ጥበብ በታሪክ ገፅ

ከያኒ አባተ መኩሪያ – ስለሱ ከተባለው ያልተባለው

ታላቁ የኪነት ሰው አባተ መኩሪያ የነኦቴሎ፣ የነቴዎድሮስ፣ የአሉላ አባነጋና የሌሎች በርካታ ቴያትሮች አዘጋጅ፣ የሊስትሮ ኦፔራ ፈጣሪና አቀናባሪ፣ወዘተ መሆኑን ብዙዎች ያውቃሉ ብዬ አምናለሁ። በበኩሌ ለዛሬ ላተኩር የፈቀድኩት በአባተ በሰውየውና በአሰራሩ ላይ ሆኖ በእግረመንገድ ፈገግ የሚያደርጉ ትዝታዎችን ለማነሳሳት አስባለሁ።

ጋሼ አባተን ከሩቅም ከቅርብም ሆኜ አይቼዋለሁ። የአብዬ መንግስቱ ለማን “ያላቻጋብቻ” እና ዶ/ር ኃይሉ አርአያ የተረጎሙትን የሶፎክልስ “ኢዲፐስንጉስ” ሲያዘጋጅም በተዋናይነት የመሳተፍ ዕድል አግኝቻለሁ። ከአንድ ዓመት በፊት ስለተለየን ታላቅ ከያኒ የማወጋችሁም በነዚሁ ጊዜያትና ከዚያም ወዲህ በተለያዩ አጋጣሚዎች የታዘብኳቸውን ይሆናል።

ጋሼ አባተን ለመጀመሪያ ጊዜ ያነጋገርኩት ለቀድሞ የዩኒቨርሲቲ መምህሬ ለወይዘሪት ጄን ፕላስቶው (ኋላ ዶክተር) ቀጠሮ ለመያዝ ቢሮው ሄጄ ነው። ይህ ከመሆኑ ከአንድ ሳምንት በፊት ከታላቁ ባለቅኔና ፀሃፌ ተውኔት ፀጋዬ ገ/መድህን ጋር ቀጠሮ ይዤላት እዚያው ባህል አዳራሽ ውስጥ አነጋግረነው ነበር ። ጋሼ አባተን በነካ አፌ እንዳናግርላት የጠየቀችኝም የመጀመሪያውን ውጤት ተመልክታ ይመስለኛል። ምን እንደምትፈልግ ከጠየቀኝና እኔም ካብራራሁለት በኋላ ፈቃደኛነቱን እንደገለፀልኝ አስታውሳለሁ። ከብዙ ጊዜ በኋላ ጄን የፃፈችውን መፅሐፍ ስመለከት ግን “ሊያነጋግረኝ ያልፈቀደ ብቸኛው ሰው” ብላ በስም ጠቅሳዋለች። ስለዚህ ጉዳይ ጋሼ አባተንም ሆነ ጄንን ደግሜ ስላልጠየቅኳቸው ብዙ ከማለት ልቆጠብና ወደዋናው ጉዳያችን ልውሰዳችሁ።

ስለጋሼ አባተ ባሰብኩ ቁጥር ቀድሞ ወደ አእምሮዬ የሚመጣው አንድም ቀን ቢሆን – እደግመዋለሁ፣ አንድም ቀን ቢሆን ሰዎችን – አጠገቡ ቢኖሩም ባይኖሩም – በክፉ ሲያነሳ ሰምቼው አለማወቄ ነው። ይህ ብቻ አይደለም። ከሱ ጋር ሲጠብ ከቴያትር ሲሰፋ ከሥነጥበብ መስክ ውጪ የተጨዋወትኩበትን ቀንም አላስታውስም። ቢቆም ቢቀመጥ፣ ቢያስብ ቢናገር፣ ቢያዝን ቢደሰት ከዚሁ አጥቢያው (ኮምፎርት ዞኑ) አይወጣም። “ቴያትር ከመስራት ሌላ ሕይወት የለኝም” የሚለውስ ለዚሁ አይደል!?

