በላ ልበልሃ

ባህላዊ ዕርቅ ለመልካም አስተዳደር ብልጽግና

መግቢያ

ባህላዊ ዕርቅ ከዘመናዊ የፍትሕ ሥርዓት አንጻር ሲመዘን

የኢትዮጵያን የፍትሐ ብሔርና የወንጀለኛ መቅጫ ሕጎችን የማዘመን ሥራ የተከናወነው በ1950ዎቹ ነው። ሕጎቹን ባረቀቁት ባለሙያ አስተሳሰብ ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶችና እነሱን የሚያጅቡት ሥልቶች፣ ብዙም የታወቁ ካለመሆናቸው በተጨማሪ፣ ለዘመናዊነት ዓላማ ተገቢነት የሌላቸው ተደርገው መቆጠራቸውን በመስኩ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች አመልክተዋል። በኢትዮጵያ የሥርዓተ ሕግ ታሪክ ውስጥ ነባር ሕግጋትን በዐዲስ የመተካት ሂደት ወቅት የሕጎች ምንጭ የነበሩት ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶች ሕልውናቸውን በይፋ ተገፈዋል። ይህንንም በ1952 ዓ.ም በሥራ ላይ የዋለው የፍትሐ ብሔር ሕግ አንቀፅ 3347 (1)፤ “ግልፅ የሆነ ተቃራኒ ድንጋጌ ከሌለ በቀር በዚህ ፍትሐ ብሔር ሕግ ውስጥ ለተመለከቱት ጉዳዮች ከዚህ በፊት በልማድ ወይም ተጽፈው ይሠራባቸው የነበሩት ደንቦች ሁሉ ይህን የፍትሐ ብሔር ሕግ ስለመተካት ተሽረዋል” በማለት ይደነግጋል። ይህ ድንጋጌ የሚሽረው ከፍትሐ ብሔር ሕጉ ጋር የማይጣጣሙትን ልማዳዊ ሕጎች ብቻ አይደለም። ከሕጉ ጋር የተጣጣሙትን ጭምር እንጂ።

በተወሰነ ደረጃ ተቀባይነት የነበራቸው ባህላዊ ሥርዓቶች የቤተሰብ ሕግ (ለምሳሌ በ2000 ዓ.ም በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ የተሻረው የቤተሰብ ዕርቅና ልጅን በጉዲፈቻ የማሳደግ ሕግ) እና በፍትሐ ብሔር ሕግ ውስጥ የሠፈረው የውርስና የዕርቅ ዳኝነትን የሚመለከተው ክፍል ነው። ሕጉን ያረቀቁት ባለሙያ ባህላዊ ሕጎችንና የፍትሕ ተቋማትን የመግፋታቸው ምክንያትም፣ “ሕግ ማለት መንግሥት ብቻ የሚያወጣው፣ ለሁሉም ሰዎች አንድ ዓይነት የሆነ፣ የተፃፈ፣ የተጠቃለለ፣ በመንግሥት አካላት የሚፈጸም እና የሚተረጎም ነው።” የሚል ፍልስፍና በመከተላቸው ይመስላል። ይህም ሆኖ፣ ባህላዊ ወይም ነባር የሆኑትን ይተካሉ ተብለው የተደነገጉት አዳዲስ ሕጎች የኢትዮጵያን ገጠራማ ክፍሎች ዘልቀው ለመግባት አልቻሉም። ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶች የማዕከላዊ መንግሥት ሕጋዊና አስተዳደራዊ ተቋማት ሥር በሰደዱባቸው በርካታ የአገሪቱ ክፍሎች ጭምር አገልግሎት መስጠታቸውን እንዳላቋረጡ ጥናቶች ይጠቁማሉ።

በ1987 ዓ.ም የወጣው የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት በተለያዩ ድንጋጌዎቹ ለብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባህላዊ ሕጎችና የፍትሕ ተቋማት ዕውቅና ሰጥቷል። ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 39 ንዑስ ቁጥር (2) ማንኛውም ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ “ባህሉን የመግለፅ፣ የማዳበርና የማስፋፋት” መብት አለው በማለት ሲደነግግ፣ ባህልን ለልዩ ልዩ ጉዳይ መጠቀም መቻሉን ይገልጻል። ባህል ከሚገለጽባቸውና ጥቅም ላይ ከሚውልባቸው መንገዶች አንዱ ባህሉ በሚፈቅደው መሠረት ግጭቶችን መፍታት መቻል ነው።

ባህላዊ ሕጎቹና የፍትሕ ተቋማቱ ዕውቅና የተሰጣቸው በሁለት ሁኔታዎች ነው። አንደኛ፣ የባህላዊ ሕጉ ሥርዓት በሕግ ተፈጻሚነት የሚኖረው፣ ተከራካሪዎች በባህላዊ ሕግ ለመዳኘት ፈቃደኛ መሆናቸው ሲረጋገጥ ነው። ይህንም፣ የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 34 ንዑስ ቁጥር (5) “በተከራካሪዎች ፈቃድ የግል እና የቤተሰብ ሕግን በተመለከተ በባህላዊ ሕጎች መዳኘት” ይችላሉ በማለት ይፈቅዳል። በዚሁ “ንዑስ አንቀጽ መጨረሻ በግልጽ እንደሠፈረው ሕገ መንግሥቱ ከመጽደቁ በፊት የነበሩና በመንግሥት ዕውቅና ያልነበራቸው ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓቶችና ተቋማት፣ አንዲሁም የሃይማኖት ፍርድ ቤቶች በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።”

ሁለተኛ፣ ባህላዊ ሕጎች በሕገ መንግሥቱ የተሰጡትን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች በአጠቃላይ የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌዎች የሚጻረሩ መሆን የለባቸውም። ይህም፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 1 “ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሠራር በመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም።” ተብሎ ተደንግጓል። ይህ አንቀጽ ሲተረጎም የሕገ መንግሥቱን ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች እስካልተጻረሩ ድረስ ግጭቶችን በባህላዊ ሕጎች መፍታት ይቻላል ማለት ነው።

ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 91 ንዑስ ቁጥር (1) “መንግሥት መሠረታዊ መብቶችን፣ ሰብአዊ ክብርን፣ ዲሞክራሲንና ሕገ መንግሥቱን የማይቃረኑ ባህሎችና ልማዶች በእኩልነት እንዲጎለብቱና እንዲያድጉ የመርዳት ኃላፊነት አለበት” በማለት ይደነግጋል። ይህም፣ ከሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 9 ጋር በሚስማማ መልኩ ባህላዊ ሕጎች እንዲጎለብቱና ሥራ ላይ እንዲውሉ የሚፈቅደው፣ የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎችና መርሆዎች በተለይም ከአንቀጽ 13 እስከ አንቀጽ 44 የተደነገጉት የሰዎች መሠረታዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መጠበቃቸው እስከተረጋገጠ ወይም እስካልተጣሰ ድረስ ነው።

ሆኖም ሕገ መንግሥቱ የባህላዊ ሕጎችንና ተቋማትን አሠራር በተመለከተ በአንቀጽ 34 (5) “ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል” የሚል ድንጋጌ ቢያስቀምጥም፣ ይህን የሚመለከት ዝርዝር ሕግ እስካሁን ባለመውጣቱ በርካታ ችግሮች መፈጠራቸው አልቀረም። ባህላዊ ሕግና ባህላዊ የፍትሕ ተቋም ማለት ምን ማለት ነው? መስፈርቶቹስ ምንድን ናቸው? ውሳኔያቸውን የሚያስፈጽመው አካልስ ማነው? አንድ ሰው በባህል መሠረት ለመዳኘት ፈቃደኛ ሆነ የሚባለው መቼ ነው? ሕገ መንግሥቱ ያስቀመጣቸው መሠረታዊ መርሆዎችና ድንጋጌዎች በባህላዊ የፍትሕ ተቋማት ተፈፃሚ መሆናቸው የሚረጋገጠው እንዴትና በምን ዓይነት ሁኔታ ነው? ወዘተ የሚሉት ጥያቄዎች መልስ አላገኙም። ይህም የሕገ መንግሥቱ ዓላማና ፍላጎት የተገደበ እንዲሆን አድርጎታል። (የፍትሕና የሕግ ሥርዓት ምርምር ኢንስቲትዩት፣ 2007፤ 50)።

የኢፌዲሪን ሕገ መንግሥት አንቀጽ 9 (1) ባገናዘበ መንገድ የባህላዊ ፍትሕ ሥርዓቶች አተገባበር ከመደበኛው ፍርድ ቤት ጋር እንዴት ይነጻጸራል? ፍትሕን ከማስፈንና ዘላቂ ሰላምን ከመፍጠር አንጻርስ እንዴት ይገመገማሉ? ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ መስጠት አስፈላጊ ነው።

ባህላዊው የግጭት መፍቻ ሽምግልና ከመደበኛው ፍርድ ቤት ጋር ሲነፃፀር:-

1)የሽምግልናው አሠራር ከመደበኛው ፍርድ ቤት እጅግ በቀለጠፈና በተሻለ መንገድ ግጭቶችን የመፍታትም ሆነ ባለመብትነትን የማረጋገጥ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ ይታመናል።

2) የሽምግልናው አሠራር ከመደበኛው ፍርድ ቤት ጋር ሲነፃፀር ወጪን ይቀንሳል። ለዳኝነት መክፈል የማይችል ሰው አስመስክሮ ፋይል ለመክፈት ቢችልም እንኳ ፍርድ ቤቱ ወደሚገኝበት ቦታ በቀጠሮ ሲመላለሰ ለመጓጓዣና ለስንቅ ገንዘብ ያስፈልገዋል። በተለይም ክርክሩ በይግባኝ ከመኖሪያ አካባቢው ራቅ እያለ ሲሄድ የሚጠይቀው የገንዘብ ወጪ ከፍተኛ ነው።

3) የመደበኛው ፍርድ ቤት አሠራር እውነቱን ፈልፍሎ በማውጣት ረገድ የሽምግልናውን ያህል ጉልበት የለውም። መደበኛው ፍርድ ቤት የሰነድ ማስረጃ ወይም የሰው ምስክር ማቅረብ ባልተቻለባቸው ጉዳዮች ከሳሽን ባለመብት የሚያደርግ ውሳኔ አይሰጥም። ሽማግሌዎች ግን በማግባባት ወይም በመሐላ ማስረጃ በቀላሉ የማይገኝለትን ድርጊት ፈጽሟል የተባለን ሰው ያሳምናሉ። ባለጉዳዮቹም በግልግል ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ያደርጋሉ።

4) ባህላዊው የዳኝነትሥርዓት ከመደበኛው ፍርድ ቤት በተሻለ ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር ያስችላል ተብሎ በተገልጋዮች ዘንድ ይታመናል። ሽምግልና፣ የተጣሉትን ሰዎች ችግር በዘላቂነት ሲፈታ ፍርድ ቤት ግን የተጣሉ ሰዎች ከጠብ ነጻ እንዲሆኑ አያደርግም።

ባህላዊ ዕርቅ ከተፈጸመ በኋላ በዘላቂነት እንዲጸና ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ እሴቶች አሉ። ከእሴቶቹ መካከልም በኅብረተሰብ መገለልን መፍራትና ዕርቁን ለማክበር መስቀል መትቶ ወይም ባህሉ በሚፈቅደው መሠረት መሀላ መፈጸም የሚሉት ይጠቀሳሉ። ይህንን በተመለከተ የሻክቾ ብሔረሰብን የግጭት አፈታት ሥርዓት ያጠኑት ስለሺ አባተ (2004፤ 82) የገለጹትን እንመልከት።

“እርቅ የፈፀሙ የብሔረሰቡ አባላት ዳግመኛ ወደ ግጭት እንዳይገቡ ቀድመው የሚፈጽሟቸው መሀላዎች ስላሉ ደግመን ከተጋጨን መሀላው ይደርስብናል በሚል ሥጋት ተመልሰው አይጋጩም። አጥፍተው ከተገኙም ቀድሞ ዕርቅ ሲፈፅሙ በጠሯቸው ዋሶች በኩል ለሽማግሌዎች የገቡትን ቃል እንዲያከብሩና እንዲፈጽሙ ይፈረድባቸዋል። ስለሆነም፣ ሁለቱም ወገኖች ከቅጣቱ ለማምለጥ ሲሉ ተበዳይ ሆነው እንኳ ከመጋጨት ይታቀባሉ። መቀጣታቸው ብቻም ሳይሆን ማኅበረሰቡም ከተለያዩ ማኅበራዊ ሕይወቶች እንደሚያገልላቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ። በመሆኑም፣ እነዚህ የብሔረሰቡ ባህላዊ የዕርቅ መፈፀሚያ ተቋማት በብሔረሰቡ ውስጥ ዘላቂ የሆነ ሰላም ለመፍጠር የቻሉና ተቀባይነትም ያላቸው ናቸው ማለት ይቻላል።”

