በላ ልበልሃ

ባህልና ሥነጥበብ ለሀገር ልማት

በበለጸጉ አገራት የባህል ኢንዱስትሪ ተሞክሮ

መግቢያ፡-

ስለአገራችን ባህልና ስነጥበብ መበልጸግ፣ መጠናትና መሰነድ በተለያዩ መድረኮች፣ በተለይም በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጉባኤዎች፣ በአዲስ አበባ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ስብሰባዎች፣ በባህል ማእከላት ኮንፈረንሶች፣ እንዲሁም በመገናኛ ብዙሀን በተደጋጋሚ ይነሳል። በአገራችን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድና በባህል ፖሊሲ ማሻሻያ ረቂቅ ላይ ውይይት በተደረገበትም ወቅት ለባህልና ስነጥበባት እየተሰጠ ያለው ትኩረት ከተገቢው ደረጃ አለመድረሱ ተጠቁሟል። መንግስትም ለሌሎች የልማት ዘርፎች የሚያደርገውን ድጋፍ ለባህልና ስነጥበባትም እድገት ማድረግ እንደሚጠበቅበት በስነጥበብ ባለሙያዎች ዘወትር ይወሳል።

በአኳያው ደግሞ፣ መንግስት ባለው ውስን የገንዘብ አቅም ቅድሚያ መስጠት ያለበት ለሌሎች መሰረታዊ የኤኮኖሚና ማህበራዊ ችግሮች እንጂ እንደስነጥበብ ላለው ቅንጦት መሆን የለበትም ሲባል ይደመጣል። አገሪቷ በምትከተለው የነጻ ገበያ ስርአት፣ ባህልና ስነጥበብ በሂደት በራሳቸው የሚበለጽጉ እንጂ የመንግስትን ጣልቃገብነት የሚሹ አይደሉም እየተባለም ይነገራል።

በሌላ በኩል፣ የሰውን ልጅ ከሌሎች ፍጡራን በሚለየው ተፈጥሯዊ ህገ ደንብ ሳቢያ ባህልና ስነጥበብ ከማህበረ- ኤኮኖሚ ተነጥለው ሊታዩ እንደማይችሉ፣ እንዲያውም ከነአካቴው ባህልና ስነጥበብን የማያማክል ማንኛውም የልማት እቅድ ግቡን እንደማይመታ፣ ስለዚህም ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው እንደሌሎቹ የነጻ ገበያ ስርአት አራማጅ አገሮች በታክስ ቅነሳና በገንዘብ ድጎማ ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ የሚሞግቱ አሉ። የስነጥበባት ማህበራትም ይህንኑ በጥናትና ምርምር አስደግፈው ለመንግስት ማቅረባቸው ይታወሳል። ምናልባትም የቀረቡት አስተያየቶች ጠንክረው ባለመውጣታቸውና የማሳመን አቅማቸው ባለመጎልበቱ መሆኑ እንደ አንድ ምክንያት ተወስዶ፣ እስካሁን በዚህ ረገድ የተካሄደው እርምጃ ጎልቶ የወጣ አልሆነም። ይህም የመወያያ ጽሑፍ ለባህልና ስነጥበብ ብልጽግና የሚሰጠው እገዛ ጥቅሙ ለመንግስትም ጭምር መሆኑን ለማሳየትና የተሻለ ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ ነው። ጽሑፉ፣ የባህል/ ፈጠራ ኢንዱስትሪን ብያኔ፣ የባህል/ፈጠራ ኢንዱስትሪ ለአገር ልማትና ለስራ ፈጠራ የሚያበረክተውን አስተዋጽዎ፣ በአንጻሩ ኢንዱስትሪው ለባህልና ስነጥበብ ብልጽግና የሚኖረውን ፋይዳ፣ የበለጸጉ አገራትን የባህል ኢንዱስትሪ ገጽታ በማመልከት ያብራራል።

