሉትም። ምነው ጧት ባልሰደድኳት! ምነው እኔው ራሴ በሄድኩ! እያሉ በቁጭት እሳት ይቃጠሉ ጀመር።

አያ ካሕሳይም አደይ አለማሽን እያጽናናከሸኛቸው በኋላ ትንሽ አርፎ ሊነጋጋ ሲል ሌሎችንም ሰዎች አስተባብሮ ለፍለጋው እንደሚነሳ ተናግሮ ወደ ቤቱ ሄደ።

ሲነጋጋ ሰዎች ተጠራርተው ወደ ማይ ሐዊ አካባቢ ተጉዘው ጎህ ሲቀድ እዚያ ደረሱ።የንጋቱ ብርሃን ጨለማውን እየገፋ ጉድባውን፣ ጎሬውን፣ ደኑን ግልጥ ያደርጋል። የጥዋቱ የደጋ ብርድ ሰውነትን ይጨብጣል። አካባቢው ፀጥ በማለቱ የወንዙ መጉረፍና መፍለቅለቅ ጎልቶ ይሰማል። ሰዎቹ የአካባቢውን ደንና ቁጥቋጦ አንድ በአንድ ዳስሰው ምንም ስላላገኙ የወንዙን ረጅም ቁመት ተከፋፍለው በየኩሬውና በየቋጥኙ ሥር መፈለግ ጀመሩ። አሁን ፀሐይ ቀጥታ ብርሃኗን መፈንጠቅ ጀምራለች። ወንዙ ውስጥ ግን አሁንም ጥላማና ብርዳማ ነው።

ከወንዙ ወደታች በኩልድንገት ወይአነ! ወይ አነ! ወይ አነ! የሚል ድምፅ ተሰማ። ሰው ሁሉ ጩኸቱ ወደተሰማበት ቦታ እየሮጠ መጣ። መረሳ ራሱን በሁለት እጆቹ ይዞ ጎምበስ ቀና ጎምበስ ቀና እያለ እየየውን ይለቀዋል። ሰዎቹ መረሳ ከቆመበት ቦታ ሲደርሱ በዓይናቸው የገጠማቸው ትርኢት የሚዘገንን ነበር። ያቺ ውብ፣ ያቺ ለምለም ሴት ከወንዙ ድንጋያማ ዳርቻ አንዳች በሚያክል ቋጥኝ ድንጋይ ሥር በግምባሯ ተደፍታ ተጨፍልቃ ሞታ አገኟት። አሰቃቂ ሞት! ቀሚሷን እንደለበሰች ነች። ነጠላዋ እና የልጇ ጨርቅ ተጠቅልሎ አንድ ድንጋይ ስር ተወሽቋል። ሶስት ያህል ወንዶች ተረዳድተው አስክሬኑን የተጫነውን ድንጋይ አንከባለው አስወገዱት። ከዚያም አስከሬኑን ወደ ሰፈር ወሰዱት። በአፋፍ ለአፋፍ የአቃብሩን ጥሪ ድፍን ደባር ከተሰበሰበ በኋላ ያቺ ያለጊዜዋ የተቀጠፈች የዓዳንደር አበባ በታላቅ አጀብ አንጀት በሚያቆስል ሀዘን ተሸኝታ ዮሐንስ ቤተክርስቲያን ተቀበረች።

ከቀብሩ በፊትም ሆነ በኋላ ፍቺ ያላገኘው ዕንቆቅልሽ የሥላስ አሟሟት ነበር። ማን ነው የገደላት? በዚያ ቋጥኝ እንዴት ልትጨፈለቅ በቃች? ሰው ነው እንዳይባል አንድ ሰው ያን ቋጥኝ ሊያንቀሳቅሰው አይችልም። ድንገት በቋፍ ላይ የነበረ ቋጥኝ ላዩ ላይ ስትቆምበትና ሲንከባለል ከስሩ ወድቃ ጨፍልቋት ነው? ብዙ ጥያቄዎች ተነስተዋል፤ ብዙ መላምቶች ቀርበዋል፣ ዕንቆቁልሹ ግን አልተፈታም። አንድ የተረጋገጠ ነገር ግን ነበር። ይኸውም ሥላስ ወደ ማይሐዊ በሄደችበት ዕለት አያ ካሕሳይ በዚያ አካባቢ ሲያርስ መዋሉ ነው። ይህ ተጨባጭ ሁኔታ ቀደም ሲል ይወራ ከነበረው ሀሜት ጋር ተዳምሮ በህዝብ ዘንድ ጥርጣሬ አሳደረ።

