ጣዕሞት

ባዶ እግር (ቴያትር)

‹‹ባዶ እግር›› ተውኔት፣ በቅርቡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴያትር ተመርቆ ዘወትር እሁድ በ8፡ 00 ሰዓት ለመድረክ የበቃ ቴያትር ነው። ደራሲ አሜሪካዊው ማክስዌል አንድርሰን፤ ተርጓሚ አስቻለው ፈቃደ፤ አርታዒ ደበበ እሸቱ እና ራሔል ተሾመ፤ አዘጋጅ ራሔል ተሸመ፤ ረዳት አዘጋጅ እንዳለ ብርሃኑ፤ ዝግጅት አስተባባሪ አልጋነሽ ታሪኩ፤ ኮሪዎግራፊ ብርሃኑ ተስፋዬ፤ የመድረክ ገጽ ሥዕልና ዲዛይን ታፈሰ ለማ፤ የፖስተር ዲዛይን የማነ ልዑል፤ ተዋንያን (ከአንጋፋው ስዩም ተፈራ እስከ ወጣት አርቲስቶች) በርከት ያሉ ተዋንያን የሚሳተፉበት የሙሉ ጊዜ ቴያትር ነው።

‹‹ባዶ እግር በአቴንስ›› በጥንታዊቷ ግሪክ ዝነኛ ፈላስፋ በሶቅራጦስ የመጨረሻ የህይወት ምዕራፍ ላይ የተመሰረተ የተውኔት ጽሑፍ ነው። ‹‹የሶቅራጦስ የመጨረሻዎቹ ቀናት›› በሚል ርዕስ የሶቅራጦስ ደቀመዝሙር የነበረው ፕሌቶ (አፍላጦን) ከጻፈው መጽሐፍ ውስጥ የሶቅራጦስን የመጨረሻ የህይወት ምዕራፍ መነሻ አድርጎ አሜሪካዊው ዝነኛ ጸሐፌ ተውኔት፣ መምህርና ጋዜጠኛ ማክስዌል አንደርሰን የጻፈው የዘመናችን ታላቅ ተውኔት እንደሆነ ይታመናል።

‹‹ባዶ እግር በአቴንስ›› የተሰኘውን ቴያትር የሚመለከት ሰው ይስቃል፣ ያለቅሳል፣ በራሱ የሕይወት ትርጉም ይብሰለሰላል። በቴያትሩ መደምደሚያ ባለው የፍርድ ሂደት ላይ ደግሞ አንዳች ኃይል ተመልካቹን ከመቀመጫው ተነስቶ ወደ መድረክ እንዲወጣ ይገፋፋዋል።

አዎን! የእያንዳንዳችንን የሕይወት ትርጉም የሚጠይቅ የዘመናችን ድንቅ ተውኔት ነው። የሺህ ዓመታት ልዩነት ሳይገድበው እኛን ከሶቅራጦስና ፕሌቶ ጋር ዘመነኛ አድርጎ የጥንትና የዛሬን ልዩነት እንዳንለይ ያደረገን ጸሐፌ ተውኔት ማክስዌል አንደርሰን ነው ይላሉ አስተያየት ሰጪዎች።

የተውኔቱ መነሻ!

‹‹የሶቅራጦስ የመጨረሻዎቹ ቀናት›› ፕሌቶ እንደጻፈው

ጽሑፉ ከጥንታዊ ግሪክ ዝነኛ ፈላስፎች አንዱ በሆነው በሶቅራጦስ ህይወት ውስጥ የመጨረሻዎቹ ቀናት ምን ይመስሉ ነበር? የሚለውን ባጭሩ ያስቃኛል። በእርግጥም ጽሑፉ በርካታ የፍልስፍና ጽንሰ- ሃሳቦችን የያዘ ቢሆንም፣ ይህ ጽሑፍ በሶቅራጦስ የመጨረሻዎቹ ቀናት ላይ ያተኩራል።

ሶቅራጦስ በጥንታዊቷ አቴና ነው የኖረውና የሥራ ዓለም ዘመኑን ያሳለፈው። ባለትዳርና የልጆች አባት የነበረው ሶቅራጦስ በአቴና ከተማ ስሙ የገነነውን ያህል ኑሮው በተለይም በህይወቱ የመጨረሻዎቹ ምዕራፍ አካባቢ በችግር የተሞላ ነበር። በባዶ እግሩ በአቴንስ ጎዳና መኳተኑም ለባለቤቱ ዛንቲፕና ለልጆቹ ሐፍረትና መሸማቀቅን አትርፎላቸው እንመለከታለን።

ጠንካራ ማህበራዊ ትስስር የነበረው ሶቅራጦስ የፍልስፍና አስተምህሮው የዘመኑን ወጣቶችና ተከታዮች አስተሳሰብ በእጅጉ ቀይሯል። በተለይም በተከታዩ ፕሌቶ አስተባባሪነት ይካሄድ የነበረው ክርክርና የሃሳብ ልውውጥ የወጣቶችን ልብ አሸፍቷል።

‹‹እውነት ምንድን ነው?›› በሚለው ጥያቄ የታጀበው ፍልስፍና ማለቂያ የለሽ ጥያቄዎችን እያስከተለ ይነጉዳል። ይሁንና የጥያቄዎቹ ጥልቅ ጽንሰ-ሃሳብ ደግሞ የአቴና ከተማን ፈላጭ ቆራጭ ሥነ-መንግሥት (ፖለቲካ) ይጎነትላል። ይገዘግዛል። እናም የጊዜው የአካባቢ ገዢዎች የፈላስፋው ሃሳብና አስተምህሮ ከፊታቸው ከባድ ስጋት ደቀነባቸው። የሶቅራጦስ ስጋትም ከዕለት ወደ ዕለት እያየለ ሲመጣ፣ ይህንን ሰው በማንኛውም መንገድ ማስወገድ እንደሚገባ ድምዳሜ ላይ ደረሱ።

እናም የኋላ ኋላ የአቴና ከሳሾቹ ለሶቅራጦስ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጡት። አቴናን ለዘለዓለሙ ለቆ እንዲሰደድ፣ አሊያም በአቴና ምድር የሞትን ፅዋ እንዲጎነጭ ሁለት አማራጮች አቀረቡለት።

ፈላስፋው ግን፣ እጅግ የሚወደውን የአቴና ሕዝብ ለቆ ከመሰደድ የሞት ፍርድ መቀበልን መረጠ። ከቤተሰብ፣ ከወዳጅ ዘመድ ሁሉ ተሰደህ ህይወትህን አትርፍ የሚሉትን መካሪዎች እነርሱኑ መልሶ በጥያቄ እና መልስ እያሳመነ በዕምነቱ ጸና።

እናም፣ የሰባ ዓመት አዛውንቱ ችሎት ፊት ቀርቦ ከሳሾቹን በጥያቄ እያጣደፈ መተንፈሻ አሳጣቸው። የችሎቱ ውሎና የመጨረሻው ፍርድስ ምን ይሆን? …

መልሱን እሁድ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ በብሔራዊ ቴያትር አዳራሽ ታገኛላችሁ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top