በዚሁ ላይ በመንተራስም፣ የሀገራችን የባህል/የፈጠራ ኢንዱስትሪ ከእነዚህ አገሮች ተሞክሮዎች ምን ሊቀስም እንደሚችል ይጠቁማል። በመንግስትና በስነጥበባት መካከል ያለውንም መስተጋብር ያመለክታል።

የባህላዊና የፈጠራ ኢንዱሰትሪ (Cultural and Creative Industries) ድንጋጌ

ዩኔስኮ ስለባህላዊ ፈጠራ ኢንዱስትሪ የሚከተለውን ደንግጓል፡- “የባህላዊ የፈጠራ ኢንዱስትሪ፣ ባህላዊ፣ ስነጥበባዊ ወይንም ቅርስ ነክ የሆኑትን ቁሳቁስና አገልግሎት ማምረትን ወይም ማባዛትን፣ ማስተዋወቅን፣ ማሰራጨትን ወይንም ለንግድ ማዋልን፣ ዋና መርሆው ያደረገ ተግባር ነው።” ‹የፈጠራ ኢንዱስትሪ› ሀብትን ለማፍሪያና ለስራ ፈጠራ የሚያግዙትን የችሎታን፣ የክህሎትንና የፈጠራን አስፈላጊነት አጉልቶ የሚያመለክት ነው።

ከዚያም አንጻር፣ ‹የባህል-ፈጠራ ኢንዱስትሪ› ስያሜ በአስራ አንድ ዘርፎች ላይ ትኩረት የሚያደርግ ይመስላል። እነሱም፡- ትውን ጥበባት፣ (ዳንስ፣ ቴያትር፣ የሙዚቃ ትርኢት፣ ኦፔራ፣ ባሌ)፤ ሙዚቃ፡-(ዘፈን መቅዳት፣ ሙዚቃ ማተም፣ የሙዚቃ አቅርቦት)፤ ተንቀሳቃሽ ምስል (የፊልም ምርትና ድህረ-ምርት)፤ የቴሌቪዥን ፕሮግራም (ምርትና ስርጭት፣ ኬብልና ሳተላይትን ጨምሮ)፣ የሬዲዮ ስርጭት ተግባራት፣ መጻህፍት (የወረቀትና ዲጂታል ህትመት)፣ የጋዜጣና መጽሄት ህትመት፣ የርእይ ጥበባት (ስእልና ቅርጻቅርጽ፣ ሙዚየም፣ ፎቶግራፍና ዲዛይን፣ ማስታወቂያ)፣ ጨዋታዎች (የቪዲዮ ጨዋታ ፈጣሪዎች፣ አታሚዎች፣ ሽያጭ)፣ አርክቴክቸር ናቸው።

ባህላዊ የፈጠራ ኢንዱስትሪ፣ በእውቀትና በጉልበት ላይ በመመርኮዝ ስራ የሚፈጠርበት፣ ሀብት የሚካበትበት በመሆኑና፣ ለአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ወሳኝ ድርሻ ያለው በመሆኑ፣ በተለይ በበለጸጉት አገራት መንግስታትና በአለም አቀፍ ድርጅቶች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት፣ ብሔራዊና አለማቀፋዊ ገዢ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተነደፉለት ነው።

የምእራቡ አገር የባህል ኢንዱስትሪ ንድፈ ሀሳብ፣ ልዩ አጽንኦት የሚሰጠው ከገንዘብ ገቢ ጋር ለተያያዘ ጉዳይ ነው። የዘመኑ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ፈጣን እድገት፣ የባህል ቁሳቁሶች፣ የግልጋሎቶችና የኢንቨስትመንት ፍሰት ሁኔታዎች ከቀድሞው በመለወጣቸው የባህል- ፈጠራ ኢንዱስትሪ በርካታ ቱጃሮችን (ባለሚሊዮኖችንና ባለቢሊዮኖችን) እየፈጠረ ይገኛል። ለኢንዱስትሪው አለማቀፋዊ ባሕርይን በማላበሱም ሉላዊ ሞኖፖሊ ጭምር ሊከሰት በቅቷል።