አያ ካሕሳይ ሥላስ ወደ ማይሐዊ በሄደችበት ዕለት ወደ ማይሐዊ ለእርሻ መሄዱ በዕቅድ ነው ወይስ በአጋጣሚ? በዕቅድም ሆነ በአጋጣሚ ማይሐዊ ሲያገኛት ልድፈርሽ ብሏት ይሆን? ልድፈርሽ ብሏት እምቢ ካለችው ይገድላታል? እንዴትስ ያን ቋጥኝ ብቻውን ሊያንቀሳቅሰው ይችላል? ሕዝቡ በሓሳብ ይተራመሳል። በእርግጥ ይህ ነው የሚያሰኝ ተጨባጭ መረጃ ግን አልነበረም።

ገብሩና መረሳ ግን የእህታቸው ገዳይ አያ ካሕሳይ ለመሆኑ ቅንጣት ያህልአልተጠራጠሩም። አመቺ ጊዜ ነበር የሚጠብቁት። ነገር በሆዳቸው ሲያብላሉ ሰንብተው ሥላስ በተቀበረች በአስራሁለተኛው ቀን ሁለቱ ወንድማማቾች አማቻቸውን ባራኪን አስከትለው በእኩለ ሌሊት በጠፍ ጨረቃ ከበላጎ ወደ ዓዳንደር አመሩ። ከሶስቱ ጠመንጃ ያልያዘው ባራኪ ብቻ ነበር።

አያ ካሕሳይ እና ሚስቱ ስንዳዮዶል (8)ላይ ተኝተዋል። ሕሉፍ ለብቻው መደብ ላይ ተኝቷል። ሁሉም በየፊናቸው በስራ ሲባዝኑ ውለው ደክሟቸው አፍላ ዕንቅልፍ ላይ ነበሩ። ሶስቱቂመኞች ዓዳንደር ሲደርሱ ወደ አያ ካሕሳይ ቤት አመሩ። የአያ ካሕሳይ ውሻ ጠቋር መጮህ ሲጀምር የሌሎች ውሾችም ጩኸት በዚያ በውድቅት ሌሊት በየመንደሩ አስተጋባ። እነ ገብሩ ውሻውን እንደምንም አባርረው ወደ ፈለጉት ቤት እንደደረሱ፤ ገብሩ “እዚህ ቤት!” ብሎ ተጣራ። መጀመሪያ መልስ አልነበረም።

“እናንተ ቤቶች! እዚህ ቤት!”

“ማነህ?” አለ አያ ካሕሳይ።

“እንግዶች ነን ከሩቅ የመጣን አንድ ጊዜ ብቅ በሉ”

አያ ካሕሳይ ምናልባት ከሩቅ የመጣና መንገድ ላይ የመሸበት ዘመድ ይሆናል ብሎ በማሰብ ተነስቶ ልብሱን እየለበሰ ሕሉፍን ቀስቅሶ በሩን እንዲከፍት ላከው።

ሕሉፍ በግማሽ ንቃት ግማሽ እንቅልፍ በጨለማ እየተደናበረ መሸጎሪያውን ስቦ በሩን ከፈት አደረገው። ተዘጋጅቶ ይጠብቅ የነበረው ገብሩ ለጋውን ልጅ በጥይት ግምባሩን ብሎ ጣለው።

