ስርሆተ ገፅ

ሥነሥዕል- የዓይን ምግብ

ሠዓሊ እና መምህርት ናት- ወ/ሮ ማክዳ ብዙነህ። የሥዕልን ጥበብ በተማረችበት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለፈለገ ሥነጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት የቀለም ቅብ መምህርት ሆና ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ በማገልገል ላይ ትገኛለች። ከአራት ዓመት በኋላም በቀለም ቅብ ጥበብ የድህረ ምረቃ የትምህርት ዕድል (ስኮላርሺፕ) በደቡብ ኮሪያ አግኝታ፣ ትምህርቷን አጠናቃ ተመልሳለች። “የሥዕል ሙያዬ እና መምህርትነቴ የቤት ውስጥ ኃላፊነቴን ከመወጣት አላገደኝም። በግልም በቡድንም ለበርካታ ጊዜያት ሥራዎቼን ለዕይታ አቅርቤያለሁ። አስተምራለሁ። ምግብ ማብሰል ላይ እንደውም ከሀበሻ ምግብ በተጨማሪ የኮሪያ ባህላዊ ምግብ ማዘጋጀቱን ችያለሁ። እንዲህ ነው የሥዕል ሙያ፣ ማስተማርና የቤተሰብ ኃላፊነት ተሰናስለው በህይወቴ ውስጥ የሚኖሩት” ትላለች በአለፈለገ ጋለሪ ውስጥ ላነጋገራት ዘጋቢያችን ጌታቸው ወርቁ። የዓይን ምግብ የሆነውን ‹‹ቪዥዋል ጥበብ›› በማክዳ አንፃር እስቲ እንመልከተው፡-

ታዛ፡- በሥነ-ጽሑፍ ውስጥ ብዙ አንባቢ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚያውቃቸው መሠረታዊ የሥነ-ጽሑፍ ዓላባውያን (ገጸባህሪ፣ ሤራ፣ ግጭት፣ አንፃር፣ ጭብጥ …) የሚባሉ አሉ። ስለዚህ አንብቦ በቀላሉ ይረዳል። በሥዕል ጥበብ ውስጥስ ብዙ ተመልካች ሊያውቀው የሚገባ መሠረታዊ የሥዕል ጥበብ ዓላባውያን አሉ? ምን ምን ናቸው?

ሠዓሊ ማክዳ ብዙነህ፡- በዚህ (አለፈለገ) ትምህርት ቤት መጀመሪያ የሚሰጡት የ‹‹ቪዥዋል ጥበብ›› ዓላባውያን አሉ። ተማሪዎቹ ይሄን ጠንቅቀው አውቀው ነው ሥዕል የሚጀምሩት። በሥዕል ጥበብ የ‹‹ቪዥዋል›› ጥበብ ዓላባውያን ከነጥብ (ዶት) ይጀምራል፤ ከዚያም ወደ መስመር ያድጋል። መስመሩ ደግሞ የተለያዩ ቅርፆች አሉት። ቀጥታ መስመር አለ፣ አግድም መስመር አለ፣ የቁም መስመር አለ፣ ዚግዛግ መስመር አለ፣ ኦብሊግ አለ፣ ቅንፍ አለ፣ ክብ የሚመስል አለ። እነዚህ ሁሉ የየራሳቸው ትርጉም አላቸው። በየራሳቸው የሚወክሉት የስሜት ነፀብራቅ አለ። መስመርን ብቻ ተከትለን ብዙ ጥናቶችን ልናደርግ እንችላለን። አንድ የሥዕል ሥራ ላይ መስመሮችን በማየት ብቻ ከዛ ሥዕል የሆነ ስሜት ልንረዳ እንችላለን። ይህንን እንግዲህ ወይ የግል ስሜታችን ነው ሊነግረን የሚችለው። ወይም ደግሞ በስነ-ጥበብ ሙያ ውስጥ ካለፍን በቀላሉ የሚወክሉትን ስሜት ልንረዳ እንችላለን።