ባህላዊ የፈጠራ ኢንዱስትሪ ለማህበረ-ኤኮኖሚ እድገት

በቅድሚያ አለማቀፋዊ ገጽታውን ከታክስ ገቢና የስራ ፈጠራ አንጻር እንመልከት። የባህል-ፈጠራ ኢንዱስትሪ በአለም አቀፍ ደረጃ በአንድ አመት ብቻ (2005 አ.ም.) 2.2 ቢሊዮን ዶላር የታክስ ገቢ አስገኝቷል። ይህም፣ የአለም ጂዲፒን 3 በመቶ ያህል ማለት ነው። ከህንድ ጂዲፒ (1.9 ቢሊዮን ዶላር) ይልቃል፤ ከኢትዮጵያም እንዲሁ። በዝርዝር ሲታይ፤ የባህላዊ-ፈጠራ ኢንዱስትሪ ያስገኘው የታክስ ገቢ በዶላር፡- ከቴሌቪዥን 4.7 ቢሊዮን፣ ከርእይ ጥበባት 3.9 ቢሊዮን፣ ከጋዜጣና መጽሄት 3.5 ቢሊዮን፣ ከማስታወቂያ 2.8 ቢሊዮን፣ ከስነሕንጻ 2.2 ቢሊዮን፣ ከመጻህፍት 1.4 ቢሊዮን፣ ከትውን ጥበባት 1.2 ቢሊዮን፣ ከሲኒማ 772.4 ሚሊዮን፣ ከሙዚቃ 653.9 ሚሊዮን፣ ከሬዲዮ 46.5 ሚሊዮን ነው።

የባህል-ፈጠራ ኢንዱስትሪ በአንድ አመት ውስጥ ለ29.5 ሚሊዮን ሰዎች የስራ እድል ፈጥሯል። የርእይ ጥበባት 6.73 ሚሊዮን ስራ፣ የመጽሀፍ ህትመት 3.67 ሚሊዮን ስራ፣ ሙዚቃ 3.98 ሚሊዮን ስራ አስገኝቷል። በአለም ላይ በተለያዩ ስራዎች ከተሰማሩት ውስጥ 1 በመቶ የሚሆኑት የባህል-ፈጠራ ኢንዱስትሪ ሰራተኞች ናቸው። ከነኝሁም ውስጥ የሙዚቃ፣ የሲኒማ፣ የትውን ጥበባትና መጻህፍት ዘርፍ ተቀጣሪዎች 46 በመቶ ሲሆኑ፣ የቴሌቪዥን 35 በመቶ ይደርሳሉ።

የአህጉራት ገጽታው በደረጃ ሲታይ ደግሞ፣ አንደኛው ኤስያ- ፓስፊክ ሲሆን በባህል-ፈጠራ ኢንዱስትሪ ከአለም ታላቁ ገበያ ነው። በአመት 743 ቢሊዮን ዶላር የቀረጥ ገቢ ያስገኘ ሲሆን፣ 12.7 ሚሊዮን ሰራተኞችን አቅፏል። 82,000 አይነት ጋዜጣዎች በማተምና በቀን 110 ሚሊዮን ኮፒ በመሸጥ በአመት 4.37 ቢሊዮን ዶላር የምታስገባውና ከአለም አንደኛ የሆነችው ህንድ ቦሊውድ፣ ኮሊውድ፣ ቶሊውድ በተባሉት የፊልም ተቋማቷ በእያንዳንዳቸው 300 ፊልሞችን በአመት በማውጣትም በአለም አንደኛ አምራች ነች። ዮሚዑሪ ጋዜጣን በቀን 10 ሚሊዮን ቅጂ የምታትመዋ ጃፓን ደግሞ፣ በነዚህ ዘርፎች ብቻ ምን ያህል ሰራተኛ እንዳሰማራችና ምንስ ያህል የቀረጥ ገቢ እንዳስገኘች መገመት አያዳግትም።