ሌላው የሚገርመኝ የጋሼ አባተ ባህሪይ ነገር ማካበድ አለመውደዱ ነው ። ጠዋት ላይ የተበሳጨበትን ጉዳይ ረፋድ ላይ ሊረሳው ይችላል። አንዳንዴ ደግሞ ሌሎቻችንን እርር ድብን የሚያደርገን ነገር እሱን ብዙም ላይነካው ይችላል ። ወይም በቀላሉ ያልፈዋል። ይህን ጉዳይ በምሳሌ ባስደግፈው ሳይሻል አይቀርም ። አንድ ቀን አብረን ሻይ ቡና እያልን እንዳለን ከቤቱ ስልክ ተደወለለት። ደዋይዋ የቤት ሠራተኛቸው ነበረች። ፍሬ ነገሩን ባልይዘውም ድምጿን ዘለግ አድርጋ ስታናግረው የመደናገጥና የመጣደፍ ነገር እንደነበረባት ያስታውቃል። ጋሼ አባተ ግን ፍፁም በተረጋጋ ስሜት “አንቺ ደሞ ምን ሆነሻል? ቀስ ብለሽ አትነግሪኝም ታዲያ?” አላትና ስልኩን ዘጋው። ከዚያ ፖሊስ እየጠበቀው መሆኑን ነግሮኝ ወደሰፈሩ ሊሄድ ሲነሳ ተከትዬው ሄድኩ። መንገድ ላይ ነው ዝርዝር ታሪኩን የነገረኝ። ለካስ ቤት እንዲጠብቅ የቀጠረው ዘበኛ መኪና ይዞ መጥቶ ቴሌቪዥንና አንዳንድ የቤት ዕቃዎቻቸውን ጭኖ ሲወጣ ተይዞ ኖሯል። ሰፈሩ ስንደርስ ዘበኛው እጁን የፊጥኝ ታስሮ ከፖሊሱ አጠገብ ቆሞ ነበር። ጋሼ አባተ ገና እንዳየው “ምነው አንተ ደህና ሰው አልነበርክም እንዴ?” ብሎት እርፍ። ሌላ ብዙ ነገር አልተናገረም። ፖሊሱ በመገረም አይነት እያየው “እነዚህ ንብረቶች የእርስዎ ናቸው?” አለው በሩን ከፍቶ ወደቆመው መኪና እያመላከተው።

“አዎ ናቸው!” ከዚያ ፊቱን ወደ ሾፌሩ ዞሮ ቀጠለ ጋሼ አባተ “በል እንዳመጣህ ውሰድና ቤት አስገባቸው።”
“ሰውየውን አይፈልጉትም?” ጠየቀ ፖሊሱ።
“በቃ ከእንግዲህማ አልፈልገውም።”
“ማለቴ … ክስ አይመሰርቱበትም ወይ?”
“አይ እኔ ምን እከሰዋለሁ … ህሊናው ይክሰሰው።”
ጋሼ አባተ በሥራ ላይ፣

ቴያትር ሲያዘጋጅ መድረክ ላይ የሚለማመዱት ተዋንያን አጨዋወት ደስ ካሰኘው ወንበሩ ላይ እንደተቀመጠ ትከሻው ሽቅብ እስኪነጥር ድረስ በሳቅ ይገነፍላል። ሲጃራውን ደጋግሞ እየሳበ ይፍለቀለቃል። ካልጣመው ደግሞ ፊቱን ቅጭም ክስክስ ያደርግና ትንሽ ይታገሳል። ከዚያ ተዋናዩን ወይንም ተዋናይቷን አስቁሞ በለዘበ አንደበት ይመራል፣ ይመክራል። ለውጥ ካላየ ግን “ምን ሆኗል ይሄ ደግሞ?! አሁን መስራትሽ ነው እንዴ? ስሜትህን አሳየኝ እንጂ”፣ “ቃላቱን በደንብ ተናገሪያቸው እንጂ” ወይም “ወስንና ተነስ! ተራህ ስለደረሰ ብቻ ተነስተሀ ትሮጣለህ እንዴ? ምን ሆነሃል?! እምልህ ይገባሃል?” እያለ ይቀጥላል።