መስመር ደግሞ ወደ ቅርጽ (ሼፕ) ከፍ ይላል። ክብ፣ አራት ማዕዘን፣ ሦስት ማዕዘን፣ ሦስት ጎን፣ አምስት ጎን፣ እያለ ይቀጥላል። ይሄም የራሱ ትርጉም፣ የራሱ የስሜት ነፀብራቅ ተምሳሌት አለው። ይኸው ቅርጽ ደግሞ ወደ ጥላና ብርሃን ያድጋል። ወደ ‹‹ስሪ ዳይሜንሽን›› ወይም ፎርም ይለወጣል። በዚህ ውስጥ ደግሞ ኪዩብ አለ፣ ፒራሚድ አለ፣ ስሊንደር አለ፣ ኮን አለ፣ እንደዛ እንደዛ እየተባለ ወደ ፎርሞች ከፍ ይላል። አሁን እነዚህን ፎርሞች በምንድን ነው የምንገልፃቸው!? ወደ ‹‹ስሪዲ›› ወይም ‹‹ሼድ›› የሚባል አለ። ያው በድሮዊንግ ቴክኒክ ጥላ እና ብርሃንን በማስቀመጥ እነዚህን ፎርሞች ልናጎላቸው እንችላለን። እነዚህ ፎርሞች ደግሞ፣ ቀስ እያልን በምንሄድበት ሰዓት ሼድ እንጠቀማለን። በዚህ ውስጥ ደግሞ ብርሃናማ (ብራይትነስ)፣ ጨለምለም ያለ (ዳርክነስ) የሚባሉ ነገሮች አሉ። እነርሱም እዚሁ የ‹‹ቪዥዋል›› ጥበብ ዓላባውያን ውስጥ ይካተታሉ። የሚወክሉት ተምሳሌትና የሚገልጡት የስሜት ነጸብራቅ አለ።

አንድ ድሮዊንግ ደግሞ ብርሃናማ (ብራይትነስ) እና ጨለማማ (ዳርክነስ) ከሌለው ‹‹ኮንትራስት›› የሚባለው አይመጣም። ይሄን ካላሟላ ደግሞ ሙሉ ሥዕል ላይሆን ይችላል ማለት ነው።

‹‹ቪዥዋል›› ጥበብን ትርጉም ከሚሰጡት ዓላባውያን መካከል ደግሞ ቀለም (ከለር) አንዱ ነው። አሁን እኛ በነጭና ጥቁር (ብላክ ኤንድ ዋይት) እናየዋለን እንጂ፣ በተለያየ ‹‹ሚድየም›› ተጠቅመን ውሃም ይሁን፣ ‹‹አክሪልክ››ም ይሁን፣ ዘይትም ይሁን፣ ቀለም ራሱ አንድ የዕይታ ጥበብ ዓላባ ነው። ሞቃት ፀሐያማ ቀለም (ቢጫ፣ ቀይ፣ ቡናማ) ስትጠቀምና ቀዝቃዛ ቀለም (ሰማያዊ፣ አረንጓዴ፣ ግራጫ) ስትጠቀም የምታስተላልፈው ስሜት ለየቅል ነው። እነዚህ ተምሳሌታዊ (ሲምቦሊክ) ናቸው። መቼም ለቅሶ ስትሄድ ነጭ በነጭ ለብሰህ፣ ቂቅ ብለህ አትሄድም። ሠርግ ላይም ጥቁር በጥቁር ተከናንበህ አትሄድም። ምክንያቱም በማኅበረሰብህ ውስጥ ቀለማቱ የሚያስተላልፉት ስሜትና ትርጉም ስላለ ነው።

ከቀለም ቀጥሎ ደግሞ ‹‹ኮምፖዚሽን›› አለ። ኮምፖዚሽን ማለት ደግሞ እነዛ ያስቀመጥካቸው ነገሮች ምን ላይ ነው የሰፈሩት፣ በምን አይነትስ መጠን ነው የሰፈሩት የሚለውን ነገር የሚያይልህ ‹‹ኮምፖዚሽን›› ነው ማለት ነው። ኮምፖዚሽን ውስጥ ደግሞ ምጣኔ (ባላንስ) የሚባል ነገር አለ። ምጣኔ ይታይበታል ወይ? ግራና ቀኝ በአግባቡ ተመጥኗዊ ‹‹ሴሜትሪካል›› ነው ወይ? ወይስ የተዛባ (አን ሴሜትሪካል) ነው ወይ? እነዚህ ሁሉ ነገሮች ናቸው ከሞላ ጎደል መሟላት ያለባቸውና የስሜትም የይዘትም ትርጉም የሚሰጡ ማንጸሪያዎች። ስለዚህ የዕይታ ጥበብን የሚከውን ሰው እነዚህን መሠረታዊ ነገሮች ማወቅ ግዴታው ነው። የሥዕል አድናቂም ይሄን ጠንቅቆ ቢያውቅ ሥዕልን በቀላሉ ይረዳል።