በባህል-ፈጠራ ኢንዱስትሪ ሁለተኛው አውሮፓ፤ አጠቃላይ የታክስ ግኝቱ 709 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ በዘርፉ 7.7 ሚሊዮን ህዝብ በስራ ተሰማርቶበታል። የአውሮፓ ባህላዊ ኢኮኖሚን ለየት የሚያደርገው ከታሪክ ላይም መመስረቱ ነው። በአለም ላይ ከታወቁት አስር ሙዚየሞች ሰባቱ በዚህ ክፍለ አህጉር ነው የሚገኙት (3ቱ በፓሪስ፣ 2ቱ በሎንዶን)። እነኚህ ሙዚየሞች በቅርስ፣ በስእል እና ቅርጻቅርጽ ጉብኝት ከፍተኛ ገቢ ያስገባሉ። እንግሊዝ በስእል ገበያ መሪ አገር ነች። ፈረንሳይ በሉላዊ ማስታወቂያ ኢንዱስትሪ የበላይ ናት። ፈረንሳይ በባህላዊ ቱሪዝም፣ በተለይም በፌስቲቫል፣ በሙዚቃ ትርኢት፣ በኦፔራና ጋለሪ ብቻ በአመት 2.6 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ታገኛለች። በዘርፉ የቱርክ አጠቃላይ ገቢ 620 ቢሊዮን ሲሆን፣ 4.7 ሚሊዮን ዜጎቿን ስራ አስይዛበታለች።

ሶስተኛዋ የባህላዊ ፈጠራ ኢንዱስትሪ ገበያ አሜሪካ ነች። 620 ቢሊዮን ዶላር ከታክስ ይገባላታል። ገበያው በባህላዊና መዝናኛ ኤኮኖሚ የሚመራ ነው። 4.7 ሚሊዮን ሰራተኛም ተሰማርቶበታል። ዋነኞቹ መስኮች ቴሌቪዥን፣ ፊልምና ሬዲዮ ሲሆኑ በአንድ አመት ከቴሌቪዥን የ182 ቢሊዮን ዶላር፣ ከፊልም የ28 ቢሊዮን ዶላር፣ ከሬዲዮ የ21 ቢሊዮን ዶላር ሽያጭ ይካሄዳል። የአንድ አመት የባህላዊ ፈጠራ ኢንዱስትሪ የኤክስፖርት ሽያጭዋ 156.8 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ይህም ከሌሎች የውጭ ሽያጯ ለምሳሌ ከኬሚካል ሽያጯ (147.8 ቢሊዮን ዶላር) እና ከግብርና ሽያጯ (68.9 ቢሊዮን ዶላር) ይልቃል። እንዲያም ሆኖ፣ በዲጅታል የባህላዊ ፈጠራ ኢንዱስትሪ ከኤስያና ከአውሮፓ ትበልጣለች። በአለም ታዋቂነትን ያተረፉት የዩስተን ቴክሳስ ፌስቲቫሎች በአመት (በ2014 እ.ኤ.አ.) 315 ሚሊዮን ዶላር አስገኝተዋል።

ላቲን አሜሪካ በባህላዊ ፈጠራ ኢንዱስትሪ አራተኛዋ ናት። 124 ቢሊዮን የታክስ ገቢ ሲሰበሰብባት፣ 1.9 ሚሊዮን ሰራተኞች በዘርፉ ተሰማርተዋል። በዩኔስኮ የተመዘገቡ የ131 የአለም ቅርስ ባለቤት በመሆኗ ከቱሪዝም ጋር በተያያዙ ገቢዎችና የፈጠራ የስራ መስኮች ብዛት የጎላ ስፍራ አላት። በአለም እውቅና ያገኙ የበርካታ ደራሲያን መጻህፍት፣ የቴሌቪዥንና ሬዲዮ ተከታታይ ድራማ ምርቶች ሽያጭ በባህላዊ ፈጠራ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ልዩ ተጠቃሚ አድርገዋታል። በተለይም ብራዚልን፣ ሜክሲኮንና አርጀንቲናን።