የባህላዊ ዕርቅ ምንነትና ሂደት

ኢትዮጵያውያን የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን፣ ማህበራዊ ግኝኙነታቸውን፣ ኢኰኖሚያዊ እንቅስቃሴያቸውን፣ በአጠቃላይ ሕይወታቸውን ሲመሩ የኖሩት በአብዛኛው በራሳቸው ባህላዊ እሴትና ሥርዓት ነው። የጋራና የተናጠል የባህል እሴቶቻቸው አገልግሎት ለትናንት የአኗኗር ሥርዓት ብቻ ሳይሆን ለዛሬም ምርኩዝ ናቸው። የባህል እሴቶች የሚሰጡትን ልዩ ልዩ አገልግሎት በወጉ ለመረዳት በተገቢው መንገድ ማጥናት ያስፈልጋል። የእያንዳንዱን ብሔርና ብሔረሰብ ባህላዊ ሕጎችና የፍትሕ ተቋማትን ማጥናት መልካም አስተዳደርን ለማበልጸግና ልማትን ለማምጣት የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው ተብሎ ይታመናል። በዚህ ጽሑፍ ትኩረት የተደረገው ሥነ-ቃል በባህላዊ የዕርቅ ሥርዓት ውስጥ ባለው አዎንታዊ ሚና ላይ ነው።

በአንድ ኅብረተሰብ ውስጥ ግጭትን ስለመቆጣጠርና ማስወገድ የሚነገሩትን ምሳሌያዊ ንግግሮች፣ ተረቶች፣ ቃል ግጥሞች፣ አፈ-ታሪኮች፣ ምርቃኖች /ርግማኖች፣ መሀላዎች እና ሌሎችንም ማጥናት የኅብረተሰቡን አመለካከትና ግጭቶችን የሚፈታበትን መንገድ ለመረዳት ያስችላል። ባህላዊ የግጭት መፍቻ ሥርዓቶች እንዴት እንደተመሠረቱ የሚነገሩት አፈ-ታሪኮች ሥርዓቶቹን በኅብረተሰቡ ውስጥ ለማስረጽና ለመትከል ከፍተኛ ሚና አላቸው። የሽማግሌዎችን ሀቀኝነት፣ እውነተኛነትና የዕርቅን አስፈላጊነት አስመልክቶ የሚፈጸሙት መሀላዎችና ምርቃኖችም ዕርቁን ስኬታማ ለማድረግ ያስችላሉ።

ስለ ባህላዊ ዕርቅ አመጣጥ የሚነገሩ አፈ-ታሪኮች

ባህላዊ ሕጎችና የፍትሕ ተቋሞች መነሻ ምክንያት አላቸው ወይም ነበራቸው ተብሎ ይታመናል። ሆኖም በአንዳንድ ኅብረተሰብ ባህላዊ ሕጎችና የፍትሕ ተቋማት መነሻ ምክንያት ወይም አጀማመር ከትውልድ ወደ ትውልድ በቃል ሲተላለፍ የነበረው አፈ-ታሪክ በጊዜ ሂደት እየተረሳ መምጣቱን በመስኩ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች (ለምሳሌ ዮሐንስ ብርሃኑ፣ 1998) ያመለክታሉ። አንዳንድ አጥኝዎች ባህላዊ ዕርቅ ከሰው ልጅ ማኅበራዊ ሕይወት ጋራ አብሮ የተፈጠረ ነው ሲሉ፣ ሌሎቹ ደግሞ (ለምሳሌ አበራ ጀምበሬ፣ 1990) ባህላዊ ሕጎች ከክርስትና ወይም ከእስልምና እምነት እንደመነጩ ይገልጻሉ።

ባህላዊ ዕርቅ ከትውልድ ወደ ትውልድ በቃልና በተግባር ሲተላለፍ የመጣ፣ በኅብረተሰብ ባህላዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኰኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ግንኙነቶችና እንቅስቃሴዎች የሚፈጠሩ አለመግባባቶችንና ግጭቶችን ለመፍታት የሚያስችል ሥርዓት ነው። ባህላዊ የዕርቅ ሥርዓት በኅብረተሰቡ በተግባር እየተፈተነ፣ እየተሻሻለና እየጎለበተ አገልግሎት ይሠጣል። በተወሰነ ቦታና ጊዜ የሚከናወን፣ የተፃፈ ሕግ የሌለው፣ በኅሊና ሚዛን የሚዳኝና በውዴታ ግዴታ የሚፈፀምም ነው።

በብዙዎቹ የአገራችን አካባቢዎች በባልና ሚስት፣ በቤተሰብ፣ በግለሰብ፣ በጎረቤት፣ በማኅበረሰብ መካከል የሚፈጠሩና ከቀላል እስከ ከፍተኛ ደረጃ የሚደርሱ አለመግባባቶችንና ግጭቶችን በአገር ሽማግሌዎች ወይም በጎሳ መሪዎች ወይም በሃይማኖት አባቶች ለመፍታትና ዘላቂና ሰላማዊ ግንኙነትን ለመፍጠር የሚያስችል እጅግ ጠንካራ መሠረት አላቸው። በዚህ ዘዴ ግጭትንና አለመግባባትን መፍታት በመንግሥት በተጻፈ ሕግ ከመዳኘትና ከመመራት የበለጠ ቦታ እንዳለው ይታመናል።

በአንድ ኅብረተሰብ ውስጥ የባህላዊ ዕርቅ ሂደትና፣ በዕርቁ ላይ የሚሳተፉት ሽማግሌዎች ቁጥርና ማኅበራዊ ደረጃ እንደ ግጭቱ መቅለልና መክበድ ይለያያል።