በስተመጨረሻ ያነሳኋትን ነጥብ ጥቂት ማብራራት ሳያስፈልግ አይቀርም ። አንድን ተዋናይ ከወንበሩ ላይ የሚያስነሳው በቂ ምክንያት ያስፈልጋል ነው። አንዱ ከሌላ ወገን የተሰነዘረበት ዛቻ ወይም ንቀት ፈንቅሎት ለትንቅንቅ ይነሳል። በናፍቆት የሚጠብቃትን ፍቅረኛ ለመቀበል ፊቱ ሁሉ ጥርስ ሆኖ በደስታ ስሜት የሚነሳ አለ። እንቅልፍ ተጫጭኖት እየተንጠራራና እያዛጋ ወደመኝታው ሊሄድ የሚነሳም ይኖራል ። ስለዚህ እያንዳንዱ የተዋንያን እንቅስቃሴ የታሰበበት፣ በበቂ ምክንያት የሚደገፍና በአእምሮና በሰራ አካላት ጥምረት (Mind and body cohesion) የሚመራ መሆን አለበት ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ አንድ ትዝታ አለኝ። ጋሼ አባተ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የቴያትርና ባህል አዳራሽ ዋና ሥራ አስኪያጅ ነበር። ታዲያ በተመስጦ ላይ ሆኖ ቴያትር ሲያዘጋጅ ከቢሮው የሚመጣለትን ወረቀት አልፎ አልፎ በግማሽ ቀልብ ሌላ ጊዜ በደንብ ሳያነበው ይፈርመዋል። “ኧረ ይኼ ፊርማ” እንላለን አንዳንዴ ከበስተኋላ ሆነን። እሱም አልፎ አልፎ ሲብስበት “ምንድነው ትንሽም ፋታ አትሰጡኝም እንዴ? ምን ሆናችኋል?” ይላቸዋል። አንዳንዴ ደግሞ የሻይ እረፍት ይሰጠንና ቢሮው ደረስ ብሎ ይመጣል። ከእንደነዚህ አይነት አጋጣሚዎች ባንዱ ፊት ለፊቴ ከነበሩት ተዋንያን አንዱ አምቦ ውሃ ሲጠጣ “ወስንና ጠጣ! ዝም ብለህ አንስተህ ትጨልጠዋለህ እንዴ?!” እላለሁ በጋሼ አባተ አይነት ቅላፄ። ለካ እሱ ሥራውን ጨርሶ ከበስተኋላዬ እየመጣ ነበር። የጓደኞቼን ፊት አይቼ ወደኋላ ስዞር አጠገቤ ደርሷል።

“ምን ሆነሃል አንተ ደግሞ! ዋዘኛ ኖረሃል እንዴ?” አለኝና ወደ ጉዳዩ ገባ። ያላቻ ጋብቻን ሲያዘጋጅ ዋናው ገፀባህሪ (ከውጭ ተምሮ የመጣው የባለፀጋዋ የወይዘሮ አልጋነሽ ዱብዳ ልጅ) ባህሩ አልጋው ላይ እንዳለ የቤት ሠራተኛው (ግን ደግሞ ሊያገባት የሚፈልጋት ወዳጁ) በለጤ አብሽ እየመታች ታዋራዋለች። ጋሼ አባተ ከሁለት የተለያዩ “መደቦች” የመጡት የነዚህ ወጣቶች ንፁህ ስሜት የሚገለፅበትን ይህን ትዕይንት ጎላ አድርጎ ለማሳየት ይፈልጋል። ስለዚህም በለጤን ሆና የምትጫወተውን ተዋናይት -ጀማነሽ ሰለሞን- “እስኪ ‘ፍለርት’ አድርጊው” (አሽኮርምሚው) ይላታል። ትሞክራለች፣ አላረካውም። እናም “እስኪ ትንሽ ይስራሽ” አላት። አሁንም ሞከረች። ሆኖም ለጋሼ አባተ በቂ አልነበረም። ከዚያ ቀጥሎ የተናገረውን ስትሰማ ግን ሮጣ ከመድረክ ጀርባ ገባች።