በባህላዊ ፈጠራ ኢንዱስትሪ አፍሪካ እና መካከለኛው ምስራቅ ከመጨረሻው ደረጃ ላይ ይገኛሉ። በግርድፍ ስሌት 58 ቢሊዮን ዶላር የታክስ ገቢ እንዳስገኙም ይወሳል። ለ2.4 ሚሊዮን ሰዎችም የስራ እድል ተፈጥሯል። ጥቂት አገሮችም በሙዚቃና በፊልም ምርት ወደ አለም ገበያ እየገቡ ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ ግንባር ቀደም ተጠቃሿ ናይጄርያ ናት። ፊልም ማምረቻዋ ኖሊውድ ለሶስት መቶ ሺህ ዜጎች የስራ እድል አስገኝቷል። አገራችን በባህላዊ ፈጠራ ኢንዱስትሪ ያለችበትን ደረጃ ለማወቅም ሆነ በኤኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፍ እያስመዘገበች ያለውን ውጤት ለመረዳት የሚያስችል የተሟላ ጥናትና ምርምር እስካሁን ባለመካሄዱ በአህጉሪቷ ውስጥ ያላትን ስፍራ በወጉ ለማመልከት የሚቻል አልሆነም። ይህ ደግሞ ለወደፊቱ ችላ የሚባል አይደለም።

የአፍሪካ የባህላዊ ፈጠራ ኢንዱስትሪ ያላደገ በመሆኑም ጭምር፣ የዘርፉ የገበያ ስርአት በወጉ አልተደራጀም። ይህም ኤኮኖሚው ኢ-መደበኛ (ኢንፎርማል) እንዲሆን ተጽእኖ አድርጎበታል። በኢ- መደበኛ ባህላዊ የፈጠራ ኢንዱስትሪ ከሚታወቁት ውስጥ በመንግስት ፈቃድ ያልተገደቡ የሙዚቃና የቴያትር አቅርቦቶች፣ የመንገድ ላይ ትርኢቶች፣ ፌስቲቫሎች፣ ኮንሰርቶች፣ የሰርግ ማዳመቂያ ዝግጅቶች፣ ወዘተ.. ይጠቃለላሉ። በባህላዊ ፈጠራ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ብቅ ብቅ ያሉ እንደ ቻይናና ህንድ ያሉ የበለጸጉ አገሮችም ጭምር በኢ- መደበኛ የገበያ አካሄድ ከፍተኛ ጥቅምን እያስመዘገቡ ይገኛሉ። እነዚህ አገራት በአመት 33 ቢሊዮን ዶላር በዘርፉ ያስገቡ ሲሆን፣ 1.2 ሚሊዮን ሰዎችም ይተዳደሩበታል።

አገራት ለባህላዊ ፈጠራ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ትኩረት ከሚሰጡባቸው ምክንያቶች አንዱ፣ ዜጎች በመንግስት መስሪያ ቤቶችና ሌሎች ድርጅቶች አንጻር እየጠበበ ከሚሄደው የመቅጠር እድል ባሻገር ሌላ አማራጭ እንዲያማትሩ፣ በተለይም የግል ስራ በመፍጠር ከጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪ መስራችነት ወደ ግዙፍ ቀጣሪነት እንዲሸጋገሩ ምቹ ሁኔታ ስለሚፈጥር ነው። በካናዳ ካሉት ጨዋታ (ጌም) ፈጣሪዎችና አራማጆች መካከል 53 በመቶዎቹ በግል የሚንቀሳቀሱ ናቸው። በአሜሪካ ከሚገኘው መላው ተቀጣሪ 3.5 በመቶ በላይ የሚሆኑት በግል ስራ የሚተዳደሩ ናቸው – በተለይም አርቲስቶች።