የአስታራቂ ሽማግሌ አመራረጥ ሂደት

“ዕርቅ የፈለገን ንጉሥ ገበሬ ያስታርቀዋል፤ ዕርቅ ያልፈለገን ገበሬ ንጉሥ አያስታርቀውም” እንደሚባለው፣ ግጭት ውስጥ የገቡ ሰዎች ለመታረቅ ፈቃደኛ መሆን ይኖርባቸዋል። ግጭት ውስጥ የገቡ ሰዎች ወደ ዕርቅ የሚመጡትና አስታራቂ ሽማግሌ የሚመርጡት አንድም ግጭት መፈጠሩን ያወቀ ቤተሰብ፣ የቅርብ ጓደኛ ወይም ዘመድ ወይም የአገር ሽማግሌ ወይም ማኅበርተኛ ወይም ጎረቤት የ“ታረቁ” ጥያቄ ሲያቀርብ ነው። አንድም በዳይ በተበዳይ ላይ የፈጸመውን በደል ገልጾ ለአገር ሽማግሌ/ ዎች የአስታርቁኝ ጥያቄ ሊያቀርብ ይችላል።

የዕርቅ ጥያቄው ከራሱ ካልመጣ፣ ተበዳይ ለቀረበለት የዕርቅ ጥያቄ ወዲያውኑ ፈቃደኛ ላይሆን ይችላል። ነገር ግን የ“ታረቅ” ጥያቄ ካቀረቡ ሽማግሌዎች አፈንግጦ አይቀርም። አብዛኛውን ጊዜ የ“ታረቅ” ጥያቄ የሚቀርበው ግጭቱ ከሮ የከፋ ደረጃ ከመድረሱ ወይም ተጨማሪ ጉዳት ከማስከተሉ ወይም ጉዳዩ ወደ ፖሊስ ጣቢያና ፍርድ ቤት ከመሄዱ በፊት ነው። ግጭቱ ከሮ በንብረትና በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት ከደረሰም በኋላ ሽማግሌ የ“ታረቁ” ጥያቄ የሚያቀርብበት አጋጣሚ አለ። ተበዳይ የ“እሽታ” ቃል እንደሰጠ ዳኛው ሁለቱ ወገኖች የሚስማሙባቸውን ሽማግሌዎች እንዲመርጡ ያደርጋል። ዕርቁ የሚፈጸምበትን ቦታና ቀንም ይወስናሉ።

የመሐል ዳኛ ሆኖ የሚመረጠው ሽማግሌ የሁለቱንም ወገኖች በአንድ ዓይን ይመለከታል ተብሎ የሚታመንበት ይሆናል። ሽማግሌ ዳኛ እንዲሆን የሚመረጠው ሰው ብዙ ጊዜ ማንበብና መጻፍ የሚችል ነው። ካልተገኘ ግን መጻፍ ባይችልም ባስተዋይነቱና በታማኝነቱ የተሻለ ነው የሚባል ሰው ይመረጣል። ለዚህም ነው “ዳኛ አውጥቼ ዘንግ አቅንቼ” የሚባለው።

ሽማግሌ የመምረጡ ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ የተሸማጋዮቹ ነው። በአንደኛው ወገን የሚመረጡት ሽማግሌዎች በሌላኛው ወገን ተቀባይነት ማግኘት አለባቸው። የሚመረጡት ሽማግሌዎች ማኅበራዊ ቦታና ብዛት እንደ ጸቡ መቅለልና መክበድ ይለያያል። ሁለቱም ወገኖች እኩል ቁጥር ያላቸውን ሽማግሌዎች ይመርጣሉ። የሽማግሌዎች ቁጥር አምስት ወይም ሰባት፣ ወይም እንደ ሁኔታው ከዘጠኝ እስከ አስራ አምስት ሊደርስ ይችላል። አስታራቂ ሽማግሌዎች በኀብረተሰቡ እምነት ካተረፉ በኋላ “አናስታርቅም” ወይም “ጊዜ የለንም” ማለት አይችሉም።

ሽማግሌ መምረጫ መመዘኛዎች

አስታራቂ ሽማግሌ ሆኖ ለመመረጥ በሀብቱ የደረጀ፣ በማኅበራዊ ከበሬታው ከፍ ያለ፣ በአስተዋይነቱና በዐዋቂነቱ የተመሰገነ መሆን ይኖርበታል። በሽማግሌነት የተመረጠ ሰው ባለ ሀብት ከሆነ መደበኛ የግብርና ሥራውን በቤተሰቡ ወይም ሠራተኛ ቀጥሮ በማሠራት በሽምግልናው ሥራ ሊሳተፍ ይችላል። ሀብታም በመሆኑ ማኅበራዊ ደረጃው ከፍ ስለሚል ቢናገር ይደመጣል፣ ይከበራል። የነገር ብልት የማያውቅ፣ ተገቢውን ውሳኔ የማይሰጥ፣ አድሎ የሚፈጽም ሰው ሀብት ቢኖረውም በሽማግሌነት አይመረጥም።

እንዲህ ያለው ሽማግሌም “ፍርድ አያውቅ ዳኛ፣ ተገን አያውቅ እረኛ” እየተባለ ይተቻል። ፍርድ የማያውቅ ዳኛ ተገቢውን ፍርድ በመስጠት ችግሩ እንዲወገድና ጠበኞቹ ዘላቂና ሰላማዊ ግንኙነት እንዲመሰርቱ አያደርግም። ውሽንፍር ያጋጠመው እረኛም መጠለያ ፈልጎ ራሱን መከላከል ካልቻለ ሊጎዳ ይችላል።

የአገር ሽማግሌ ሆኖ ለመመረጥ መማር ወይም አለመማር ወሳኝነት የለውም። “መንደር ከዋለ ንብ፣ አደባባይ የዋለ ዝንብ” እንደሚባለው በተፈጥሮ ያገኘውን አስተዋይነትና ችሎታ በተገቢው ልምድና ክህሎት ማዳበር የቻለ ሰው በአገር ሽማግሌነት ይመረጣል። ስለዚህ አንድ ሰው ሽማግሌዎች ሲያስታርቁ በማየት ልምድ ሊያገኝ ይችላል። ከዚህም በላይ፣ በተለያዩ ባህላዊ የዕርቅ ሥርዓቶች ላይ በመሳተፍ ችሎታውን ያሳየ፣ ልምዱን ያዳበረና እውነተኛነቱን ያስመሰከረ ሰው በሽማግሌነት ይመረጣል።

