ታዛ ስፖርት

እውነት የሚያጓጓ ኖሮን ነው ደጋፊዎች “ኳስ ጨዋታ” የሚጋጩት!?

በሌለ ኳስ፣ መቆራቆስ!

ስ ፖርት ለጤንነት፣ ለፍቅር፣ ለአንድነት፣ ለወንድማማችነት፣ ለብልጽግና፣ ለአካል ጥንካሬ … እግር ኳስ ሰላማዊ ስፖርት ነው። ለዚህ ነው አንድ ተጫዋች ከሜዳ ውጪ (በካምፕ) በክለቡ መመሪያና ሥነምግባር መሠረት የሚገራው። ሜዳ ውስጥ ከገባ በኋላ ደግሞ እያንዳንዱ እንቅስቃሴው በፊፋ ሕግ እና በስፖርታዊ ጨዋነት መርህ እንዲሆን የሚጠበቀው።

ዳኛው ፊሽካቸውን ፒርርር አድርገው እንደነፉ፣ ኳስ ጨዋታው በአንደኛው ቡድን አማካይነት መሃል ሜዳ ላይ በቅብብል ይጀምራል። ከዚያ በኋላ ኳሷን የያዘም ሆነ፣ ኳሷን ለመቀማት የሚያባርር የተቃራኒ ቡድን ተጫዋች የጨዋታ ክህሎቱን፣ ብቃቱን እና እውቀቱን እስከ ፈለገው ጥግ ድረስ የመጠቀም ነፃነት ቢኖረውም፣ በፊፋ ሕግና ሥነምግባር የመመራት ግዴታ ግን አለበት።

አለበዚያ የቃል ማስጠንቀቂያ፣ ቢጫ ካርድ፣ ቀይ ካርድና ከፍ ሲልም በፊፋ ዲስፕሊን ኮሚቴ ከፍተኛ የቅጣት እርምጃ በተጫዋቹ፣ በቡድኑ እና በሀገሩም ላይ ሊወሰድ ይችላል። ከላይ የተጠቀሱትን የሜዳ ላይ የዳኛ ውሳኔዎች ተከትሎ ከዕለቱ የጨዋታ ሜዳ መባረር፣ ለተከታታይ ሁለትና ሶሥት ጨዋታዎች መታገድ፣ ለወራት ከዓለም አቀፍ እግር ኳስ መገለልና ከዚህም የከፋ ውሳኔ በሀገር የእግር ኳስ እንቅስቃሴ ላይ ሳይቀር ሊወሰን ይችላል።

የእግር ኳስ ድጋፍም እንዲሁ ከስፖርቱ ሠላማዊነት፣ ሕግ እና ሥነምግባር ተገንጥሎ የወጣ ልቅ ዓውድ አይደለም። ቡድንን በጭብጨባ፣ በማበረታቻ ቃላት፣ በዝማሬ፣ በጭፈራ፣ በሆታና በምልክት መደገፍ ትናንት የነበረ፤ ዛሬም ያለና፤ ወደፊትም የሚኖር የተፈቀደ ሠላማዊና አስደሳች የድጋፍ ሥልት ነው። ለእግር ኳስ ጨዋታም ውበቱ ይሄ ዓይነት የድጋፍ ሥልቱ ነው።

ከዚህ ማዕቀፍ የወጣ እንደሆነ፣ ለጤንነት የተፈጠረውን ስፖርት ለህመም ያውለዋል። ለፍቅር የሚሆነውን ስፖርት ለጸብ፣ ለአንድነት የሚሆነውን ዓላማ ለልዩነት፣ የወንድማማችነቱን መድረክ ወደ ጠላትነት መንፈስ መቀየር ነው። ለብልጽግና የሚውለውን ህዝባዊ ሃብት ለውድመት ማዋል ነው። ለአካል ጥንካሬ መሆኑ ቀርቶ ለአካል ጉዳት የሚዳርግ፣ ከፍ ሲልም ህይወትን የሚቀጥፍ የጨረባ ተዝካር ይሆናል። ከዚህ ማን ይጠቀማል? ማንም! ሁሉም ሰው (ቡድን) ተጎጂ ነው የሚሆነው።