የባህላዊ ፈጠራ ኢንዱስትሪ ማህበራዊ እሴቱ

የባህልና የፈጠራ ኢንዱስትሪ ለአንድ አገር ኢኮኖሚ ጉልህ ድርሻ ያለው ብቻ ሳይሆን፣ ለህዝብ ባህላዊና ማህበራዊ ብልጽግና የሚውል የፈካ እሴት እንዳለው ይታመንበታል። ስነጥበብ ማህበራዊ ማእቀፎችን እያነቃቃ ያለማል። ድንቅ የባህልና ስነጥበብ መሰረተ- ልማቶች የከተማ እድገትን ያፋጥናሉ። በአንዲት ምሳሌ እንመልከት – በሙዚየም። ሙዚየም መገንባት የአንድን ከተማ ልዩ ማንነት በባህላዊ ፈጠራ ለማነጽ ያስችላል። የስፔኗ ቢልቦ ከተማ ‹ጉግነሂም ሙዚየም›ን በመገንባቷ፣  የቱሪስቶች ፍሰት በስምንት እጥፍ አድጓል። በዚህም ሳቢያ ለ1,000 ቋሚ ተቀጣሪዎች የስራ እድል ተፈጥሯል። ባህላዊ የፈጠራ ኢንዱስትሪ ስራ አጥነትን በመቀነስ ረገድ ለከተማ ወጣቶችና ሴቶች ያደላል። የአውሮፓ አብዛኛው ከተሜ ተቀጣሪ እድሜው በ15 እና 29 አመት ክልል ያለ ነው። ከሌሎች ኢንዱስትሪዎች በበለጠ ለሴቶች የስራ እድል የሚፈጥረውም ይሄው ዘርፍ ነው። አንዱን መስክ በምሳሌነት ብንወስድ፣ በሙዚቃ ኢንዱስትሪ ከተቀጠሩት ውስጥ 50 በመቶዎቹ ሴቶች ናቸው።

ድንቅ የባህልና ስነጥበብ መሰረተ ልማቶች እና የባህላዊ ፈጠራ ስነጥበባት የከተማን መስህብነት ያሳድጋሉ፤ ከተሜነትን ያጎለብታሉ፣ ከባቢያዊ ማንነትንና ባለቤትነትን ይፈጥራሉ። የከተማን ህዝብ ትስስርና ወዳጅነት ያጠናክራሉ፣ የብዝሀነትን ልቦና ያፈረጥማሉ። ባኳያውም ፈጠራን በማነቃቃት ስነጥበባዊ ፈጠራን ያጎለብታሉ። የሚነደፉ የከተማ ፕላኖች፣ የሚገነቡ ህንጻዎችና አውራ ጎዳናዎች፣ የሚመረቱ የፋብሪካ ውጤቶች፣ የሚከፈቱ የመዝናኛ ስፍራዎች፣ የእለት ተለት ህይወት ማካሄጃ የቤት እቃዎች፣ እንደጌጣጌጥና አልባሳት ያሉ የሰው ልጅ መገልገያዎች ወዘተ.፣ ያለ ስነጥበባዊ የፈጠራ ክህሎት እሴታቸው በአያሌው ዝቅተኛ ነው። ፋይዳቸውም እንዲሁ።

እሴታቸው የላቀ ባህላዊና ስነጥበባዊ ምርቶች የማህበረሰቡ ጥቅል ትውስታ በመሆን ለመጪው ትውልድ የፈጠራና የምሁራዊ እሳቤ ቋት ይሆናሉ። ባህልና ስነጥበብ ከማህበረሰብ ጋር ያላቸው መስተጋብር፣ በሰው ልጅ ተግባቦትና እድገት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ የሚያሳርፍ ነው። ለዚህም ነው፣ የአውሮፓ ምክር ቤት በ1997 (እ.ኤ.አ.) የባህል ተቋማትና ስነጥበባት የሰውን ልጅ አጠቃላይ ህይወት እንደሚያሻሽሉ እምነቱን ያወጀው። ለዚህም ነው፣ በ2001 (እ.ኤ.አ.) የአውስትራሊያ መንግስትም፣ የባህልና መዝናኛ ዘርፍ በፈጠራና በራስ ገለጻ አማካይነት ለአንድ አገር ኤኮኖሚያዊ ብልጽግና ቁልፍ ሚና የሚጫወት ብቻ ሳይሆን የማህበረሰብ ህላዌ እንደሆነ ያሰመረበት።