መረሳ በሩን በርግዶ ቤት ውስጥ ሲገባ ከአያ ካሕሳይ ጋር በጨለማ ግብግብ ተያያዙ። አያ ካሕሳይ ብድግ አድርጎ መሬት ላይ ሲጥለው እሱም እላዩ ላይ ወደቀ። መሬት ላይ እየታገሉ ሳሉ ገብሩ ገብቶ የጣለው ወንድሜ ነው በማለት በአያ ካሕሳይ ስር ሆኖ የሚፈራገጥ ወንድሙን በጥይት ደረቱ ላይ አለው። ወገቡን ጠፍረው ይዘው የነበሩት የመረሳ እጆች ሲለቁት አያ ካሕሳይ ተንደርድሮ ከቤት በመውጣትና በሚያስደንቅ ፍጥነት በአጥር ዘልሎ በማምለጥ በመንደሩ ዳርቻ ከመጠን በላይ ተመችቶት የሰው ቁመት ያህል በበቀለ ለምለም የሳማ ዱር ውስጥ ዘሎ ገብቶ ተደበቀ።

ለአጭር ጊዜ ገብሩ የሰራውን ባለማወቁ እሱም ሆነ ውጭ የሚጠብቀው ባራኪ በሁኔታው ተደናግረው ነበር። ገብሩ የፈፀመውን ስህተት እንደተረዳ ሰማይ ምድር ዞረበት። ህሊናውን ሲገዛ የንዴትና የፀፀት ነበልባል እያቃጠለው ባራኪም የመረሳን ጠመንጃ አንስቶ አያ ካሕሳይን ለማደን ሮጠው ተከታተሉት። ርቆ እንደማይሄድ ስላወቁ የአከባቢውቁጥቋጦ አንድ ሳይቀር እያገላበጡ ፈለጉ። በየቦታው አደፈጡ። ሳማው በበቀለበት አከባቢ ተመላለሱ። ሳማው ውስጥ ይገባል የሚለው ሃሳብ ግን በአእምሯቸው ውስጥ ፈፅሞ አልገባም።

አንጀታቸው አርሮ ወደ አያ ካሕሳይ ቤት ተመለሱ። የሕሉፍንና የመረሳን ሬሳ ተራምደው ገብተው ቤት ውስጥ ስንዳዬን ቢፈልጉ አጧት። እሷን ፍለጋ ተያይዘው ብዙም ሳይደክሙ አደይ ኪዳን ቤት ተደብቃ አገኟት። ከድንጋጤዋ ብዛት ቀሚሷንም አልለበሰችም። የሌሊት ልብሳቸው የሆነውን ሸማነ (9) ለብሳ ነው ነፍሷን ለማዳን አደይ ኪዳን ቤት ሮጣ የተደበቀችው። የአደይ ኪዳንን መማጠን ከምንም ነገር ሳይቆጥሩ ስንዳዬን እየጎተቱ ወደ ውጭ አወጧት። ስንዳዬን ሲያሰቃይዋትና ስትጮህ ባሏ አላስችል ብሎት ከተደበቀበት ይወጣ ይሆናል የሚል ሃሳብ ነበራቸው። ስለዚህ ጩኸቷ በአካባቢው እንዲሰማ ወደ መንደሩ ዳር አያ ካሕሳይ በተደበቀበት የሳማው ዱር አጠገብ እየገፈተሩ ወሰዷት።እዚያ መሬት ላይ ጥለው ሁለቱ ወንዶች እየተፈራረቁ በጥፊ፣ በእርግጫ፣ በሰደፍ ይደበድቧት ጀመር።

“ጥሪው! ጥሪው! ያን ነፍሰገዳይ ባልሽን! ጥሪው ያድንሽ!”