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ደጋፊዎች መካከል በሌለ ወይም እዚህ ግባ በማይባል ኳስ ጨዋታ ሰበብ የሚፈጠሩ ግጭቶችና ሁከቶችን ተመልክቶ እንዳላየ መሆን፣ በሚቀጥለው ተረክ ላይ ያለውን እውነታ ነው የሚደግመው። ነገሩ እንዲህ ነው፡-

በሁለት መንደር መካከል ባለ ቅያስ መንገድ የሚያዘግሙ ሽማግሌ፣ ሁለት ውሾች በአጥንት ሲጣሉ ይመለከቱና ‹‹ልጆች፣ እባካችሁ! እነዚህን ውሾች ቶሎ ገላግሏቸው፤ ዳፋቸው ለሌላ ይተርፋል።›› አሉ። የውሾቹን ጸብ እንደ ትርዒት የሚመለከቱት ልጆች ግን ‹‹አባት የውሾች ጸብ እንደሁ የተለመደ ነው። ሲደክማቸው ያቆማሉ!›› አሏቸው። ሆኖም፣ የሁለቱ ውሾች ጸብ በፍጥነት ወደ ሁለት መንደር ውሾች ጸብ እየተቀየረ ነበር። አፍታም ሳይቆይ ውሻው እንደተጠቃበት የሰማ ወጣት የሌላኛውን ውሻ እግር በድንጋይ ቀለጠመው።

ከጥቂት ቆይታ በኋላ፣ ውሻው ሲያነክስ የተመለከተው አሳዳጊ ደግሞ ተንደርድሮ መጥቶ ውሻውን የጎዳበትን ወጣት በቡጢ አለው። ሁለቱ ወጣቶች እርስ በእርስ ሲቧቀሱ የተመለከቱት ሽማግሌም ‹‹ኧረ እናንት ጎልማሶች! እነዚህን ሁለት ወጣቶች ቶሎ ገላግሉ፤ የእነርሱ ጸብ ዳፋ ደግሞ ቤተሰብን ብሎም መንደሩን እንዳያውክ›› በማለት አስጠንቅቀው ጉዟቸውን ቀጠሉ። የሰማቸው ግን አልነበረም። ጎልማሶቹም እንደ ልጆቹ አፌዙባቸውና ጸቡን እንደ ትርዒት ይመለከቱ ጀመር።

አመሻሹ ላይ በዛው በኩል ወደ ቤታቸው የሚመለሱት ሽማግሌ የመንደሩ ውሎ እንዴት ነበር? ብለው ቢጠይቁ በሁለት ውሾች የጀመረው ጸብ፣ ወደ ሁለት ወጣቶች፣ ከዚያም ወደ ወላጅ እናቶቻው፣ ከዚያም ወደ አባቶቻቸው ከዚያም ወደ ጉረቤቶቻቸውና በመጨረሻም የሁለት መንደር ጸብ ሆኖ እንዳረፈውና ለሽምግልና እንደሚፈለጉ ነገሯቸው። ‹‹ታዲያ እኮ ጸቡን ከሁለት ውሾች ሳይዘል፣ በኋላም ከሁለቱ ወጣቶች ሳይሻገር አስቁሙት ብለንም አልነበር፤ ሰሚ አጣን እንጂ!›› አሉ ይባላል።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ደጋፊዎች ባህሪይ ወደ ብጥብጥ፣ ሁከትና ግጭት እያመራ ያለው በእንዲህ ዓይነት የሁለት ግለሰቦች ጸብ መነሻነት ነው። አስረጅ ማስቀመጥ ካስፈለገም፡- አዲስ አበባ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ እና ኢትዮጵያ ቡና ሲጫወቱ ግጭትና ሁከትን ማስተናገድ ተለምዷዊ እየሆነ ነው። በቅርቡ በሁለቱ ቡድኖች ደጋፊዎች የተከሰተው ግጭት የመጀመሪያው አርባ አምስት ደቂቃ ጨዋታ ተጠናቆ በእረፍት ሰዓት ላይ ነው። ከኳስ ጨዋታ እንቅስቃሴ እና ከድጋፍ የስሜት ጡዘት ውጪ ማለት ነው።