አብዛኛውን ጊዜ የሚመረጡት ሽማግሌዎች የዕድሜ ተሞክሮ ያላቸው ናቸው። አንድ ሽማግሌ የዕድሜ ባለጸጋ ከመሆን በተጨማሪ ማኅበራዊ ችግሮችን በጥንቃቄ ለመፍታት የሚያስችል ዕውቀትና ልምድ ያለው፣ የነገሮችን ብልት ለይቶ ውስብስብ ችግሮችን ለመፍታት የሚችል፣ ሁለገብ ዕውቀት ያለው፣ ፍርድ ዐዋቂና ምስጢር በመጠበቅ ባህላዊ ዕርቁን ለማከናወን የሚችል መሆን አለበት።

የባህላዊ ዕርቅ ድርድር ሂደት

ባህላዊ ዕርቁ የሚካሄድበትን ቀንና ቦታ በግጭቱ ውስጥ የነበሩት ወገኖች ተስማምተው ለሽማግሌ ዳኛቸው ይነግራሉ። ቦታው በትልቅ ዛፍ ሥር ወይም በቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ወይም በወንዝ ዳር ሊሆን ይችላል። ዕርቅ የሚፈጸምበት ቀን እንደ ኅብረተሰቡ እምነትና የኑሮ ሥምሪት የተለያየ ነው። በኅብረተሰቡ እምነት መሠረት ዕርቅ ይሠምርባቸዋል የሚባሉ ቀናት ይመረጣሉ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና እምነት ተከታዮች በሚበዙባቸው አካባቢዎች፣ ዕርቅ የሚፈጸመው ከሥራ ቀናት ውጪ ቅዳሜ ወይም እሑድ ወይም በአካባቢው በሚከበር የበዓል ቀን ነው።

ባህላዊ ዕርቁ በሚካሄድበት ቦታ፣ በሽማግሌ ዳኛው ሰብሳቢነት ሽማግሌዎች መደዳውን በተደረደረ ድንጋይ ወይም እንጨት ላይ ይቀመጣሉ። በዳይና ተበዳይ በሽማግሌዎቹ ፊት ለፊት ይቀመጣሉ። የዕርቁ ሂደት እንደተጀመረ፣ በዳይና ተበዳይ በሽማግሌዎቹ ፊት ለፊት ለመቀመጥ የሚችሉት ግጭታቸው ቀላል ከሆነ ነው። ግጭታቸው ከባድ ከሆነ በዕርቁ ሂደት እንዳይጋጩ በዳይና ተበዳይ ተራርቀው እንዲቀመጡ ይደረጋል። ወደ ሽማግሌዎቹ የሚቀርቡት በየተራ ሲሆን ቀድሞ የሚመጣውም ተበዳይ ነው።

የዕርቁ ድርድር ከመጀመሩ በፊት ሽማግሌው ዳኛ ሁለቱም ወገኖች ዋስ እንዲጠሩ ያደርጋል።ይህ የሚሆንበትም ምክንያት ሽማግሌዎች የሚሰጡትን ውሳኔ ለማስፈጸም ከባለጉዳዮቹ በተጨማሪ ዋስ የሆነው ሰው ኃላፊነት እንዲወስድ ለማድረግ ነው።

ተበዳይ “ሰው አይወድም በደል፣ በሬ አይወድም ገደል እንደሚባለው” ብሎ በመጀመር የደረሰበትን በደል ለሽማግሌዎች ያስረዳል። ተበዳይ በደሉን በሚዘረዝርበት ጊዜ ተከሳሹ እንዲያዳምጥ ይደረጋል። ተበዳይ በደሉን ለሽማግሌ ሲያስረዳ፣ እንዲሁም ተከሳሽ ራሱን ሲከላከል ጣልቃ ገብቶ መናገር አይቻልም። ጣልቃ እየገባ ሐሳቡን ለመግለጽ የሚሞክር ካለ የሽማግሌ ዳኛው ወይም ከአስታራቂ ሽማግሌዎች አንዱ ይከለክለዋል። ሽማግሌዎችም ተበዳይ በደሉን አፍስሶ እስኪጨርስ በዳይም ራሱን ተከላክሎ እስኪያበቃ ጣልቃ አይገቡም። ከጨረሱ በኋላ ግን ዳኛውን አስፈቅደው ግልጽ መሆን በሚገባቸው ነጥቦች ላይ ማብራሪያ ሊጠይቁ ይችላሉ። ተበዳይ በደሉን ለሽማግሌ በሚያሰማበት ወቅት በዳይ ራቅ ብሎ እንዲቀመጥ የሚገደድበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ከዚያ በኋላ በዳይ ተጠርቶ የቀረበበት የበደል ክስ ይነገረውና እምነት ክህደቱ ይጠየቃል።

“የባህላዊ ዕርቅ ሥርዓት ፍትሕን ያስገኛል። የዘር፣ የሃይማኖት፣ የፆታ፣ የሃብት ወዘተ. ልዩነት ሳይደረግ ሚዛናዊ የሆነ የዳኝነት አገልግሎት የሚገኝበት ሥርዓት ነው ተብሎም ይታመናል።

በመቀጠል ሁለቱም ወገኖች በተለያየ ቦታ ራቅ ብለው ይቀመጡና ሽማግሌዎች ለብቻቸው የምክክር ቆይታ ያደርጋሉ። በዳይ ባቀረበው፣ ተከሳሽ ባመነው ወይም በካደው ወይም በመከላከያ ሐሳቡ ላይ ይወያያሉ። እያንዳንዳቸው የተናገሩትን ይመረምራሉ፤ ይተነትናሉ። መጠየቅ ያለባቸው ነገር ካለም ሁለቱንም በየተራ እየጠሩ እንደገና ያነጋግራሉ፤ ይመረምራሉ።

ጉዳዩን በዚህ መልክ ካጣሩ በኋላ ተበዳይ ምን ያህል እንደተበደለ፣ በዳይም ምን ያህል እንደበደለ ይረዳሉ። ባለጉዳዮችን ፊት በተናጠል፣ ቀጥሎ አንድ ላይ ጠርተው የማስማሚያ ሃሳባቸውን ያቀርባሉ። በዚህ ሂደት ተበዳይ ከተፈጸመበት በደል አንዳንዱን በይቅርታ እንዲተው ያግባባሉ። ለበዳይም የፈጸመውን በደል መጠንና ጥፋተኛነቱን ያስረዳሉ። በዚህም የውሳኔ ሐሳባቸው በሁለቱም ወገኖች ተቀባይነት እንዲኖረው ያደርጋሉ። ሁለቱ ተሸማጋዮችም ቀደም ብለው የተስማሙበት ውሳኔ ሲነገራቸው መቀበላቸውን ይገልጸሉ።

