ከቀንዱም ከሸሆናውም

አጼ ኃይለሥላሴና ቴያትር

ከወጣትነቱ ጀምሮ ከኪነጥበብ አምባ ያልራቀውና ለቁጥር በሚያታክቱ ቴያትሮች ላይ የተወነው አንጋፋ ከያኒ ጌታቸው ደባልቄ ዛሬም በአረጋዊነቱ ከዚያው የጥበብ አድባሩ አይጠፋም። እናም መረጃ የፈለገ ተመራማሪ፣ ጋዜጠኛ ወይም የጥበብ ሰው ብሔራዊ ቴያትር ውስጥ ፈልጎ አያጣውም። እሱም ያለፈበትን ረዥም የኪነጥበብ ህይወት ፍንትው አድርጎ ከማሳየት አይቦዝንም። የታዛ መጽሔት ዝግጅት ክፍል ባልደረባ ዓለማየሁ ገ/ ሕይወትም በተወሰኑ አጋጣሚዎች ከከያኒ ጌታቸው ደባልቄ ጋር ተወያይቶ ነበር። ለዛሬ ከቤተመንግስትና ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጋር የተያያዙ ቴያትር ነክ ገጠመኞችን እንዲህ አቅርቦላችኋል።

የኦቴሎ ቴያትር ተርጓሚና ተዋንያን በቤተመንግስት

በእንግሊዛዊው ዊልያም ሼክስፒር ተደርሶ በታላቁ ገጣሚና ጸሐፌ ተውኔት ፀጋዬ ገብረመድኅን ወደ አማርኛ የተተረጎመው ኦቴሎ በ1964/65 ዓ.ም. በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ (ዛሬ ብሔራዊ) ቴያትር መድረክ ቀርቦ ነበር። አንዱን ቀን ታዲያ አጼ ኃይለሥላሴ ቴያትሩን በአካል ተገኝተው ተመለከቱ። ከዚያ ወዲያ ያለውን ታሪክ ከአንጋፋው ከያኒ ጌታቸው ደባልቄ አንደበት እንከታተል።

“በማግስቱ ተጠራንና ወደቤተመንግስት ሄድን። ብላታ ግርማቸው፣ ያን ጊዜ ገና ደጃዝማች አልተባሉም፣ የማስታወቂያ ሚኒስትር ነበሩ። አቶ ከበደ አስፋው ደግሞ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቴያትር ሃላፊና ረዳት ሚኒስትር ነበሩ። ሁለቱ ሃላፊዎች ጃንሆይ ፊት ይዘውን ቀረቡ።

“በእውነቱ” አሉ ጃንሆይ በትካዜ አይነት አነጋገር፣ “እንደነዚህ አይነቶቹ ለሃገር የሚጠቅሙና የሚያስተምሩ ድርሰቶች፣ በልጆቻችን እየተተረጎሙ ማየታችን ራሱ በጣም አስደስቶናል። ውጪ ሆነን በሌላ ቋንቋ አይተነዋል። ሆኖም ይህን ሰራን ብላችሁ እንዳይበቃችሁ፣ ሌላም ተመሳሳይ ቴያትር እያሳያችሁ ህዝቡን አስተምሩ።” ሲሉ ፀጋዬ ጣልቃ ገባና “ጃንሆይ፣ ሰባት ጊዜ ጠርቼዎት ሰባት ጊዜም አልመጡልኝም” ይላቸዋል።

ያን ጊዜ ካባቸውን ወደጎን ብትን አደረጉና “እኮ የት? በየትኛው ቀን?”

“እኔ ላለቃዬ፣ አለቃዬ ላለቃቸው፣ እሳቸው ደግሞ ለግርማዊነትዎ” ይላል ፀጋዬ። አቶ ከበደ አስፋው ናቸው እንግዲህ ሌላ አለቃ የለም።

“ይኼ ነዋ! ይችላል ብለን አስቀምጠነው …” ሲሉ ጃንሆይ አቶ ከበደ ለጥ ብለው እጅ ነሱ። ያው እሳቸውን ነዋ የወቀሷቸው። ይህ እንግዲህ ያው ይቅርታ መጠየቅ ማለት ነው። ከዚያ “ግርማዊ ሆይ” አለ ፀጋዬ እንደገና፣ “ኳስ አበደች ከጨርቅ ኳስ ተነስታ እዚህ ደረጃ ስትደርስ የቴያትር ጥበብ ግን ካለችበት ቦታ ፈቅ አላለችም” ይላል። አመጡታ ጃንሆይ! “ኳስ አበደችን ማነው ለዚህ ያበቃው? ማነው? ሰው እኮ ነው! ይድነቃቸው እኮ ነው! እንደሱ ስሯ!” ፀጋዬ እንዴት እጅ ይንሳ? አያውቀውማ የቤተ መንግስቱን ሥርዓት። እጅ ንሱ ነው በየደቂቃው፣ እኛ እጅ እንነሳለን።