ታዛ፡- ምን ዓይነት ሥዕሎች ናቸው ከራስጌሽ፣ ከሳሎንሽ፣ ከስቱዲዮሽ እንዳይጠፉ የምትፈልጊው? ወይም የማትሸጫቸው?

ሠዓሊ ማክዳ ብዙነህ፡- የድሮ የልጅነት ሥራዎቼን ነው። ምንም ዓይነት የቴክኒክም ሆነ የሥዕል ትምህርት ዕውቀት ሳላዳብር፣ በንፁህ ልቦናና አዕምሮ የሰራኋቸው ሥራዎቼን ተመልሼ እንደማልሰራቸውና እንደማላገኛቸው ስለማውቅ እነርሱ ከአጠገቤ እንዲርቁብኝ አልፈልግም። በገንዘብም አልሸጣቸውም። እነርሱ የማንም ተማልሏዊ ተጽዕኖ (ኢንፍሎዌንስ) ያላደረባቸው ሥራዎቼ በመሆናቸው፣ ትልቅ ዋጋ እሰጣቸዋለሁ።

ከሌሎች ሠዓሊያን ሥራዎች ደግሞ የወሰኔ ኮሶሮቭ ሥራዎች አድናቂ ነኝ። እርሱ በአሁኑ ጊዜ አሜሪካ አገር የሚኖር ዓለማቀፋዊ አርቲስት ነው። የገብረክርስቶስ ደስታ፣ የእስክንድር ቦጎስያን፣ የጋሽ ዘሪሁን የትምጌታ አድናቂ ነኝ። እነዚህ የኢትዮጵያዊነትን ትክክለኛ ማንነት ያለውን ሥዕል ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ የማሸጋገር ብቃት ያላቸው አርቲስቶች በመሆናቸው ለነሱ ትልቅ አክብሮት አለኝ። እኔም ወደነሱ መንገድ መሄድ ብችል በጣም ደስ ይለኛል። አነቃቅተውኛል።

ታዛ፡- ሥትስይ ልዩ መነቃቂያሽ ምንድን ነው?

ሠዓሊ ማክዳ ብዙነህ፡- እኔ ሙዚቃ ወይም ሬድዮ በጣም ማዳመጥ አለብኝ። ‹‹ክላሲካል›› እና ‹‹በመሳሪያ ብቻ የተቀነባበረ›› (ኢንስትሩመንታል) ሙዚቃ ስሰማ… በቃ… በደንብ… የሆነ ደስ የሚል ሥራ እንደምሰራ ይሰማኛል። ወይም ደግሞ በራዲዮ ወሬም ሊሆን ይችላል የማደምጠው

ታዛ፡- ለስነ-ሥዕል ተማሪዎችሽ ምንድን ነው የምትመክሪያቸው? ሠዓሊ ማክዳ ብዙነህ፡- በስነሥዕል ሙያዊ ህይወታቸውን ቀስ ብለው በተፈጥሯዊ ሁኔታ (ፕሮሰስ) እንዲያልፉ ነው። አሁን- አሁን በርካታ ወጣቶች ላይ የሚታየው ዝንባሌ ቴክኖሎጂ ላይ መጣበቅ ነው። ሥራዎቻቸውንም ወደ ኮምፒዩተር የሚወስዱት ነገር አለ። ግን ያ የሆነ ደረጃ ላይ ሊመጣ የሚችል ነውብዬ ነው የማስበው። በእርግጥ ኮምፒውተር መጠቀም ሥራህን ሊያቀልልህና ጊዜህን ሊያሳጥርልህ ይችላል። ነገር ግን ክህሎት ላይ ደግሞ የሆነ ተጽዕኖ ሊያመጣል ይችላል። ሆኖም፣ አንድ ሰው በተለምዶ ቢጀምር ከመነሻው በጣም ጠንካራ የሆነ መሠረት ካለው የትም መድረስ ይችላል። ቴክኖሎጂም በሁሉም ነገር ያለ ጠንካራ መሠረት ያን ያህል ውጤታማ እንደማያደርግ እንዲያውቁ እጥራለሁ።

