ቀዳሚ ቃል

ውድ አንባቢያን፣

‹‹ታሪኩን፣ ምንጩንና ባህሉን የማያውቅ ሕዝብ ሥር እንደሌለው ዛፍ ነው›› ማርከስ ጋርቬይ

በቅድሚያ ሁለተኛዋን እትም አንብበው ግድፈቶቻችንን ላመላከቱንና ሃሳባቸውን ላጋሩን በሃገር ውስጥም ሆነ በውጪ ያሉ ወዳጆቻችን ልባዊ ምስጋናችን ይድረሳቸው እንላለን። ምንጊዜም ምኞታችን ታዛ የሁላችን መነጋገሪያ፣ የእውቀትና የልምድ መጋሪያ መድረክ እንድትሆነን ነው። የመጽሔታችን ዋና ዓላማ የሃገራችንን ባህልና ሥነጥበብ በጋራ ማወቅ፣ ማስተዋወቅና ማበልጸግ ነውና። ከዚህ ዓላማ ጋር ሰምረው የሚሄዱ ጽሁፎችን ለሚልኩልን ወገኖቻችንም አምዶቻችን ሁሌም ክፍት ሆነው ይጠብቋቸዋል። “ታዛ” ሃሳቦቻችሁን በነፃነት የምታንሸራሽሩባት ቤታችሁ ናት።

በአሁኗ የ“ታዛ” እትምም የተለያዩ ጉዳዮችን ለመዳሰስ ሞክረናል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ሰላማዊ መሆን የሚገባቸው የስፖርት ሥፍራዎች የብጥብጥ መድረኮች እየሆኑ ነው። ይህም ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን የሚሸረሽር፣ የሃገራችንን መልካም ገጽታ የሚያበላሽና በአስቸኳይ ካልታረመ አንድነታችንንም የሚያናጋ ነው። የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል በቋፍ ያለውን የሃገራችን ስፖርት ደብዛውን ያጠፋዋል እንጂ ሌላ ፋይዳ አይኖረውም። ስለዚህም ይህን አሳሳቢ ጉዳይ በቅርብ ከሚከታተሉ የስፖርት ቤተሰብ አባላት መካከል የተወሰኑትን አነጋግረናል።

ከሥነጽሑፍ አሐዛቢው ከአቶ አስፋው ዳምጤ ጋር በሃገራችን ሥነጽሑፍና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተናል። የአንጋፋ ደራሲያን እውቀትና ተሞክሮ የሚገበይበትን የአቶ መንግስቱ ለማ ሶሥተኛና የመጨረሻ ክፍልም ይዘናል። የፖለቲካ ባህላችንን ይዞታ በታሪክ አይን የሚያጠይቀው ተከታታይ ጽሑፍም ይቀርባል። ባህልና ሥነጥበብ ለሃገር ልማት ያላቸው ድርሻ ይተነተናል። ሙዚቃ፣ ቱሪዝምና ኢኮኖሚ ያላቸው ግንኙነትና የውጪ ሃገራት ተሞክሮ የሚቀርብበት፣ እኛስ ምን ልንማርበት እንችላለን ብለን የምንጠይቅበት ጽሑፍም ተዘጋጅቷል። ሌሎች አዝናኝና ቁምነገር አዘል ጽሑፎችንም ታገኛላችሁ።

እንደተለመደው ጻፉልን፣ ሃሳብ አስተያየታችሁን አካፍሉን። መልካም ንባብ!

መልካም ንባብ!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top