ተስፋዬ ሳህሉ ደግሞ ቀጠለ። “ግርማዊ ሆይ፣ ቴያትርን ለዚህ ስናደርስ ሴት ባልነበረበት ጊዜ ቅንድባችንን እየተላጨን ሰርተናል፣ ከዚያ ሴቶች ወደ መድረኩ እንዲመጡ አድርገን ጥበቡን እዚህ ደረጃ አድርሰናል” ሲል “ታዲያ ምን ጎደለህ?” አሉት ጃንሆይ።

“ያለ አቤቱታ ደሞዛችንን አግኝተን አናውቅም” ይላል። አቤቱታ ተጀመረ እንግዲህ። ያን ጊዜ እልፍኝ አስከልካዩ መጥቶ ወደ ውጪ አስወጣን። ስሞታ ማቅረብ ጀመርና! ትንሽ ቆየት ብሎ ደግሞ ተጠራንና ገባን።

“በሉ አሁን ለችግራችሁ እንዲሆን አንዳንድ ነገር አዘንላችኋል” ሲሉ ጃንሆይ እጅ ንሱ ተባልን። እጅ ነሳን። ከዚያ በኋላ መቶ መቶ ብር ሰጡን። ተስፋዬ ሳህሉ ታዲያ፣ “ከጃንሆይ አንደበት መቶ ብር ስጡ የሚል አልተነገረም። ይቺን ደግሞ አንድ ቀን ሲያጋጥሙኝ እነግራቸዋለሁ” አላቸው። “አንሷል ለማለት ነው አይደል?” “ታዲያስ!”ጌታቸው ደባልቄ

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና የጠቅላይ ሚኒስትራቸው ቴያትር

የጠቅላይ ሚኒስትር መኮንን እንዳልካቸው ድርሰት የሆነው “አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም” ቴያትር በ1951 ዓ.ም. በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴያትር ታይቶ ነበር። በአምስት ዓመቱ የጠላት ወረራ ላይ የተመሰረተ ታሪክ ያለው ነው። አቶ አሐዱ ሳቡሬ በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ቴያትሩን ተችተው ይጽፋሉ። አቶ ተማቹ የተባለው ዐቢይ ገጸባህሪይ ምንም አይነት ኢትዮጵያዊ ቁመና እንደሌለው፣ እሬሳ መሃል ቆሞ አሞራ ሲያባርር እንጂ ሲተኩስ እንደማይታይ፤ ቤቱ ሲመጣ ደግሞ ሚስቱ ከጣሊያኖች ጋር ስትደንስ አይቶ፣ እሱ ወይን የጠጣበትንና ከንፈሩ የነካውን ብርጭቆ ሲሰብሩት ተመልክቶ፣ ደብዳቤ ከጻፈ በኋላ ራሱን መስቀሉ ደካማነቱን ነው የሚያሳየው ብለው ተችተውታል። በዚህ ቅር የተሰኙት ደራሲው ራስ ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸውም አቶ አሐዱን ጃንሆይ ዘንድ ይከሷቸዋል። አቶ አሐዱ ይጠሩና ቤተመንግስት ሲደርሱ አቶ መኮንን ውጪ ሆነው ሲጠባበቁ ያገኟቸዋል። ውስጥ እንደገቡም ጃንሆይ ፈጠን ብለው፣ አሐዱ ሳቡሬ “አሐዱ! ምነው አሐዱ አልክብኝ” ይሏቸዋል። ከዚያ በጋዜጣ ላይ ስለጻፉት ነገር በዝርዝር ማስረዳት ሲጀምሩ ጃንሆይ ያቋርጧቸውና፣

“እኔም ላመሰግንህ ነው የጠራሁህ፣ ትክክለኛ እርማት ነው የሰጠኸው” ይላሉ። አቶ አሐዱ ለጥ ብለው እጅ ነስተው ይወጣሉ። ውጪም እንዲሁ አቶ መኮንንን እጅ ነስተው ሲሄዱ ከደራሲው አንደበት የሰሙት አንድ ቃል ብቻ ነበር፣ “ታዝቤሃለሁ!”።