‹‹አየህ እኔ የተረፍኩት በእረፍት ሰዓት ላይ ብስኩት ነገር ለመቀማመስ ወደ ታች ወረድ ስላልኩ ነው። የሁለት ግለሰቦች ግጭት ነው በፍጥነት የሁለት ቡድን ደጋፊዎች ግጭት የሆነው። ጩኸትና ሁካታ እንደሰማሁ ዘወር ብል ጸቡ በፍጥነት እየተዛመተ የደጋፊዎች ስብስብ ለሁለት ተከፍሎ ተመለከትኩ።

ሽሽት፣ ማባረር፣ መመታታት፣ መወራወር፣ ቦክስ፣ እርግጫ፤ በቦታው ላይ ግማሹ ሰው ተጎድቷል። ግማሹ ሰው ዘሎ ወጥቷል። የወደቀ፣ የተሰበረ፣ እግሩን ወለም ያለው፣ የተፈነከተ፣ የደማ፣ ያበጠ፣ ልብሱ የተቀደደበት ወዘተ. ሰው ታያለህ።

እውነት ለመናገር የሁለቱ ልጆች ጸብ በምን ምክንያት እንደተጀመረ አላውቅም። ግን ከሰላሳ በላይ ሰው መጎዳቱን በቦታው ሆኜ ተመልክቻለሁ። የሚያሳዝነው ከተጎጂዎች ውስጥ ሴቶችም ነበሩ፣ ህፃናቶችም አሉ፣ ትልልቅ ሰዎችንም አይቻለሁ›› ይላል በእለቱ ኳስ ጨዋታ ለመመልከት የገባውና የሁለቱም ቡድኖች ደጋፊ ያልሆነው ዳዊት ተካልኝ።

ክልል ላይ ደግሞ የደጋፊዎች ግጭት ወዲያው ነው መልኩን የሚቀይረው። መቀሌ ላይ፣ መቀሌ እና ባህርዳር ሲጫወቱ ከፍተኛ የደጋፊዎች ጸብ ነበር። በኋላ የመልስ ጨዋታ በገለልተኛ ሜዳ ይደረግ በሚል አዲስ አበባ ላይ ተካሄደ፤ ቀጣዩ ዳፋ ተፈርቶ። ጎንደር ላይ፣ ጎንደር ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡና ሲጫወቱ እንዲሁ ጸብና ሁከት ነበር። አዳማ ላይ፣ አዳማና ቡና ሲጫወቱ የደጋፊዎች ጸብ ነበር። አዲስ አበባ ላይ ወላይታ ዲቻ እና ደደቢት ሲጫወቱ ውጥረቱ ከፍተኛ ነበር። ትግራይ ላይ መቀሌ ከተማ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ሲጫወቱ ከአሁን አሁን ምን ተፈጠረ በሚል ውጥረትና ጭንቀት ተሞልቶ ነው። ጨዋታው ሰላማዊ ኳስ ሳይሆን ሌላ ውጥረት ነው የሚመስለው። ለምን?

የስፖርት ጋዜጠኛው ዮሴፍ ከፈለኝ በዚህ ጉዳይ ላይ የዓይን እማኝ በመሆኑ ብዙ የሚለው አለው። ‹‹በእርግጥ ብዙ ጊዜ የሚነሳው ረብሻ ምክንያቱ እግር ኳስ ነው ለማለት ይከብደኛል፤ ብዙው ነገር ከስፖርታዊ ጉዳይ ወጣ ያለ ነው›› ይላል።

