ዘባሪቆም

ቅናት! በሦስት ጉልቻና በሳቱ ዙርያ

ዛሬም እንዳለፈው ቀልድና ቁምነገር እያጣቀስን እንደ ቀልድ የምንጠረጥረውና እንደ ቀልድ የምንሰነዝረው በቁምነገር ተጋብተው እንደ ቀልድ የሚፈርሱ ትዳሮችን ጉዳይ ነው። በቁምነገር የተገነባ ትዳር እንደ ቀልድ ከሚፈርስባቸው ምክንያቶች አንዱ ቅናት ሳይሆን አይቀርም። ቅናት በሁሉም አፍቃሪ ልብ ውስጥ አለ ይባላል። ስሜቱ ሌጣውን ከጤናማ የፍቅር ባህሪያት እንደ አንዱ ይቆጠራል የሚሉም አሉ። በሌሎች ሰላምና ህልውና ላይ አደጋ እስካላስከተለ ድረስ ማለታቸው ነው። ይሄ የአደጋ ነገር ከተነሳ አንድ ጥያቄ አለኝ።

በቅናት ጦስ በሚወዷቸው ላይ አደጋ በማድረሱ ረገድ ወንዶችን የሚስተካከል ይኖር ይሆን? ይሄንን እየጠየቅኩ እና እያሰላሰልኩ በአንድ ወቅት ከወንዶች የበለጠ ሴቶች ቀናተኛ መሆናቸውን የሚገልፅ አዲስ ጥናት ማንበቤን አስታወስኩ። አዲሱ ጥናትም እንደ ቀልድ የሰማሁትን ጥንታዊ አባባል መልሼ እንዳሰላስል አደረገኝ።

በዚህ ዓለም ስትኖር በባሏ ቀንታ የማታውቅ አንዲት ሴት አለች። እሷም ሄዋን ነች ይላል። ይሁን እንጂ ይሄ በአዲሱ ጥናት እና በአሮጌው አባባል የተመሰከረለት የሴቶች ቅናት በወንዶች ላይ ስለሚያደርሰው የጉዳት መጠን በደንብ የተብራራ ጥናት አልገጠመኝም። የወንዶች ቅናት በሴቶች ላይ ስለሚያደርሰው ከፍ ያለ አደጋ ግን ብዙ ተጠንቷል፣ ብዙ ተብሏል፣ ብዙም ሰምቻለሁ። በቅርቡ እንኳ አንድ ወዳጄ የሚከተለውን አሳዛኝ ታሪክ አጫውቶኛል።

ባልና ሚስት ናቸው። እራት በልተው ወደ መኝታ ቤታቸው ገብተው መብራታቸውን ካጠፉ ቆይተዋል። ሚስት ከመጋደሟ እንቅልፍ ይዟት ሄዷል። ባልየው ግን ገና ነው። እኩለ ሌሊት አልፎ እንኳ ዓይኑ አልተከደነም። ለረጅም ሰዓት ከወዲያ ወዲህ እየተገላበጠ እንቅልፉን ያምጣል። ዓይኖቹ መኝታ ቤቱ ከዋጠው ድቅድቅ ጨለማ ላይ እንዳፈጠጡ ናቸው። በድቅድቁ ጨለማ ውስጥ ኪንታሮት የምታክል ቀይ መብራት በቀስታ ቦግ ድርግም ትላለች። ብልጭታዋ የምትመጣው የሚስቱ ሞባይል ቻርጅ እንዲሆን ከተሰካበት ግድግዳ አካባቢ መሆኑ ነው።

ድንገት የሆነ ድምፅ ተሰማው። እንቅልፍ ያጡ ዓይኖቹ ተጎለጎሉ። የሰማው በሚስቱ ሞባይል ውስጥ መልዕክት (ሜሴጅ) መግባቱን የሚያመለክት ድምፅ መሆኑን ሲገነዘብ መጀመሪያ ደነገጠ። ከዛ ቁጣ ቁጣም አለው። በዚህ ደረቅ ሌሊት ወደ ሚስቴ ሞባይል ሜሴጅ የሚልክ ማን ነው!? እንዴት ያለ ደፋር ነው!? እንዴት ያለ ባለጌ ነው!? ይህን እያውጠነጠነ ካልጋው ዱብ ይላል።

በዚያ ድቅድቅ ጨለማ ያቺን ቀይ መብራት ተከትሎ መራመድ ጀመረ። መጀመሪያ ኮቴው እንዳይሰማ የመኝታ ቤቱን ወለል በእግሮቹ አውራ ጣት እየረገጠ ነበር ሞባይሉ ጋ የደረሰው። ሞባይሉን አንስቶ የተላከውን ሜሴጅ ካነበበ በኋላ ግን ራሱን መቆጣጠር አቃተው። በንዴት “ቢዩቲ ፉል” ሲል ጮኸ።

ከንዴቱ ብዛትም ስልኩን ባለበት ትቶ ወደ መኝታው ተወረወረ። ተወርውሮም በሚስቱ ሰላማዊ እንቅልፍ ላይ ተከመረ። ከተጋደመችበት ትራስ ነጥሎና አንጠልጥሎ ብድግ አደረጋት። ጉሮሮዋን አንቆ ከግድግዳው ጋር አላጋት። ከወለሉ አላተማት። በቡጢ ደረገማት። በርግጫ አዳፋት። በጥያቄ አጣደፋት። “ማን ነው በእኩለ ሌሊት ‘ቢዩቲ ፉል’ የሚል ሜሴጅ የላከልሽ? ንገሪኝ እኮ! ማን ነው? ምን ይዘጋሻል! ማን ነው? ማን ነው? ማን ነው?” እያለ። ከእያንዳንዱ ማነው ጋር አንዳንድ ቡጢና እርግጫ ደረገመባት።