“እባካችሁን ስለ ነፍስ! የት እንዳለ አላውቅም! ስለ ግድያውም ምንም የማውቀው ነገር የለም” እያለች እየጮኸች እንዲራሩላት ተማጠነች።

በንዴትና በበቀል የሰከሩት ሁለት አረመኔዎች ለስንዳዬ መማጠን ጆሮም አልነበራቸው። የስቃይውርጅብኙንቀጠሉባት። በድብደባ ሰውነቷ ደቀቀ። ይህ አላረካቸው ብሎ የለበሰችውን ሸማነ ገፍፈው ሹርባዋን ይዘው እርቃነ ስጋዋን አውጥተው መሬት ለመሬት ጎተቷት። ስንዳዬ ገላዋ በዚያ ጭንጫ መሬት ላይ ሲጎተት የጀርባዋና የጎኗ ቆዳ ተገሸላለጠ። ገብሩያን ራቁት ቆዳ ሲያይ ሌላ የማሰቃያ መንገድ ታየው። ሳማ! ያን ተፈነዳድሶ የበቀለውን የደጋ ሳማ በነጠላው ይዞ እየቆረጠ የተላላጠ ጀርባና ጎኗን፣ጡቶቿን፣ፊቷን፣ጭኗን መላ ሰውነቷን አገላብጦ ገረፋት።የገረፈበት ሳማ እሾሁ ሲረግፍ ሌላ አዲስ እየቆረጠ በሰውነቷ ላይ አሸው። ሰውነቷ እንደ እሳት እየነደደ ነፍስና ስጋ ለሚለይ ስቃይ ተዳረገች።

“የነፍስ ያለህ! ያገር ያለህ! ኡ! ኡ!” ትላለች። ግን አገር ሁሉ እየሰማ ማንም ወጥቶ ሊያድናት የሞከረ አልነበረም። ሁሉም ለህይወቱ ፈርቶ በየቤቱ በሩን ዘግቶ ያዳምጣል። የእነገብሩ እናት አደይ አለማሽም ይሰማሉ።

አያ ካሕሳይም በዚያ የሳማ ዱር ውስጥ ተጨብጦ በአንድ በኩል የውጭ አካሉን ሳማው ያንገበግበዋል። በሌላ በኩል የሚወደው አንድ ልጁ በእምቡጥነቱ በመቀንጠሱ፣ የልጁ እናት ግማሽ አካሉ አጠገቡ ስትሰቃይ በጆሮው እየሰማ በአይነ ህሊናው እያዬ ለነብሱ አድልቶ ለጥሪዋ ባለመድረሱ ውስጠ ህሊናው በረቂቅ እሳት ይቃጠላል።

ስቃይ የበዛባት ስንዳዬ ተዳከመች። መጮኽም አልቻለችም፤ ገብሩና ባራኪ ያሰቡት እንዳልተሳካላቸው ተረዱ። ንዴት ያደነዘዘው፣ በቀል ሰብዓዊ ስሜቱን የደመሰሰው ገብሩ ራቁቷን እግሩ ስር የወደቀችውን ሰንዳዬንባለ በሌለ ኃይሉ በርግጫ አድቅቋት በሞትና በህይወት መካከል ትተዋት ከአጠገቧ ሄዱ።

ጥቂት ሄድ እንዳለ ገብሩ በእጁ የገደለው የወንድሙ ሬሳ እንደሚጠብቀው ትዝ አለው። ፀፀቱ አቃጠለው። ቆም ብሎ አንገቱን ደፍቶ አሰበ። ከመቅፅበት ወደ ኋላው ዞር በማለት በፈጣን ርምጃ ተመለሰ። ስንዳዬ ወድቃ ከምታጣጥርበት ቦታ ሲደርስ ጠመንጃውን አቀባበለ። በሰለለ ድምፅ “ስለነፍስ!” ስትል የጠመንጃውን አፈ-ሙዝ ከጆሮ ግንዷ ላይ ደግኖ ቃታውን ሳበው። የደባር ምላሽ ተራሮች የጠመንጃውን ድምፅ አስተጋቡ። ምስኪን ሴት!