ለምሳሌ መቀሌና ወልዋሎ አዲግራት፣ ትግራይ ክልልን ከረጅም ጊዜ በኋላ የወከሉ ሁለት ክለቦች ናቸው። ሆኖም፣ በመካከላቸው እኔ ነኝ የክልሉ ዋና ወኪል፣ እኔ ነኝ ትግራይን የበለጠ የምወክለው የሚል የተቀናቃኝነትና የተነሳሽነት መንፈስ የፈጠረባቸው የፀብ ዝንባሌ ያለ ይመስላል። እንግዲህ የኛ አገር እግር ኳስ የተቀናቃኝነት መንፈስ ከተላበሰ ሰንበትበት ብሏል። ከእግር ኳስ የወጣ ግን ደግሞ ሌላ የፀብ መንፈስ ያለው ነው። በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የለንደን ወኪል ማነው ሲባል አርሴናልም፣ ቸልሲም፣ ቶተንሃምም ቀድመው እኔ ነኝ የምወክለው ይላሉ።

ነገር ግን እነርሱ በአደገ ኳስ ጨዋታና በሰለጠነ መንገድ ነው የሚፎካከሩት። በዚያ ላይ ሕጉ ጥብቅ ነው፣ አያፈናፍንም። እዚህ ግን የሞተ ኳስ ላይ ነው ንትርኩና ፀቡ። እርግጥ የተጫዋቾች ደሞዝ እጅግ ልቋል፤ ሆኖም የእኛን ሀገር ኳስ በገበያ ዋጋ ከወሰድከው አንድ ኪሎ ስኳር በአንድ መቶ ሺ ብር እንደመሸጥ ያለ ነው። የደጋፊው የኳስ ፍቅር ማየል፣ ለክለቡ ያለው ፍቅር መላቅ፣ ካለው የወረደ የእግር ኳስ ጨዋታ ጋር አይመጣጠንም።

ደጋፊው ስሜቱ ከጨዋታው በላይ አይሎና ገንፍሎ ይወጣል። ሆኖም፣ የክለቡ ጥሩ አለመሆን ደግሞ ያናድደዋል፤ በአንፃሩ ከተቃራኒው ቡድን ደጋፊ የሚሰነዘረው ትችት ያበሳጩታል። ደጋፊው ባላደገው እግር ኳሱና ቡድኑ ያደጉትን አገራት የድጋፍ ስሜት ይዞ ወደ ስታድዮም መጥቷል። እናም በቀላሉ ወደ ግጭት ይገባል። አንዳንድ ጊዜ ከኳስ ጋር የተያያዘ የሚመስል ግን ያልሆነ ግጭት ነው ያለው።

አሁን የቡና እና የጊዮርጊስ ደጋፊዎች ጋ ስትመጣ፣ ጊዮርጊስን መደገፍ ቡናን መስደብ፤ ቡናን መደገፍ ደግሞ ጊዮርጊስን መስደብ ሆኗል። እዚህ ጋ ያሉ ደጋፊዎች ክለባቸውን ብቻ ደግፈው ሲያሸንፍ ከመደሰት ይልቅ፣ ሌላኛው ክለብ ሲሸነፍ መደሰትን ይመርጣሉ። እነዚህ ከኳስ የወጡ ስሜቶች ናቸው። ባላደገ ኳስ ላይ ከውጪ የገባ የደጋፊዎች የተቀናቃኝነት መንፈስ ይመስለኛል።

ከአንድ ዓመት በፊት ቡና ከሀዋሳ ጋር ሲጫወት ረብሻ ነበር። ደጋፊው ለመጋጨት ምንም ምክንያት አልነበረውም። ግን በውስጡ የታመቀ ከኳስ ጨዋታ ያጣው እርካታ፣ በአኅጉር አቀፍና ዓለማቀፍ ጨዋታዎች ላይ በብሄራዊ ቡድን አለመወከሉ፣ በፌዴሬሽን ላይ ያለው ንዴት፣ በዳኞች ላይ ያለው የብቃት ማነስ፣ በክለቦች አመራሮች ላይ ያለው ንዴት፣ በተጫዋቾች ብቃት መውረድ የተነሳ የሚሰማው ብሽቀት፣ እንዲሁም የስፖርት ጋዜጠኞችና ሚዲያዎች ወገናዊ ዘገባዎች ተዳምረው ደጋፊውን ቁጡና ግልፍተኛ አድርገውት ለግጭት ሰበብ ፈላጊ ሆኗል።