“ልደተ ኢትዮጵያ” እና አጼ ኃይለሥላሴ

አቶ ኢዩኤል ዮሐንስ የደረሱትን “ልደተ ኢትዮጵያ” የተሰኘ ተውኔት በመጀመሪያ ሳንሱር ይከለክለዋል። በኋላ ግን ቤተመንግስት የግቢ ሚኒስትሩ ፀሃፌ ትዕዛዝ ተፈራወርቅ ኪዳነወልድ ፅሁፈ ተውኔቱን ንጉሡ ዘንድ አቅርበው፣ እሳቸው ከማየታቸው በፊት ለህዝብ እንደማይታይ አሳምነው፣ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቴያትር እንዲሰራ አስፈቀዱ። በዚያን ጊዜ እንደልዩ ፀሃፊያቸውም እንደ አስተርጓሚያቸውና አማካሪያቸውም ነበሩ። እናም ከያኒ ጌታቸው ደባልቄ በ1960 ዓ.ም. አዘጋጀውና ንጉሡ ቴያትሩን ሊመለከቱ መጡ። መኪናቸው በረንዳው ላይ ቆመ። ከዚያ ገቡና ባልኮኒያቸው ላይ ተቀመጡ። ቀሪውን ከከያኒ ጌታቸው አንደበት።

“ቴያትሩ ሲጀመር ሃይለኛ የዝናብ ድምጽ ይሰማል። ፊት ለፊት የሚታየው ትዕይንት (ሥዕል) ደግሞ ኤጄርሳ ጓሮን የሚያሳይ ነው። ራስ መኮንን ከፍ ያለ ቦታ ላይ ቁጭ ብለው አንድ መልዓክ ከኋላ ያነጋግራቸዋል። የራስ መኮንንን ገጸባህሪይ የተጫወተው ተስፋዬ ሳህሉ ነበር። ታዲያ መልዓኩ “ወንድ ልጅ ትወልዳለህ፣ ስሙንም ኃይለሥላሴ ትለዋለህ፣ እሱም የኢትዮጵያ መሪ ይሆናል” ከማለቱ ንጉሡ ካባቸውን አወናጭፈው ተነስተው ይሄዳሉ – ብቻቸውን። ሾፌሮቹ ሁሉ ቁጭ ብለዋል። አንጋቾቹም ሌሎቹም አብረው የመጡት የግቢ ሚኒስቴር ሰዎች፣ ጄኔራል አሰፋ የእልፍኝ አስከልካዩ ጭምር ቁጭ ብለው ቴያትር ያያሉ። ጃንሆይ ወጥተው ታች ወደ መኪናቸው ሲሄዱ ኃይሉ ገ/ማርያም የሚባል የቴያትር ቤቱ ባልደረባ ተከትሎ፣ ሲፈራ ሲቸር ካባቸውን አስተካክሎ ያለብሳቸዋል። ጃንሆይ ግን፡-

“ማነው እኛን መለኮት ያደረገን? እኛ እንደማንኛውም ሰው ነን። ማነው እኮ መለኮት ያደረገን? ማነው እሱ?” እያሉ ንዴታቸውን መቆጣጠር ተስኗቸዋል። ይሄኔ አቶ ከበደ አስፋው፣ የቴያትር ቤቱ ረዳት ሚኒስትር፣ እኔም ባዘጋጅነቴ ሮጠን መጣን። ኃይሉ ወደ መኪናቸው አቅጣጫ የሚወስደውን የውጩን በር ከፈተላቸው። ከዚያ ሌሎቹ ሰዎች ሁሉ መጡ። ወዲያው መኪናቸው ውስጥ ገቡ። ምን ልበልህ ተቆጡ፣ ተቆጡ። እርግጠኛ ነኝ በጊዜው ፈርተው ካልጣሉት በስተቀር ተውኔቱ ቢፈለግ አይጠፋም። በቁም ጽሕፈት የተጻፈ ነበር።

“በቃ ገና ሲጀመር ነዋ ወጥተው የሄዱት?”

“ታዲያስ!”