ታዛ፡- ማነነትን በማግኘት ላይስ ? ሠዓሊ ማክዳ ብዙነህ፡- በተለይ ደግሞ ማንነት (ኢትዮጵያዊነት) ላይ በደንብ አተኩረው እንዲተጉ ስለራሳቸው እንዲያውቁ ነው የምመክራቸው። ከምንም በላይ ደግሞ ማንበብ ነው ትልቅ ለውጥ የሚያመጣው። ብዙ ጊዜ ሥዕል ሲባል ሁሉም ሰው ወደ ተግባሩ፣ ወደ ንድፉ፣ ወደ ቀለም ቅቡ ነው የሚቸኩሉት። ነገር ግን ከንባብ እንዲጀምሩ፣ አንብበው መፃፍ እንዲጀምሩ፣ ስለ ራሳቸው ሥራ ብዙ ነገር እንዲጽፉ የሌሎችንም ስራ እንዲያነቡ ነው በአሁኑ ጊዜ የሚመከሩት።

ብዙ ጊዜ ሰዓሊያን ጭምቶች ናቸው፣ ራሳቸውን በቋንቋ መግለጽ አይችሉም፣ ከሰው ጋር አይግባቡም፣ ሥራቸውን በንግግር መግለጽ አይችሉም የሚባለው እንዲቀረፍና አሁን ደግሞ በዘመኑ ትኩረት የተሰጠበት እንደ ሌላው ሙያ ሥራዎቻቸውን በተመለከተ ገለፃ እንዲያደርጉ፣ ስለስራቸው እንዲያሳምኑ፣ እንዲጽፉ እያበረታታን ነው።

ታዛ፡- በልጅነትሽ ምን ዓይነት ዝንባሌ ነበረሽ?

ሠዓሊ ማክዳ ብዙነህ፡- የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ እያለሁኝ ድርሰቶች እጽፍ ነበር። ሥዕል የጀመርኩት ገና በሦስተኛ ክፍል የሥዕል መምህራችን አማካኝነት ነበር። በልጆች ፕሮግራም ላይ ብዙ ውድድሮችን ተሳትፌያለሁ። አባባ ተስፋዬ ነበሩ ጥሪውን የሚያቀርቡት። ቤተሰብም ድጋፍ አድርገውልኝ የክረምት መሠረታዊ የህፃናት የሥዕል ኮርሶችን እዚሁ (ሥነጥበብ ት/ቤት) እንድማር ያደርጉ ነበር። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን እንዳጠናቀቅኩ ሥነ ሥዕል ለማጥናት ቤተሰብ ስላልፈቀደልኝ ኮሜርስ ገብቼ ማርኬቲንግ ማኔጅመንት አጥንቼ ተመረቅኩ። በኋላ በራሴ ፈቃድ መኖር ስጀምር የራሴን ፍላጎት አድምጬ ሁለተኛ ዲግሪዬን ቀለም ቅብ አጠናሁ።

ታዛ፡- ጀምረሽ ያልጨረሽው ሥዕል አለ?

ሠዓሊ ማክዳ ብዙነህ፡- ሊኖር ይችላል። ያ ደግሞ መሆን የሚችለው በ‹‹ሙድ›› ነው ልሰራ የምችለው። ያ ሙድ ካለፈ በኋላ ተመልሰህ እዛ ሥራ ላይ መምጣት እንደ ተራራ ሆኖ ሊከብድህ ስለሚችል ታስቀምጠውና አመቺ ጊዜ የምትፈልግበት አጋጣሚ ይኖራል።

ታዛ፡- የሠዓሊ ኃይሉ ዓይኑ ነው ይባላል፤ ቀለምን ከቀለም፣ ብርሃንን ከጥላ፣ መስመርን ከመስመር መለየትና መረዳት መቻሉ?