ገብሩና ባራኪ በፍጥነት ወደ አያ ካሕሳይ ቤት ሄደው ከቤቱ ጣራ ሁለት ወፋፍራም እንጨት መዝዘው የመረሳን ሬሳ እዚ ላይ ወደጎን አጋድመው በመሸከም አገር ከፍርሃቱ ተላቅቆና ተሰባስቦ መጠቶ ማንነታቸውን ሳያያቸው በጨለማ ከመንደሩ ወጡ። ከዚያም ማይሐዊን ተሻግረው ወደ መንደራቸው ወደ በላጎ ሄዱ።

አደይ ኪዳን ተሾልኮው እያዩ የእነገብሩን መሄድ ሲያረጋግጡ ስንዳዬ ወደ ወደቀችበት ሄዱ። ሬሳውን ሲያዩ ከድንጋጤያቸው የተነሳ ለጥቂት ጊዜ አእምሯቸውን እንደመሳት አላቸው። እንባቸው እየጎረፈወደዚያ ተሸቀንጥሮ ተጥሎ የነበረውን ሸማነ በደመ ነፍስ አንስተው ሬሳውን አለበሱት። ጎትተው ቤት ሊያስገቡት ፈለጉ፤አቅማቸው አልቻለም። ከሬሳው ጎን ተቀምጠው ራሳቸውን በሁለት እጃቸው ደግፈው ለቅሶውን ተያያዙት።

የአደይ ኪዳንን ለቅሶ ሲሰሙ ቓሺ ማዕረጉና ሚስታቸው መጡ። በልጆቻቸው ድርብ ሞት ሃዘን ያቆራመዳቸው አደይ አለማሽም እየፈሩ እየቸሩ ከቤታቸው ወጥተው መጡ። በመጨረሻም አያ ካሕሳይ ካደፈጠበት የሳማ ዱር ቀስ ብሎ ወጥቶ ራቅ ካለ ቦታ እንደመጣ በመምሰል በጆሮው የሰማውን ጉድ በዓይኑ ሊያይ “ወይ አነ!” እያለ መጣ። ከመደንገጣቸው የተነሳ በሰዎች መካከል ምንም ዓይነት ንግግር አልነበረም። በቀጥታ ወደ አስከሬኑ ሄዶ ሸማነውን ትንሽ ገለጥ አድርጎ አየ።ደማቁ የጨረቃ ብርሃን በደበዘዘ ሁኔታ የሚዘገንን በደም የተሸፈነ ፊት አሳየው። ሸማነውን መልሶ አልብሶ በቓሺ ማዕረጉ እየተረዳ የሚስቱን ሬሳ ተሸክሞ ወደ ቤቱ አመራ። ቤቱ ሲደርስ ሬሳውን በራፉ ላይ አጋድሞ ወደ ቤቱ ገባና የልጁን ሬሳ ተሸክሞ አምጥቶ እናቱ ጎን አጋደመው። አደይ ኪዳንና የቓሺ ማዕረጉ ሚስት ቤት ውስጥ እሳት ካነደዱና መደቡን ካሰናዱ በኋላ ሬሳዎቹ ወደ ቤት ገቡ።

የተፈጠረው ሁኔታ ውስብስብ ያለና ግራ የሚያጋባ የመንፈስ ውጥረት የሰፈነበት ነበር። አደይ አለማሽ አያ ካሕሳይ የልጄ ገዳይ ነው ብለው ስለሚጠረጥሩ በልባቸው ቁስል አለ። የልጆቻቸውንም የልብ ቁስል ያውቃሉ። የልጆቻቸውን የበቀል ዕቅድ ግን አያውቁም። ሆኖም ይኸ ስራ የነሱ ሳይሆን አይቀርም የሚል ጥርጣሬ አላቸው። አያ ካሕሳይ ላይ ቂም ይያዙ እንጂ ስንዳዬና እሳቸው ጥሩ ጎረቤታሞች ናቸው።ስንዳዬስ ራሷ ተበዳይ አይደለችም? ባልዋ በላይዋ ላይ ሌላ ሴት ፈልጎ ከሆነ? ይህንንም እኮ ለማለት የሚቻለው አያ ካሕሳይ አደረገ የተባለውን ለማድረጉ ተጨባጭ ማስረጃ ሲኖር ነበር። ለጋው ሕሉፍስ በምን አበሳው ነው ለሞት የተዳረገው? ሕሉፍና ሐድሽ የሚዋደዱ የእረኝነት ጓደኛሞች ናቸው። አደይ አለማሽ የልጃቸው ሞት ሃዘን፣ በአያ ካሕሳይ ላይ ያላቸው ቂም፤ በነገሩ እርግጠኛ አለመሆን፣ የጎረቤታቸው የስንዳዬና የልጇየሕሉፍ አሳዛኝ ሞት፣ገዳዮቹ ልጆቻቸው የመሆን ጥርጣሬ እየተደበላለቁባቸው በሃሳብ ውዥንብር ተውጠው ይጨነቃሉ።