ጸቡ ሁሉ የሁለት ክለብ ደጋፊዎች የተቀናቃኝነት ስሜት ነው ብለህ እንዳትደመድም ደግሞ የአንድ ክለብ ደጋፊዎች በሞሉበት ስታዲየም ውስጥም ረብሻና ግጭቶች ተስተናግደዋል።

አምና አንድ ውጥረት ፈጥሮ የነበረው በደደቢትና በወላይታ ዲቻ ክለቦች መካከል ተካሄደ የተባለው የመለቃቀቅ አሻጥር (ሆን ተብሎ የሌላውን ውጤት ለማዛባት) ነው። በማስረጃ ባይረጋገጥም የሌሎች ክለቦች ደጋፊዎች እንደዛ ተደርጓል ብለው አስበዋል።

ጨዋታው የሊጉ የመጨረሻ ጨዋታ ነበር። ዲቻ በሊጉ ውስጥ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረት የግድ ደደቢትን ማሸነፍ ነበረበት፤ ላለመውረድ። የደደቢቱ ኮከብ ጎል አግቢ ጌታነህ ከበደ ደግሞ ለ16 ዓመታት የተያዘውን የኮከብ ጎል አግቢነት ሪከርድ ለመስበር የግድ ሁለት ተጨማሪ ጎል ማግባት ያስፈልገው ነበር። ክለቡ ግን አሸነፈም አላሸነፈም በውጤቱ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ አልነበረውም።

እናም ጨዋታው ሲያልቅ የነበረው ውጤት ጌታነህም ሁለቱን ጎል አገባ፤ ዲቻም አራት ለሁለት ደደቢትን አሸነፈ። ሌሎች ክለቦችና ደጋፊዎች የሚሉት ደደቢት ዓመቱን ሙሉ አራት ጎል ገብቶበት አያውቅም። ከቡናም ሆነ ከጊዮርጊስ ጋር ሲጫወት በዚህ ውጤት አልተሸነፈም፤ እኩል ተፎካካሪ ነው። ዲቻም ዓመቱን ሙሉ አንዴም አራት ጎል አግብቶ አሸንፎ አያውቅም። ደደቢትን የሚያሸንፍበት ወቅታዊ ብቃትም አልነበረውም ይላሉ። እናም ነገሩ ጠርጥር ከገንፎ መሐል አይጠፋም ስንጥር እንደሚባለው ነው። ስለዚህም ደጋፊው ጨዋታው በአሻጥር የተካሄደ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሶ ነበር። በዚህም የተነሳ ውጥረት ተፈጠረ።

‹‹እኔም ከጨዋታው በፊት ሰምቼው የነበረ ወሬ ነበር›› ይላል የስፖርት ጋዜጠኛው ዮሴፍ ከፈለኝ። ‹‹እንደወሬው፣ ጨዋታው ሶሥት ለሁለት በዲቻ አሸናፊነት ያልቃል፤ ነገር ግን ጌታነህ ከበደ ሁለት ጎል ያገባል። በመጨረሻው ውጤት ግን ዲቻ አንድ ጎል ጨምሮ አራት ለሁለት አሸነፈ፤ ጌታነህም እንደተባለው ሁለት ጎል አገባ።

በባህርዳር እና በመቀሌ መካከል የተፈጠረው ግጭት፣ ምንም እንኳ በእግር ኳስ ሜዳ የተከናወነ ቢሆንም ቅሉ፣ ከእግር ኳስ ጋር የተያያዘ ነው ብዬ አላስብም፤ ከኳስ ማዕቀፍ የወጣ ነው ይላል ዮሴፍ።

የኢትዮጵያ ቡና እና የአዳማ ከነማ ደጋፊዎች ግጭት ደግሞ ከጀርባው ምንም የሌለበት በጥቂት ደጋፊዎች መካከል የተፈጠረ የቃላትና በድጋፍ ብሽሽቅ የተከሰተ ግጭትና ጸብ ነው። እዚህ አዲስ አበባ የመልስ ጨዋታ ሲደረግ የመልስ ግጭቱም ቀጥሎ ተመልክተነዋል በማለት ቂም መያያዝ መኖሩን ይጠቁመናል።