ሚስት ስለምን እንደሚያወራ ሊገባት አልቻለም። በጨለማ ውስጥ የሚሰነዘርባትን የቡጢ፣ የርግጫና የቴስታ መዓት ለመከላከል የውር ድምብሯን እየተፈራገጠች “እሪ” ትላለች። “የሰው ያለህ” ትላለች። “የጎረቤት ያለህ” ትላለች። “ድረሱልኝ” ትላለች። “አሰጥሉኝ” ትላለች። ትጮኃለች። “ዋይ ዋይ” ትላለች።

ስገምት ጎረቤቶቿ የደረሱላት በቴስታ አፍንጫዋን ካነሰረው፣ በጡጫ ናላዋን ካዞረውና በርግጫ የጎድን አጥንቷን ከሰባበረው በኋላ ሳይሆን አይቀርም። ብቻ እንዳይደርሱ የለም ደረሱላት። “ኧረ በገላጋይ” እያሉ፣ “ምን ነው አቶ እገሌ” እያሉ፣ “ኧረ ጡር ፍራ” እያሉ ተማፅነውና ለምነው እንደምንም ሚስቱን ወደ ሌላ ክፍል ከወሰዷት በኋላም ስራ በዛባቸው። የሱን እልህና መወራጨት ለማብረድ ብዙ ጊዜ ፈጀባቸው። አሁንም ይደነፋል። አሁንም ያጎራል። ያዙኝ ልቀቁኝ ይላል።

ሲይዙት “ብልግናዋን መቼ አያችሁት” ሲል ይወራጫል። ሲለቁት ቻርጅ ላይ የተሰካውን የሚስቱን ሞባይል ብድግ አድርጎ ያሳያቸዋል። “በኔ የደረሰ አይድረስባችሁ” ይላቸዋል። “ጉዷን ተመልከቱልኝ” ይላቸዋል። “ብልግናዋን እዩልኝ” ይላቸዋል። “መድሃኒአለም ነው ያጋለጣት” ይላቸዋል። “የዋህነቴን አይቶ እግዚአብሔር ነው እጄ ላይ የጣላት” ይላቸዋል። እጁንም ዘርግቶ ያሳያቸዋል።

በዚህ ስልኳ ላይ በደረቅ ሌሊት ይህንን ‘ቢዩቲ ፉል’ የሚል ሜሴጅ የላከላትን ደፋር ማወቅ እፈልጋለሁ” ይላል። “የኔን መተኛት ጠብቆ ይሄን ሜሴጅ የላከላት ውሽማዋ ማን እንደሆነ ገና አልተናገረችም” ይላል። ጎረቤቶችም እጁን ዘርግቶ “ተመልከቱልኝ” ያላቸውን ሜሴጅ አተኩረው ይመለከታሉ። እየተመለከቱም ደጋግመው ያማትባሉ። እያማተቡም “ኧረ አንተስ ሞተህ ባረፍከው” ይላሉ። ሞቱን እየተመኙ ሚስቱን በሰላም ከተኛችበት ቀስቅሶ በመደብደብ ከጥቅም ውጭ ያደረጋት በግፍ መሆኑን ይናገራሉ። እየተናገሩም ማስረጃቸውን ያቀርቡለታል።

ማስረጃ አገኘሁ ብሎ እንዲመለከቱ ከጋበዛቸው የባለቤቱ ሞባይል ላይ “ቢዩቲ ፉል” የሚል ሜሴጅ አለመኖሩን ያሳዩታል። ለካንስ ይሄ ሁሉ ኹከት የተፈጠረው በቅናት በታወረ ዓይኑ ሲደናበር “ባትሪ ፉል” የሚለውን ሜሴጅ “ቢዩቲ ፉል” ሲል በማንበቡ ኖሯል። ሲያሳፍር!

ደግነቱ ምድራችን እንደዚህ ያሉትን አሳፋሪና አስፈሪ ገገሞች ብቻ አይደለም ያፈራችው። በዚህች ምድር “ስማ ጓደኛዬ ሰሞኑን አንተ ቢሮ ደጋግማ የምትመላለሰውን ቆንጂዬ ልጅ በጣም ሳልወዳት አልቀረሁም፤ እባክህ አስተዋውቀኝ” ሲሉት፤ “ኦ! ያልካት ቆንጂዬ ልጅ እጮኛዬ ነች። ምርጫህን ግን አደንቃለሁ።” በማለት ነገርን ሁሉ በበጎ ዓይን መቀበል የሚችሉ ስልጡን ወንዶችም አሉ። ፍቅር አይሸበርም። ፍቅር አይደናገርም። ፍቅር አይጠራጠርም። ፍቅር አይሳደብም። ፍቅር አይደባደብም። ፍቅር- ፍቅር ብቻ ነው የሚሉ ስልጡን ወንዶች ይብዙ ይባዙ። ምድርንም ይሙሏት።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top