በሁለቱም ወገኖች የተፈጸመው ጥፋት ተመጣጣኝ ነው ተብሎ በሽማግሌዎቹ ከታመነ ዕርቁ “አንተም ተው፣ አንተም ተው” በማለት “ማረኝ” “ማረኝ” እንዲባባሉ ይደረጋል። በዳይ በተበዳይ ላይ አደረሰ የተባለው በደል ቀላል መሆኑ ከተረጋገጠ ደግሞ፣ ተበዳይ የተፈጸመበትን በደል “ይቅር ለእግዚአብሔር” በማለት እንዲተው ይደረጋል። ዕርቁ የተፈጸመው በዳይ ለተበዳይ ተመጣጣኝ ካሣ ሰጥቶ ከሆነም የዕርቁ ስምምነት ለታራቂዎቹና ለዋሶቻቸው ይነገራል። በዳይ ለተበዳይ የሚከፍለው የካሣ መጠንና የሚከፍልበት ጊዜ ይነገራቸዋል። በአጠቃላይ የዕርቁ ስምምነት ይጻፍና ሁለቱም እንዲፈርሙበት ይደረጋል። ዳግም ወደ ግጭት እንዳይገቡም ይመከራሉ፤ ይመረቃሉ።

በመጨረሻ በሽማግሌዎቹ ጥያቄ መሠረት በዳይ ድንጋይ ተሸክሞና ጎንበስ ብሎ ተበዳይን “ይቅር በለኝ” ይላል። ተበዳይ በበኩሉ በዳይ የተሸከመውን ድንጋይ አንስቶ መሬት ላይ ይጥልና “ይቅር ብየሃለሁ፣ ይቅር ለእግዚአብሔር” ይለዋል። በመቀጠል በዳይና ተበዳይ እንዲሳሳሙ ሽማግሌዎቹ ይጠይቃሉ። በእድሜ የሚያንሰው ወገን ወደ ሌላኛው ጉልበት ዝቅ በማለት ይስማል። በዕድሜ የሚበልጠው ወገንም ያጎነበሰው ሰው ወደ ጉልበቱ ከመድረሱ በፊት ቀና አድርጎ ይስመዋል። በዳይና ተበዳይ በዕድሜ እኩያ ከሆኑ ጉንጭ ለጉንጭ ወይንም ትከሻ ለትከሻ በመነካካት ይሳሳማሉ።

በመቀጠል ሽማግሌዎች በየተራ እንዲመርቁ ይደረጋል። በባህላዊ ዕርቁ ላይ ቄስ ወይም የቤተክሕነት ትምህርት ያለው ሰው ካለ ዕርቁን በአቡነ ዘበሰማያት ያሳርጋል። ከዚህ በኋላ በዳይና ተበዳይ እንዲታረቁ የደከሙት ሽማግሌዎች የተዘጋጀውን መብልና መጠጥ ይጋበዛሉ። መብሉና መጠጡ የሽማግሌዎችን ድካምና ጦም መዋል በማሰብ ብቻ ሳይሆን “አብሮ የበላን ቅዱስ ዮሐንስ አይሽረውም” የሚለውን ባህላዊ እምነት ለመፈፀምም ነው። የተጣሉት ወገኖች አንድ ማዕድ ላይ መቁረሳቸው፣ ከአንድ እንስራ ወይም ማንቆርቆሪያ የተቀዳን ጠላ ወይም ቡቅሬ መጠጣታቸው ያቀራርባቸዋል ስለሚባል ያንኑ ለመተግበርም ነው።

የደም ካሣ ሽምግልና ሂደት

ሰው የገደለን ወይም ከፍተኛ የአካል ጉዳት ያደረሰን ሰው ከተበዳይ ወይም ከሟች ቤተሰቦች ጋር ለማስታረቅ የሚደረገው እንቅስቃሴና የሽምግልና ሂደት፣ ቀደም ሲል ከተገለጸው የዕርቅ ሥርዓት በአንዳንድ ሁኔታዎች ይለያል። በአንዳንድ አካባቢዎች አንድ ሰው የግድያ ወንጀል መፈጸሙ እንደታወቀ፣ የቅርብ ዘመዶቹ ከሟች ዘመዶች ጋር ዕርቅ ይጠይቃሉ። የዕርቁ ዓይነት የባድማ ወይም የፈሪ ዕርቅ ይባላል። የዕርቁ ዓላማ የገዳይ ዘመዶች ቀደም ሲል በሚኖሩበት አካባቢ ሥራቸውን እያከናወኑ ለመኖር እንዲችሉ ማለትም የሟች ዘመዶች እንዳይበቀሏቸው ለማድረግ ነው።

የተበዳይ ቤተሰብ ወይም ተበዳይ በአንድ ሽማግሌ ወይም አማላጅ ብቻ እንዲታረቅ አይጠየቅም። ሽማግሌዎች መስቀልና የቤተክርስቲያን ጥላ ይዘው ተበዳዩ ዘንድ ደጋግመው በመሄድ ለመታረቅ ፈቃደኛ እንዲሆን ያግባባሉ። በአንዳንድ አካባቢ የ“ታረቁ” ጥያቄውን የሚያቀርበው የጎሳ መሪ ወይም የሃይማኖት አባት ሊሆን ይችላል። ተበዳይ ለመታረቅ ፈቃደኛ የሚሆነው ከተደጋጋሚ ጥያቄና ድካም በኋላ ነው። በዳይ የአስታርቁኝ ጥያቄ የሚያቀርበው፣ ሽማግሌ የሚመርጠውና የዕርቁን ቦታና ቀን የሚወስነው በተወካዩ (በፈጁ) አማካይነት ነው።