የክለብ አመራሮችን በተመለከተ የትኛውም ክለብ አመራር ስለተጋጣሚው ክለብ ጥሩ አውርቶ አያውቅም። ተጫዋቾቻቸው ጥፋት ሲሰሩ እንኳ፣ እነርሱም ሆነ አሰልጣኞቻቸው እውነታውን ከመቀበል ይልቅ፣ መሸፋፈንና ችግሮችን ወደ ሌሎች አካላት ላይ ማላከክ ነው የሚቀናቸው። በውጪ አገር ተጫዋቾቻቸው ሲያጠፉ፣ አሰልጣኞቻቸውና የክለቦቹ አመራሮች ኃላፊነት ወስደው ይቅርታ ሲጠይቁና ይሄ የክለቡ አቋም አይደለም እናስተካክላለን ብለው ተጫዋቹን ሲቀጡ ነው የሚታየው። ገፅታ እንዳይበላሽ።

የሀገራችን ክለቦች አመራሮችና አሰልጣኞች የተጫዋቾቻቸውን ስህተት ወደ ሌላ አካል በማላከካቸው፤ ተጫዋቾቹም ተበረታተው ሜዳ ውስጥ የሚያሳዩት ተንኳሽ ምስልና ንግግር ለሁከት መነሻ ይሆናል። ደጋፊውም የሚቃኘው በክለቡ አመራርና አሰልጣኝ ንግግርና ስሜት ስለሆነ በቀላሉ ሁከቱን ወደ ግጭት ከፍ ያደርገዋል።

አንድ ጊዜ አንድ ተጫዋች ዳኛው ቢጫ ካርድ ሲያሳየው እጁን ወደኋላ አድርጎ ከወገቡ ጎንበስ በማለት ከንፈሩን አንቀሳቀሰ፤ ዳኛው ተበሳጭቶ ቀይ ካርድ ሰጠው። ደጋፊው ደግሞ ‹‹ከዚህ በላይ ምን ያድርግልህ! ውሳኔህን አክብሮ በጸጋ ጎንበስ ብሎ ተቀበለ፤ ይስገድልህ ወይ›› ብሎ ሁከት አነሳ። በኋላ ሁኔታው ሲጣራ ተጫዋቹ ለደጋፊው ጎንበስ ብሎ ቢታይም፣ ለዳኛው ግን ‹‹እናትህ እንዲህ ትሁን›› ነበር ያለው። ዳኛው በስድቡ ተበሳጭቶ ነው ለካ ቀይ ካርድ የሰጠው። ግን ሁከት ተፈጠረ።

በዳኞች በኩል ደግሞ የአቅም ማነስ፣ ብዙ ደጋፊ ባለው ክለብ ጫና ስር መውደቅና ፍርድ ማጓደል አለ። በዚህም የተነሳ አንዳንድ ጊዜ ዳኛ አንደኛውን ቡድን ሲበድል የሚነሳ ረብሻም አለ።

ከሚድያ እና ከስፖርት ጋዜጠኝነት ጋር በተያያዘ፣ የትኛውም ሙያ ላይ ጤነኛም በሽተኛም አለ። የባለሙያ እንጂ የሙያ ባለጌ የለም። የዛሬ ስድስት ዓመት ብሔራዊ ቡድናችን ሱዳን ሄዶ ይጫወት ነበር፤ ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ። ግጭት ነበር። አንድ ታዋቂ የስፖርት ጋዜጠኛ በራዲዮ ሲዘግብ “ኧረ ገደሉን፣ በድንጋይ መቱን፣ ወረወሩብን” እያለ ነበር። ይሄ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ምን ዓይነት ስሜት ፈጠረ? ሱዳኖች ለመልስ ጨዋታ ሲመጡ ቂም የቋጠረ ደጋፊ ነበር የጠበቃቸው።