ሠዓሊ ማክዳ ብዙነህ፡- ይሄንን ከትምህርት ቤት ጀምረህ የምታዳብረው ነው። እኛ ስንማር መጀመሪያ የተሰጠን ሥልጠና ምንድን ነው መሰለህ- ነገሮችን ጥርት አድርጎ ማየት መቻልን ነው። በቃ ማስተዋል ነው ሥዕል ማለት ተብሎ ነው የተነገረን።

ታዛ፡- ስለ ‹‹አብስትራክት›› ሥዕል ምን ትይናለሽ?

ሠዓሊ ማክዳ ብዙነህ፡- በገሃዱ ዓለም ስንኖር የምናውቃቸው ነገሮች አሉ። ለምሳሌ የሰው ልጅ ብለህ በተለምዶ ምስሉን ስታስብ የሚመጣልህ አማካኝ መጠኑ፣ ‹‹አናቶሚው›› አለ። ሁለት ዓይን፣ አንድ አፍንጫ፣ ሁለት ጆሮ፣ ቁመናው ምናምን ነው። ነገር ግን፣ አብስትራክት ብለን በሥዕል ጥበብ ስንተረጉመው ያ የተፈጥሯዊ ይዘቱን በከፊል ወይም በሙሉ በመደበቅ (ሚስጥራዊ ነው) ከሰዓሊው ሃሳብ፣ የህይወት ምልከታና ፍልስፍና እና ስሜት ጋር በማዋሃድ ሰውን የሚወክል ፎርም ወይም ሰውን ሊወክል የሚችል ቀለም አሊያም መስመር ተጠቅመን፣ ነገር ግን እንዲህ ስናየው ሰው ነው ልንለው የማንችለውን ከተለምዶ ውጪ የሆነ ወይንም ደግሞ ያንን ነገር አጋነንና አጉልተን የምናቀርብበት ጥበብ ነው።

አብስትራክት ማለት ሠዓሊዎች ከብዙ ኤክስፐርመንት በኋላ፣ ከብዙ ስራዎችና ኤግዚቪሽኖች፣ ከብዙ አስተያየቶችና የስቱድዮ ቆይታዎች በኋላ በህይወታቸው የሚደርሱበት ነው። ይሄ ጅኦሜትሪካል ፎርሞች ስላሉት፣ ሦስት ማዕዘን፣ አራት መዓዘን፣ ክብ የምንለው፤ እነሱን በማወቅ ነው የሚሰራው። የሚወክለውም ነገር አለው። በነራችን ላይ አንጋፋ ሠዓሊያን ናቸው ይሄን የሚሰሩት። በሥዕል ህይወታቸው ብዙ ምርምርና እውቀት አዳብረው የራሳቸውን አተያይና ፍልስፍና ጨምረው ነው የሚሰሩት። ገና ሥራውን ስታይ ምን ያህል እንደተጠበቡበት በቀላሉ ትረዳለህ።

እኔ በፊት የሰራኋቸው አብስትራክት ሥዕሎች አሉ፤ በጣም ያረጁ የአዲስ አበባ ቤቶች ናቸው። የፈረሱም፣ በመፍረስ ላይ ያሉም ወደፊት ይፈርሳሉ የተባሉ ቤቶች ናቸው። መጀመሪያ በእውነታው አሳሳል ልቅም አድርጌ ሰራሁት። ነገር ግን፣ በሥዕል ሙያ ከጊዜ ብዛት ብዙ ምርምርና ጥናት አድርገህ ወደ ቀላል (ሲምፕል) የሆነ ነገር ትመጣለህ። በቃ ቀላል መስመሮችንና ቀላል ፎርሞችን ተጠቅመህ እነሱን ይወክሉልኛል የምትለውን የግል አተያይና ምርምርህን አካተህ ገፅታውን ታስቀምጣለህ ማለት ነው። እኔም ይሄ የኢትዮጵያ ባህላዊ ቀለም ቅብ ሥራዎችን ዘዬ በመጠቀም (‹‹ዲኮራቲቭ›› ነገር ይበዘዋል) ተደጋጋሚ ምስሎች (ኢሜጆች)፣ ፓተርኖች በማስቀመጥ በዛ መልክ እነዛን ቤቶች አብስትራክት አድርጌ ሰርቻለሁ።

ታዛ፡- አመሠግናለሁ

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top