በዚሁ ቴያትር ታሪክ ውስጥ ባህሩ የሚያሳድገው ቦጋለ የተባለ ትንሽ ልጅ አለ። እናም ያን ገፀባህሪ እንዲጫወትለት የመደበው በመድረክ ያሳደገውንና (በቴዎድሮስ ቴያትር ምኒልክን የወከለለትን) የመንፈስ ልጁን ሳምሶን ወርቁን ነበር። ሳምሶን በመድረክ ሲለማመድ ድምፁን እንደ ህፃን ልጅ አድርጎ “ካሼ ባህሉ! እማማ ትልኳ እንዳሉ…” እያለ ነበር። ጋሼ አባተ የሚፈልገው ደግሞ የሳምሶንና የገፀባህሪው ዕድሜ ተቀራራቢ ስለሆነ በራሱ የተፈጥሮ (Normal) ድምፅ እንዲተውንለት ስለነበር “ምን ሆኗል እሱ?! ልጅ ሆኖ እንደልጅ ሊጫወት ይፈልጋል እንዴ?!” አለና ፈገግ አስደረገን።

የአዲስ አበባ ቴያትርና ባህል አዳራሽ የሙያ ታላቆቼ ካጫወቱኝ ትዝ የሚለኝ ደግሞ በአንድ ወቅት አንድ ተዋናይ ከመድረክ ልምምድ ይቀራል። ጋሼ አባተ ፈልጎሲያጣው“የት ሄደ እሱ ደግሞ?” ይላል። አባቱ ይሁኑ አጎቱ እንደሞቱበት ሲነገረው ታዲያ፣ “ምን ሆነዋል እሳቸው ደግሞ፣ በዛሬው ዕለት ይሞታሉ እንዴ!” ብሏቸው እርፍ።

ኢዲፐስ ንጉሥን ሲያዘጋጅ ‘ጋሽ ተስፍሽ’ የሚላቸው አባባ ተስፋዬ ሳህሉ የአይነስውሩን ተረሲያስ ገፀባህሪ ይጫወቱ ነበር። እናም መቀለድና መጫወት የሚወዱት አባባ ተስፋዬ በተገናኘን ቁጥር የትናንቱን የመድረክ ታሪክ እያዋዙ ይነግሩናል። በልምምድ ወቅት ታዲያ አይናቸውን ጨፍነውና በሚጫወቱት ባህሪፈጽሞ እንደተመሰጡ ሆነው ወደ መድረኩ ጫፍ ሲንደረደሩ ጋሼ አባተ በሰቀቀን “ኧረ ጋሽ ተስፍሽ፣ ተጠንቅቀህ” እያለ ይጮሃል። እሳቸው ወደኛ ዞረው ይጠቅሱናል። እንደገና ይደግሙታል። እንደገናምጋሼ አባተን ያስጮኹታል።

ጋሼ አባተ በሥራው ሲመሰጥ የለኮሰውን ሲጃራ ሳይቀር ይረሳዋል። እናም ብዙውን ጊዜ ሲጃራው እጁ ላይ ነበር የሚያልቀው። ከዚያ ሌላ ያወጣና ባለቀው ሲጃራ ለኩሶ ጠረጴዛው ላይ ያስቀምጠዋል። እንደገናም ይረሳዋል። አልፎ አልፎ ከንፈሩ ሲደርቅበት እንደጀበርና ከሚታጠቀው ቦርሳው ውስጥ ቫዝሊን ያወጣና በዚያ ያወዛዋል። እጁ ላይ የቀረውን ደግሞ ፀጉሩ ላይ ይጠርገዋል። አስቦበት አይመስለኝም። አንዴ ከያኒ ዓለሙ ገብረአብ ይህችን ሂደት በጨዋታ መልክ አቀረባትና ሁላችንንም አሳቀን። ጋሼ አባተን ጭምር።