በእርግጥ የስፖርት ጋዜጠኝነት ለስሜት የተጋለጠ ነው። ማንኛውም ጋዜጠኛ በግሉ የሚወደውና የሚደግፈው ክለብ ሊኖረው ይችላል። ነገር ግን ዘገባውን ሲሰራ ከስሜት ጸድቶ፣ በሙያዊ ብቃትና ሥነምግባር በተላበሰ ቋንቋ መዘገብ ነው ያለበት። ሆኖም፣ በስፖርት ዘጋቢዎች አካባቢ ያለው ችግር- አንዱን የመደገፍና ሌላውን የመንቀፍ ዝንባሌ ነው።

አንድ ሌላ የራዲዮ ጋዜጠኛ ደግሞ ደደቢት ከቡና ጋር ሲጫወቱ ቡና አራት ለዜሮ አሸነፈ። ይሄ ጋዜጠኛ ሲዘግብ “ቡና ደደቢትን አራት ለዜሮ ረመረመው” ብሎ ዘገበ። በሁለተኛው ዙር ጊዮርጊስ አራት ለዜሮ አሸነፈ። ዜና ሲዘግብ ግን “ጊዮርጊስ አሸነፈ” ብቻ ነው ያለው። ስለዚህ ተመልካቹ ጋዜጠኛው የማን ደጋፊ እንደሆነ አወቀ ተባለ።

በፌደሬሽን በኩል ደግሞ ሦስት ችግሮች ጎልተው ይታያሉ። አንደኛ ወጥ ፕሮግራም የለውም፣ ይዋዥቃል። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ፕሪሜር ሊግ ጥቅምት 4 ቀን ነው የሚጀምረው ተባለ። ከዛ ለአንድ ሳምንት አራዘመውና ለጥቅምት 11 ይጀምራል ተባለ። እንደገና ደግሞ ለ18 ተብሎ ተራዘመ። የተጀመረው ግን ጥቅምት 25 ቀን ነው።

በሌላ በኩል የፍትሐዊነት ጥያቄ አለ። ለምሳሌ አንድ ክለብ በገሃድ ሲቀጣ፣ የፌደሬሽኑ አመራሮች በጎን ያንዱን ቅጣት ያነሳሉ። የሌላውን ደግሞ አያነሱም። ሁለት ክለቦችን በእኩል አያዩም፤ አያስተናግዱም። ለምሳሌ አንድ ተጫዋች ተቀጣ። ለሁሉም ክለቦች በደብዳቤ አምስት ጨዋታዎች ተቀጣ ተብሎ ይነገራል። በጎን ደግሞ በሌላ ውሳኔ ይነሳለትና ቅጣቱን ሳይጨርስ ይጫወታል። ይህ በሌሎች ክለቦችና ደጋፊዎቻቸው ዘንድ ቅሬታ ይፈጥራል።

ውድ አንባቢያን፣ ይህን ጽሑፍ እያዘጋጀን በነበረበት ወቅት ሁለት ቸር ወሬዎችን ሰምተናል። የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በስፖርት ሜዳዎች የማንም ደም መፍሰስ የለበትም፣ ይልቁንም ‹‹ደማችን ለወገናችን›› በሚል ዓላማ ህዳር 3 ቀን 2010 ዓ.ም. በቀይ መስቀል ተገኝተው የደም ልገሳ ፕሮግራም ማካሄዳቸው ነው። ሁለተኛው የጎንደሩ ፋሲል ከነማ ቡድን ለውድድር አዲግራት ከተማ ሲገባ ህዝቡ ልዩና ደማቅ የሆነ አቀባበል ያደረገለት መሆኑ ነው። ይህም የሰፖርታዊ ጨዋነት አንዱ መገለጫ ነውና ይበል ይበል ብለናል። ቀጥለን ደግሞ ያነሳናቸውን ሃሳቦች የሚያጠናክሩልንና በስፖርቱ መስክ ያገለገሉ ባለሙያዎችን አነጋግረናል። እነርሱም አቶ ኢብራሂም ሀጂ ከሠላሳ ዓመታት በላይ በስፖርት ጋዜጠኝነት ያገለገለ፣ አቶ አዳነ ሽጉጤ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊና ዋና አስጨፋሪ፣ አቶ ይድነቃቸው አሸናፊ (አቸኑ) የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ደጋፊና ዋና አስጨፋሪ፣ ናቸው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top