እነዚህ የነጻ ገበያ አራማጅ አገሮች መንግስታት ከዚህ እምነታቸው በመነጨ ለባህልና ስነጥበባት እድገት ከፍተኛ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በዘርፉ ለተሰማሩት የብድር አገልግሎት በመስጠት፣ ከውጭ የሚገቡ ባህላዊና ስነጥበባዊ ግብአቶችን ከቀረጥ ነጻ በማድረግ፣ በአገር ውስጥ ለሚመረቱ የስነጥበብ ምርቶች የቀረጥ ቅነሳ በማድረግ፣ ስነጥበብን ለሚያግዙ ባለጸጋዎች የቀረጥ እፎይታን በመስጠት፣ የምርትንና የድርጅትን አቅም ለማጎልበት ብሄራዊና ክልላዊ የገንዘብ ድጎማ ቋትን በመፍጠር፣ ለዘርፉ ጥናትና ምርምር ብሄራዊና ክልልዊ በጀት በመመደብ፣ እና በሌሎች መንገዶች ልዩ ድጋፍ በማድረግ መንግስታትም ሆኑ ህብረተሰቡ እንዲጠቀም በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ይህም ሂደት ባህላዊ የፈጠራ ኢንዱስትሪ በፈጣን የእድገት ጎዳና እንዲገሰግስ እየረዳ ነው።

ማጠቃለያ

ባህላዊ የፈጠራ ኢንዱስትሪ ባህላዊ፣ ስነጥበባዊ ወይንም ቅርስ ነክ የሆኑትን ቁሳቁሶችና አገልግሎቶች ማምረትን ወይም ማባዛትን፣ ማስተዋወቅን፣ ማሰራጨትን ወይንም ለንግድ ማዋልን፣ ዋና መርሆው ያደረገ ተግባር መሆኑ ከፍ ብሎ ተገልጿል። ባህላዊ የፈጠራ ኢንዱስትሪ የአለም ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት እንደሆነም ተመልክቷል። ከሌሎች የኤኮኖሚ ዘርፎች ጋር ሲነጻጸር ከአንዳንዶቹ ልቆ መገኘቱ፣ ለአንድ አገር የሚያስገኘው የቀረጥ ገቢ ለህዝብ ብልጽግና ጉልህ ድርሻ ያለው መሆኑ፣ የስራ እድልን መፍጠሩ፣ የባህልንና ፈጠራን እድገት ማነቃቃቱ፣ ብሄራዊነትንና አለም አቀፋዊነትን መገንባቱ፣ የሰውን ልጅ የመዝናናት ጥማት ማርካቱ፣ ለተሻለ አምራችነት አእምሮንና አካልን ማዘጋጀቱ፣ ለባህላዊ ፈጠራ ኢንዱስትሪ ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግም ተጠቁሟል።

በመሆኑም፣ የሚመለከተው ሁሉ ስለባህላዊ ፈጠራ ኢንዱስትሪ ያለውን ግንዛቤ ይበልጥ በማስፋት የየድርሻውን ማከናወን ይኖርበታል። ዋና ዋና ተግባራቱም፣ እሳቤውን ለፖሊሲ አውጭዎች ማስረጽ፣ የኢትዮጵያን የባህላዊ ፈጠራ ኢንዱስትሪ ፖሊሲ መደንገግ፣ ከዚህም ጋር በተያያዘ የአገሪቱን የባህል ፖሊሲና የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ያወጣውን የባህልና የስነጥበብ መመሪያ፣ እንዲሁም የልማትና የትራንስፎርሜሽን እቅዶችን እንደገና መፈተሸ፣ የተለያዩ የአለም አገራትን ተሞክሮዎች ቀስሞና ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር አቀናጅቶ በስራ ላይ ማዋል ናቸው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top