እኔ እስከማውቀው ድረስ ጋሼ አባተ ቴያትር ሲያዘጋጅ መድረክ ላይ ለመውጣት አይጣደፍም። ይልቁኑ ስለሚያዘጋጄው ቴያትርና ስለሚከተለው መንገድ ተዋንያኑ በቅድሚያ እንዲረዱለት ይፈልጋል። ስለዚህም ሃሳቡን ያካፍላቸዋል። በዚህ ብቻ ግን አያቆምም። እሱ ከሚፈልገው የዝግጅት ስልት ጋር ይሄዳል ብሎ ያሰበውን ሥራ ተዋንያኑ እንዲመለከቱትና እንዲወያዩበትም ያደርጋል። “ያላቻ ጋብቻ”ን ሲያዘጋጅ የአሜሪካዊውን ፀሐፌ ተውኔት የአርተር ሚለርን “የአሻሻጩ ሞት” (Death of a Salesman)፣ በ”ኢዲፐስ ንጉሥ” ጊዜ ደግሞ ታዋቂው እንግሊዛዊ የቴያትር ባለሙያ ፒተር ብሩክ ያዘጋጄውን “ዘማህበራታ” (The Mahabharata) እንድንመለከት አድርጎናል። የመጀመሪያው ቤተሰባዊ ህይወትን የሚያሳይ ሲሆን ሁለተኛው በህንድ ጥንታዊ (የሶስት ሺህ ዓመት) ታሪክ ላይ የተመሠረተና ሕይወትንናየስነምግባር እሴቶችንበጥልቀት የሚዳስስ ነው።

“ኢዲፐስ ንጉሥ” በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከራስ መኮንን አዳራሽ ፊት ለፊት በሚገኝ “መዋኛ ሥፍራ” (Swimming pool) ተብሎ የሚታወቅ – ተማሪዎች ደግሞ “መሳሳሚያ ሥፍራ” (Kissing pool) ብለው የሚጠሩት – መፈናሻ ውስጥ ተመድርኮ ነበር። በዚያ ምሽት ያሬዳዊው ዜማ የነገሰበት ህብረ ዝማሬ (Choire) በጧፍና በችቦ ብርሃን ደምቆ ሲቀርብ፣ ተዋንያኑም ከየማዕዘኑ ብቅ እያሉ ሲጫወቱ ሁለቱን ቀደምት የባህልና የታሪክ ሃገራት – ግሪክንና ኢትዮጵያን – በጉልህ መመልከት ተችሏል። የአዘጋጁ ህልምም ምኞትም ይኸው ነበር። ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ አሳምረው የተረጎሙትን ተውኔት ኢትዮጵያዊ ለዛና ጣዕም ሰጥቶ በመድረክ ላይ መከሰት። ከዚያ በኋላ ቴያትሩ ለረጅም ጊዜ በብሔራዊ ቴያትር መድረክ ቀርቧል።

የመጨረሻ ትዝታዬ ወደ ቃሊቲው የገነት መናፈሻ ይወስደናል። በ”ያላቻ ጋብቻ” ቴያትር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተሳተፉ ባለሙያዎች የተገኙበት አንድ የመዝናኛ ምሽት (Cast party) ተዘጋጅቶ ነበር። አንዱን የገነት መናፈሻ ጎጆ ብቻችንን ተቆጣጥረነዋል። ራት ከበላንና አንድ ሁለት ካልን በኋላ አብሮን የተጓዘው የመሰንቆ ባለሙያ መጫወት ጀመረና ምሽታችንን ያስውበው ገባ። ብዙም ሳይቆይ ጋሼ አባተ አንድ ሃሳብ አቀረበ። “አሁን ደግሞ ሁላችንም በየተራ እየተነሳን የመረጥነውን ዘፈን እንዘፍናለን” አለን።

አንዳንዶቻችንን ድንጋጤ ዋጠን። ከፊሎቻችን ደግሞ የምናንጎራጉረውን ዜማ ፍለጋ በሃሳብ መኳተን ያዝን። በዚህ ጊዜ ተነሳና “እኔ እጀምርላችኋለሁ” ብሎ አረጋጋን። “የማቀርብላችሁ “ሺልንግዬን” ነው። “ሺልንግዬ ሺልንጌ” ስላችሁ “ሺልንግዬ ሺልንጌ” እያላችሁ ትቀበሉኛላችሁ” አለና ዜማውን እንዲሁም የምንወጣበትንና የምንገባበትን ቦታ አስረዳን። ሲዘፍን ታዲያ ትዊስት በሚባለው ስልት እየደነሰም ጭምር ነው።