የዕርቁ ድርድር ለረጅም ጊዜ ከተካሄና ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ ሁለቱም ወገኖች ሽማግሌዎች ወዳሉበት በመምጣት ይቅር እንዲባባሉ ይደረጋል። ዕርቁን ለማጽናት ያስችላሉ የሚባሉ ተግባሮች እንደየ አካባቢው ይትባህል፣ ለምሳሌ የሟችን እናት ጡት በመጥባት፣ ጠመንጃ በመዝለል፣ አንዱ በሌላው እጅ በመብላት ወዘተ. ይፈጸማሉ።

ነፍሰ ገዳይ የሚከፍለው የካሣ መጠን ግድያውን እንደፈጸመበት ምክንያት ወይም ከግድያው በኋላ በአስከሬኑ ላይ እንደፈጸመው ድርጊት ሊጨምር ወይም ሊቀንስ ይችላል። በአንዳንድ አካባቢዎች የተወሰነበትን የደም ካሣ ለመክፈል ያልቻለ ሰው በቅርብም በሩቅም ከሚኖሩ ዘመድ ወዳጆቹ የገንዘብ ድጋፍ ይጠይቃል። በዚህ መንገድ የተገኘው ገንዘብ ካልበቃው ደግሞ እጁን በሰንሰለት አስሮ ሰው በሚሰበሰብበት ቦታ (በደብር፣ በማኅበር፣ በገበያ፣ በሠርግ፣ በለቅሶ ወዘተ.) ሁሉ በመገኘት ያጋጠመውንና የፈጸመውን ድርጊት በማስረዳት ይረጠባል። ሰንሰለቱ ሰው በእጁ እንደጠፋበትና የደም ካሣ እንዳለበት ስለሚያስረዳ ሁሉም የቻለውን ያህል ይሰጣል።

በአንዳንድ አካባቢ ደግሞ የደም ካሣውን የሚከፍለው የገዳይ ጎሣ ይሆናል። በተለይም ጎሣን መሠረት ያደረገ ማኅበራዊ ግንኙነትና ዝምድና ባላቸው

ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የደም ካሣ የሚከፈለው ከገዳይ ጎሣ አባላት ተዋጥቶ ነው። የበደል ካሣው የሚከፈለው በዓይነት ነው (ብዛት ያለው ከብት ወይም ግመል ወይም ፍየል)። የጎሣው አባላት አዋጥተው የሚከፍሉበት አንዱ ምክንያት የአንድ ጎሣ አባል የሆነ ሰው የሌላን ጎሣ አባል ቢገድል፣ ደም የሚበቀሉት የሟች ጎሣ አባላት ማንኛውንም የገዳይ ጎሣ አባል በመግደል ስለሆነ ነው።

በዕርቁ ፍጻሜ ላይ የሚደረግ ምርቃንና የምሥጋና ጸሎት

ዕርቁ የሚጠናቀቀው፣ ሽማግሌዎች ለፈጣሪያቸው በሚያቀርቡት የምሥጋና ጸሎት ነው።

የምሥጋና ጸሎቱም፣ ፈጣሪያቸው ፈቅዶ የሽምግልና ሥራቸውን ስላስጀመራቸውና ስላስፈጸማቸው፣ በተጣሉት ሰዎች ልቦና አድሮ የሽማግሌዎቹን የዕርቅ ሐሳብ እንዲቀበሉና እንዲፈጽሙ ፈቃደኛ ስላደረጋቸው ነው። ተበዳይና በዳይ ሽማግሌዎች ያቀረቡላቸውን የማስማሚያ ሐሳብ ተቀብለው በመታረቃቸው ይመረቃሉ። “እናንተ እኛን ሰምታችሁ፣ እናንተ እኛን ‘አድክመናችኋል’ ብላችሁ ስለታረቃችሁልን እናመሰግናችኋለን፤ ተባረኩ። እንደኛ ደሞ ተቀምጣችሁ አስታርቁ” ተብለውም ይሞገሳሉ።

የባህላዊ ዕርቅ ሥርዓት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ያለው ሚና

ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓት በኅብረተሰቡ ውስጥ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት የሰጠና ተቀባይነት ያለው በመሆኑ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ተቀባይነቱ የሚመነጨውም አንደኛ፣ በሽምግልናው የሚሳተፉት ሰዎች በኅብረተሰቡ ዘንድ ተሰሚነትና ታማኝነት ያላቸው መሆኑ ነው። ሽምግልናቸውም ፈሪሐ እግዚአብሔር ወይም አላህ ያለበት ነው ተብሎ ይታመናል። “ፍርድ ለልጅ፣ ጥርብ ለደጅ” እንደሚባለው በአድሎ ቢፈርዱ ጡሩ በልጅ ላይ ይደርሳል ተብሎ ስለሚታመንም ነው። ሁለተኛ፣ ሽማግሌዎች ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን መስዋዕት በማድረግ ተበዳይንና በዳይን ለማስታረቅ ጥረት የሚያደርጉት የተለየ ጥቅም ለማግኘት ሳይሆን፣ ግጭት ውስጥ የገቡትን ሰዎችና ቤተሰቦቻቸውን በማስማማት ሰላማዊ ግንኙነታቸውንና ኑሯቸውን እንዲቀጥሉ ለማድረግ ነው። ሦስተኛ፣ በዕርቁ ሂደት ተበዳይና በዳይ የሽማግሌ ዳኛና ሽማግሌዎች በመምረጥና በሚሰጠው ውሳኔ ቀጥተኛ ተሳታፊ ናቸው።

ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓት በባሕርይው መልካም አስተዳደርና ሥነ- ምግባር የሚፈጽማቸውን ተግባሮች ለመፈጸም ያስችላል። ይኸውም፣

1) ግልጽነት (transparency):- የሽማግሌዎቹ የዕርቅ ውሳኔ አሰጣጥ በዳይና ተበዳይን በግልጽ በሚያሳውቅ አሠራር ላይ የተመሠረተ ነው። ሽማግሌዎቹ የተበዳይን በደል፣ የበዳይን ሐሳብ ካዳመጡና ከተረዱ በኋላ፣ የውሳኔ ሐሳባቸው ምን ሊሆን እንደሚችል ለሁለቱም ወገኖች ግልጽ ያደርጋሉ። በሽማግሌዎቹ የውሳኔ ሐሳብ ላይ በዳይና ተበዳይ ጥያቄዎች ወይም ቅሬታዎች ካሏቸው ተገቢውን ማብራሪያ ይሰጣሉ።