“ከዚያ በኋላስ ቴያትሩ ታዬ? እንደው ተሻሽሎም ቢሆን ማለቴ ነው።”

“በፍጹም፣ አልታዬም። እሳቸው እንዲያ ብለው ተናግረው ማን ይሞክራታል”

“የተጀመረውስ ቴያትር እንዴት ሆነ? መቼም ብዙ ተጋባዥ/ተመልካች ይኖራል”

“የለም ከርሳቸው ጋር ከመጡትና ከቤተመንግስት እንዲህ ነው እንጂ ገና ለሕዝብ ክፍት አልተደረገም ነበር። እሳቸው ከተመለከቱት በኋላ ለህዝብ ይታያል የሚል ሃሳብ ነበር። ያው እንደሳንሱር ማለት ነው።”

“እስኪ ታሪኩን ጨርስልኝ። ከትንቢቱ በኋላ ምንድነው የሚሆነው?”

“ያው የታወቀው ነው፣ ይወለዳሉ፣ ራስ መኮንንም ልጃቸውን ያሳድጋሉ። ከዚያ እንደተባለው አድገው የሃገር መሪ ይሆናሉ።

የኢትዮጵያ ልደት ነው የጠቅል ልደቱ እንደማቱሳላ በእድሜ ይሰንብቱ፣ እያለ የጻፈው ነው። ነገሩ እንደአሁን ቢሆን ቢታይ ምንም አልነበረም። ግን እንደዘመኑ ነው፣ እንደጊዜው።”

ትኋን ይዞ ቤተመንግስት የገባው ቴያትር

አንጋፋዎቹ የመድረክ ባለሙያዎች አውላቸው ደጀኔ፣ ተስፋዬ ሳህሉና ጌታቸው ደባልቄ የሚተውኑበት የታላቁ ደራሲ የፀጋዬ ገብረመድኅን ቴያትር “የከርሞ ሰው” በአንድ ወቅት በቤተመንግስት ቀርቦ ነበር። ያን ወቅት ከያኒ ጌታቸው ደባልቄ እንዲህ ያስታውሰዋል።

“በ1961 ዓ.ም. “የከርሞ ሰው” ቴያትርን በቤተመንግስት ስንሰራ ዋናዎቹ ተመልካቾች ጃንሆይ፣ ልዑላን ቤተሰቦች፣ ልዑል ራስ እምሩ፣ ልዕልት ሳራ ግዛው፣ እነሱ እነሱ ነበሩ። እንግዲህ እንደምታውቀው ታሪኩ አጎታችን ከገጠር መጥቶ እኛ ዘንድ አርፏል። የእኔ አልጋ ላይ ነው የሚተኛው። እና ቴያትሩ እንደተጀመረ እዘልና “መቼ ነው አልጋዬን የሚለቅልኝ?” እላለሁ። (አብዬ ዘርፉ ገመምተኛ ሽማግሌ ናቸው።) ከበስተጀርባ ደግሞ የዕድር ልፈፋ ይሰማል። ከዚያ እንደገና ከአጎቴ ጋር እነጋገራለሁ።

“አብዬ ዘርፉ ቁርስህን በላህ?” ስለው “መቼም እንደነገሩ” ይለኛል። ደግሞ መለስ ብዬ “መቼ ነው ቦታዬን የሚለቅልኝ” እላለሁ። ያን ጊዜ መብራት ድርግም ይላል። ከአፍታ በኋላ ሲበራ ወፍ እንኳ የለም። ግራ ገባን። በኋላ ዶ/ር ምናሴ ኃይሌ መጡ፣ የማስታወቂያ ሚኒስትር ነበሩ። “ጃንሆይ በሌላ ቀን እጨርሰዋለሁ ብለዋል” አሉን። ከዚያ ከመድረክ ጀርባ ወስደው ቢራ ጠጡ አሉን፣ አንጠጣም አልን። ቆየት ብሎ ዋናው አስተናጋጅ መጣና “በሉ በሉ ውስኪ አምጡላቸው” አለና ጋበዘን፣ ጠጣን። የመድረክ ቁሳቁሱንም አልባሳቱንም እዚያው ትተን ሄድን። ከዚያ ከዛሬ ነገ ጠርተው ያሰሩንና ይሸልሙናል ብለን ብንጠብቅ ብንጠብቅ ምንም የለም። ጭራሽ አንድ ቀን የንብረት ክፍሉ ደውሎ “ኑና ይህን ኮተታችሁን ከነትኋናችሁ ውሰዱ” አለን። ከዚያ የመድረክ ክፍሎች ሊያመጡ ሲሄዱ እውነትም የሳር ፍራሹ ትኋን በትኋን ሆኗል። ያው የደካከመ የድሆች አይነት ቤት ነው። ፍራሹም ከመንገድ ላይ የተገዛ መሰለኝ። በቃ ቴያትሩን ሳንጨርሰው ቀረን።”

 

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top