ሺልንግዬ ሺልንጌ – ጎርነን ባለ ድምፅ እሱ
ሺልንግዬ ሺልንጌ – በህብረ ድምፅ
እኛ
ሺልንግዬ ሺልንጌ – እሱ
ሺልንግዬ ሺልንጌ – እኛ
ዱዲዋ ለፓስቲ፣ ስሙኒ ለሽሮ- እሱ
ካራዳ ልጅ ጋራ፣ መብላት ነው ተባብሮ
በሳቅ በጨዋታ፣ በደስታ ሰክሮ
መገን ያራዳ ልጅ፣ እነድንጋይ ኳሱ
ከምኔው ተጩኾ፣ ከምኔው ደረሱ …

ጋሼ አባተ ከጨረሰ በኋላ ሁላችንም እንደየአቅማችን መሞካከራችን አልቀረም። ሆኖም ምንጊዜም የማይረሳኝ የፍሥሃ በላይ እንጉርጉሮ ነው። ስለእሱ ልንገራችሁና ላብቃ። ፍሥሃ ፀሐፌተውኔትም፣ አዘጋጅም፣ ተዋናይም፣ ሙዚቀኛም ነበር። በአጭሩ የባህል ጎተራ ሊባል የሚገባው ነው።

ዘመኑ የደርግ መንግስት እየተዳከመ የመጣበትና ከሶስትና ከአራት በላይ ሆኖ (ሰብሰብ ብሎ) መታየት የተከለከለበት፣ በሻምበል ለገሰ አስፋው የሚመራው የትግራይ ልዩ ራስ ገዝ አስተዳደር መቀሌን ለቆ የወጣበትም አካባቢ ይመስለኛል። ታዲያ ፍሥሃ “ጉማዬ” የተሰኘ እንጉርጉሮ ለማቅረብ ፈለገና እሱ “ጉማዬ ጉማ” ሲል እኛ “ሃይ ጉማ” እንድንል ጠየቀን።መግቢያውን ስንጨርስ እሱ፡-

ዝናር ሙሉ ጥይት፣ ክላሺን ይዘህ
ትሸሻለህ አሉ፣ ክፉ አመል አለህ።
ከሰላሳ በሬ፣ ከሰላሳ ላም
ይሻላል ምንሺር፣ ሰባራም ቢሆን፡

ሲል አንዳንዶቻችን በፍርሃት ሞቅታችን ጥሎን ሄደ። ነገርዬው በህዝባዊ ግጥማችን ውስጥ ያለም ቢሆን ግጥምጥሞሹን ነበር የፈራነው። ፍሥሃ ግን አልበቃውም። እንደውም “የወሎ ለቅሶ ዘፈን ማለት ስለሆነ አለቅሳለሁ” ብሎን እርፍ አለ። አይሆንም ብለው ከተከራከሩት አንዱ እኔ ነበርኩ። ፍሥሃ ቅር ስላለው ከቃሊቲ አዲስ አበባ የምሽት የእግር ጉዞውን ጀምሮ ነበር። ደግነቱ እየተጠናቀቅን ስለነበር ብዙም ሳይርቅ ደረስንበት።

ጋሼ አባተ እጅግ የሚያስደንቅ ሰብዕና ያለው ባለሙያ ነበር። በቅርቡ “ዝክረ አባተ – ፩” የተሰኘ ሕይወትና ሥራዎቹን የሚዘክር ልዩ ዝግጅት በብሔራዊ ቴያትር ተሰናድቶ ነበር። በዚሁ ዕለት ከሙያ ልጆቹ የሰማኋቸው አዳዲስ ነገሮችና የተመለከትኳቸው ሥራዎቹም ይህንኑ ሰብዕናውንና የሙያ ታላቅነቱን ነው አጉልቶ ያሳየኝ።

 

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top