2) አለማዳላት (impartiality)፡- ለሽምግልና የተመረጡት ሰዎች ተበዳይንና በዳይን በእኩል ዐይን በማየት በመካከላቸው የተፈጠረውን ግጭት ለመፍታት ጥረት የሚያደርጉ ናቸው። በሽምግልና የተቀመጠ ሰው በሥጋ ዝምድና፣ በሃይማኖት፣ በዘር ወይም በሌላ ምክንያት አድሎ ከመፈጸም የፀዳ ሥራ ይሠራል ተብሎ ስለሚታመን፣ ዕርቁ ተቀባይነት እንዲኖረው ያስችላል።

3) ታማኝነት (loyality)፡- ታማኝነት የሚለው ቃል፣ የሽምግልና ሥራን ለመሥራት ፈቃደኛ የሆኑበትን ቃል መጠበቅ ወይም ማክበር፣ ለባህላዊ የዕርቁ ሥርዓትና ሕግ ታማኝ መሆንን ይገልጻል። በአንድ ባህላዊ የዕርቅ ሥርዓት ላይ የሚሳተፍ የሀገር ሽማግሌ ለተበዳይና ለበዳይ እንዲሁም አብረውት ለሚሠሩት ሽማግሌዎች ታማኝ ነው። ከሽማግሌዎቹ መካከል ትክክለኛ ያልሆነ መንገድ የሚከተል ቢኖር በግልጽ ይቃወማል ተብሎ ይታመናል።

4) ቅንነት (integrity)፡ – በሽምግልና ሥራ የሚሳተፉ ሰዎች በመጀመሪያ ሰብዕናቸው የተስተካከለ፣ በተመረጡበት ሽምግልና ኃላፊነታቸውን መወጣት የሚችሉ ናቸው። ከሁለቱም ወገኖች ጋር ያላቸው ግንኙነት በትክክለኛ ሥነ-ምግባር ላይ የተመሠረተ ነው። የሽምግልና ሥራቸውንም በጥንቃቄ፣ በሙሉ ጉልበትና በብቃት ይወጣሉ ተብለው የሚታመኑ ናቸው። ሥርዓቱም አንዱ ለሌላው አክብሮት የሚሰጥበት፣ ከጥላቻና ከስሜታዊነት የጸዳ አሠራር የሚከተሉበት ነው። የሽማግሌዎቹ የግል ባህርይ ተመዝኖና ሥራውን ለማከናወን የሚያስችል ሆኖ ሲገኝም ነው የሚመረጡት።

5) ተግባቦተ መሥራት (consensus oriented)፡- ባህላዊው የዕርቅ ሥርዓት አሠራር በመግባባት ላይ የተመሠረተ ነው። የሽማግሌ ዳኛ ሆነ ሽማግሌ የሚመረጠው፣ ዕርቁ የሚካሄድበት ቀንና ቦታ የሚቆረጠው በዳይና ተበዳይ ተስማምተው ነው። ሽማግሌዎች የዕርቁን ድርድር የሚያካሄዱትና ውሳኔ የሚሰጡት በዳይና ተበዳይን ባሳተፈ መንገድ ነው።

6) የባህል ሕጉን ማክበር (respecting the customary law):- ሽማግሌዎች ሥራቸውን የሚያከናውነት የባህል ሕጋቸውን በማክበር ነው። በዳይ ጥፋተኛ የሚባለው ተበዳይም መበደሉ የሚመዘነው፣ ከዚህም በላይ ካሣ የሚከፈለው የባህል ሕጉን መመሪያ በማድረግ ነው።

7) ተሳታፊነት (participation)፡- በአርሲ ኦሮሞ የሲንቄ ሥርዓት በባህላዊ የግጭት አፈታት ወቅት ሴቶችን ተሳታፊ እንደሚያደርግ ቶሎሳ ማሙዬ (2011) ጽፈዋል። ይሁንና በብዙ ማኅበረሰቦች የዕርቅ ሥርዓቶች ላይ ሴቶች ሽማግሌ ሆነው አይሳተፉም። ይህም፣ የባህላዊ ዕርቅ ሥርዓት ድክመት ተደርጎ ይቆጠራል። ስለዚህም ተቋማቱ ሴቶችን አሳታፊ እንዲያደርጉ ተከታታይነት ያለው ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ በመሥራት የአፈጻጻም አቅማቸውን ማጎልበት ያስፈልጋል።

ቀደም ሲል እንደተገለጸው፣ ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓት የሚተገበረው፣ እምነትን ባተረፉ የአገር ሽማግሌዎች ወይም የሃይማኖት መሪዎች ወይም የጎሣ መሪዎች አማካይነት ነው። ተበዳይ የተፈጸመበትን በደል ለሽማግሌ ይዘረዝራል። በዳይም የፈጸመውን ድርጊት በግልጽ ያስረዳል ወይም በደል መፈጸሙ በተለያየ መንገድ በሽማግሌ ይረጋገጣል። በዳይ ለተበዳይ ተገቢውን ካሣ እንዲከፍል ይደረጋል። ይህ ሁሉ የሚደረገው በመስማማት ስለሆነ ዕርቁ ተቀባይነትና ዘላቂነት ያለው ግንኙነትን ለመመሥረት ያስችላል።

የባህላዊ ዕርቅ ሥርዓት ፍትሕን ያስገኛል። የዘር፣ የሃይማኖት፣ የፆታ፣ የሃብት ወዘተ. ልዩነት ሳይደረግ ሚዛናዊ የሆነ የዳኝነት አገልግሎት የሚገኝበት ሥርዓት ነው ተብሎም ይታመናል። ፍትሕ እንዲበየን ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርገው ድርድሩ በእውነት ላይ የተመሠረተ መሆኑ ነው። በዳይ ጥፋቱን አምኖ ሽማግሌ የወሰነበትን ካሣ ለተበዳይ ወገን መክፈሉ፣ ከዚህ በተጨማሪ ተጎንብሶ ይቅርታ መጠየቁ፣ የወደፊት ግንኙነትን ለማጽናት የሚያስችሉ ድርጊቶችን መፈጸሙ የሥነ-ልቦና እርካታን መፍጠሩ ነው። እነዚህ በባሕላዊ ዕርቁ የሚፈጸሙ ተግባሮች ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ያስችላሉ። ዘላቂ ሰላም ደግሞ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ቁልፍ ጉዳይ ነው።

 

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top