የተተኮሱጥይቶች ሶስት ናቸው። የሁለቱ ጥይቶች ጥፋት ታውቋል። የሶስተኛውን ጥይት ጥፋት ካለ አያ ካሕሳይ በስተቀር ለጊዜው ያወቀው የለም። አደይ አለማሽ የልጃቸው በልጃቸው እጅ መሞት መርዶ ገና ይጠብቃቸዋል። ለቅሶውን ግን ከአሁኑ ጀምረውታል። አሁን የሚያለቅሱት ለስንዳዬ፣ ለሕሉፍና በሰበቡም በቅርብ ለቀበሯት ልጃቸው ነው። በፊታቸው የሚጎርፈው እንባ ከብዙ ጥልቅና የሚጋጩ ስሜቶች የመነጨ እንባ ነው። ለሚጠብቃቸው ሌላ የሐዘን ምዕራፍ መግቢያ።

አያ ካሕሳይም እንደ አደይ አለማሽ በውስጡ የተለያዩ ስሜቶች ይፈራረቁበታል። የሚስቱና የልጁ ገዳዮች እናት አጠገቡ ቀምጠው ያለቅሳሉ። ልጆቻቸው ባይገድሉትም እሱንም ገድለውታል። ስለ ሥላስ ሞት በልቡ ያለውን እውነት የሚያውቀው እሱ ብቻ ነው። ተበድያለሁ ባይ ይሆን? እውነት ሥላስን ገድሎ እንደሆነስ?

ጊዜው ጥያቄዎች ተነስተው መልስ የሚሰጥበት ጊዜ አልነበረም። ሁለት ሬሳ አጋድሞ ነህ አይደለህም? አድርገሃል አላደረግህም?ተብሎ ክርክር የሚገባበት ጊዜ አልነበረም። በሆድ ውስጥ የሚብላሉ የተለያዩ ስሜቶችን አፍኖ ይዞ ወቅቱ የሚጠይቀውን የጋራ የእንባ ቋንቋ የሚናገሩበት ጊዜ ነበር። ስለዚህ መሃይማኑ እያለቀሱ፤ ቄሱ በቤተስኪያን ቋንቋቸው የሚሉትን እያሉ ሌሊቱ ነጋ።

አደይ አለማሽ በሃዘን ተቀምጠው እንዳሉ እቤታቸው ይፈለጋሉ የሚል መልዕክት ስለመጣባቸው ተነስተው ሄዱ። ከበላጎ የመጣ መልዕክተኛ ነበር። መልዕክተኛው ይዞ የመጣውን መልዕክት መሸፋፈን አስፈላጊ መስሎ አልታየውም። የልጃቸውን መሞትና የአሟሟቱን ሁኔታ ነግሯቸው ከዚህ በፊት በሥላስ ሞት እንደታየው ሹርባ ፀጉራቸውን በመንጨትና በመውደቅ በመነሳት ራሳቸውን እንዳይጎዱ በቅርብ ቆሞ ጠበቃቸው። ለብሰውት የነበረ ነጠላ ከትክሻቸው ላይ እንዘፍ ብሎ ወደቀ። አእምሯቸውን እንደ መሳት ብለው እቤቱ መሃል ምሶሶውን ተደግፈው ቁጭ አሉ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ድንገት ብድግ ብለው ቀኝ እጃቸውን እራሳቸው ላይ አድርገው ኡኡታቸውን እየለቀቁትና በግራ እጃቸው ነጠላቸውን መሬት ለመሬት እየጎተቱ ከቤት ወጡ። መልዕክተኛው ነጠላቸውን ሊያለብሳቸው እየሞከረ ተከተላቸው። ወደ ሌላ ሬሳ። ወደ ሌላ የሃዘን ቤት።

ወደ እነ አያ ካሕሳይ የሚመጣው የአቅራቢያ መንደሮች ሰው አደይ አለማሽ እንደ ማበድ ብለው እያለቀሱ ከመንደሩ እየራቁ ሲሄዱ ሲያይ ግራ ተጋብቶ ነበር። በኋላ ግን የሶስቱ ጥይቶች ታሪክ ሲነገር ሁኔታው ግልፅ እየሆነ መጣ።

የአገሩ ህዝብ በዓዳንደር በደረሰው እልቂት ጉድ እያለ እናትና ልጅ በዮሐንስ ቤተክርስቲያን በአንድ መቃብር ተቀበሩ። አደይ አለማሽም በዚያው ዕለት ምቻአል (10) ባላጎ ሁለተኛ ልጃቸውን ቀበሩ።

ዓዳንደር ከዚያ ወዲህ መንደር አልሆነችም። አያ ካሕሳይ ጠላቶች አድብተው እንዳይገድሉት ለመከላከል ወደሚችልበት ወደ ዘመዶቹ አገር ወደ ሽብጣ ሄደ። አደይ አለማሽ ሐድሽን ይዘው ከቀሪ አንድ ልጃቸው ጋር ተጠቃለሉ። የሥላስን ልጅ አባቱ ወሰደው። አደይ ኪዳንም ከአንዱ ልጃቸው ጋር ተጠጉ። ቓሺ ማዕረጉም ከዓዳንደር በስተ ምዕራብ ዮሐንስ ቤተክርስቲያንን አልፎ በሚገኘው ሸማት በሚባለው ሸለቆ ውስጥ አዲስ ቤት ሰርተው ሄዱ። እዚያም ብዙ አልቆዩም። ከጥቂት ዓመታት በኋላ አገልግሎታቸውን ማይጨው ከተማ ማርያም ሕዝባ ወደ ምትባል ቤተክርስቲያን ስለ አዛወሩ ቤተሰባቸውን ጠቅልለው ወደ ማይጨው ወረዱ። ዓዳንደር የደም መንደር ተብላ ኦናዋን ቀረች። የሥላስ ገዳይም አልተረጋገጠ።

ማስታወሻዎች

1.ቀጭን ወንዝ ማለት ነው (የወንዙ ስም)

2.የባለ እጆች መንደር።

3.ሲራራ ነጋዴ።

4.ቄስ።

5.ወንዶች አልፎ አልፎ በመኸር ጊዜ አዝመራቸውን ከአስገቡ በኋላ ጥጋብ ሲሰማቸውና ለጊዜው ስራ ሲፈቱ ለመግደልና ለመዝረፍ ጠልጣል /አዳል/ ይወርዳሉ። ይህ ባህላዊ ዘመቻ ጋዝ ይባላል።

6.የወንዝ ስም። የእሳት ውሃ ማለት ነው።

7.ያልቦካ የስንዴ እንጀራ፤ አይን ያለው ግን በሁለቱም ወገን ተገላብጦ የሚበስል።

8.ከመደብ በጣም ከፍ ብሎ ተገንብቶ ውስጡ ግን ባዶ ሆኖ በአንድ በኩል ተበጅቶለት የሚሰራ የመኝታ ቦታ። ውስጡ ክፍት ቦታ የዕቃ ማስቀመጫ ይሆናል። 9.በጥቁር የበግ ፀጉር የተሰራ ሽክሽክ የሌሊት ልብስ፤ማቅ።

10.ሚካኤል።በአገሩ የመሃይም አባባል የበላጎ ሚካኤል ማለት ነው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top