ዘባሪቆም

ምልከታ ከትዝብት ማስታወሻ

የሆድ ነገር!

አ ንዲት በመጠኗ የሱሪዬን የኋላ ኪስ የምትስተካከል ማስታወሻ ደብተር አለችኝ። ላይ እና ታች ማለት ከሰው እያገናኘኝ የምሰማቸውን አስገራሚ አንዳንዴም አስቂኝ ሃሳቦች፣ ቀን ላይ በርክተው ሲመሽ በዝንጋታ ፅልመት እየተዋጡ አልታይ ቢሉኝ፣ ይህቺን ማስታወሻ ደብተር ገዝቼ ከኋላ ኪሴ አኖርኳት። የኑሮን ጥያቄ ለመመለስ ታች እና ላይ ስል በድንገት ብልጭ ብለው አፍታ ሳይቆዩ ድርግም የሚሉ ሃሳቦችን እከትብባታለሁ። እንዳመቸኝና እንደተመቸኝም ከኪሴ እየመዘዝኩ ስሞነጭርባት ከርሜ የፊትና የኋላ ገፆቿ ሞልተው ‹አለቅሁ› ብትለኝ ወደ ኋላ ተጉዤ በውስጧ የሰፈረውን መፈተሽ ጀመርሁ።

ይህቺ ማስታወሻዬ በገፅ ብዛትና በመጠኗ አነስተኛ ትምሰል እንጂ በርካታ አነጋጋሪና አሳሳቢ ማኅበራዊና ባህላዊ ሕፀፆቻችንን በአጭሩና በትዝብት መልኩ ይዛ አገኘኋት። ለምሳሌ በመጀመሪያ ገፅ ላይ ከሰፈሩት አራት ጉዳዮች አንዱ እንዲህ ይነበባል፡-

‹‹መስከረም 12/2008- አንድ ግለሰብ ሚስቱን (ፍቅረኛውም ልትሆን ትችላለች) ጉለሌ አካባቢ ከሚገኝ የግል ሆቴል ቅጥር ግንብ ጋር ጭንቅላቷን እያጋጨ ሲደበድብ፤ ሰው ከማገላገል ይልቅ ተሰብስቦ እንደ ትርዒት ሲመለከት…›› ይላል። ክስተቱን በሙሉ ለማስታወስ ይህ ለእኔ በቂ ነው።

እንግዲህ እኔም በዚህች ማስታወሻዬ ላይ በተለያየ አጋጣሚ ያሰፈርኳቸውን በርካታ ትዝብቶች ተመለካክቼ ሳበቃ በተራው ለአንባቢ ደርሶ ብንማማርበት እንዲሁም ብንታረምበት መልካም መስሎ ታሰበኝ። እናም የመጀመሪያ ምርጫዬ ያደረኳቸውን ሁለት የምግብ ቤት ትዝብቶቼን እንደመነሻ እነሆ እላለሁ።

መሐል ፒያሳ፤ የማሕሙድ ሙዚቃ ቤትን በመታከክ ቁልቁል ወደ ቸርችል (?) የሚወስደውን መንገድ ሲጀምሩ ከምትገኝ አንዲት ምግብ ቤት እንገኛለን። (አንባቢን አደራ የምለው በስተግራ ከሚገኘውና ስላየሁ ብቻ ያስከፍሉኛል ብዬ ከምሰጋው ሬስቶራንት ጋር ምግብ ቤቷን እንዳያምታታብኝ ነው።) ምግብ ቤቷ ዘወትር በተስተናጋጅ ብትጨናነቅም የምግቧ ጣፋጭነት ከዋጋዋ ተመጣጣኝነት ጋር ተዳምሮ ወንበር የማጣትን ችግር እንዳናስበው አድርጎናል። ታዲያ የዚያን ቀን ከወዳጄ ጋር ስንደርስ አስተናጋጇ ክፍት ቦታ ፈልጋልን ብታጣ ከባንኮኒው ሥር ሁለት ወንበሮች አስቀምጣ በመሐሉ ጠረጴዛ አስገባችልን። የዚያን ቀን የተቀመጥንበትን ሥፍራ ልዩ የሚያደርገው በቤቷ እየተከናወነ ያለውን ማንኛውንም ድርጊት ለመመልከት ማስቻሉ ነበር።

እንደየምርጫችን ምግባችን ቀርቦ በወግ እያጣጣምን መመገብ ስንጀምር ከአጠገባችን የነበረ ጠረጴዛ ተለቅቆ ኖሮ አንድ ወጠምሻ ፍቅረኛው የምትመስል ኮረዳ አስከትሎ በፍጥነት ሰፈረበትና ማጨብጨብ ጀመረ። ‹ገና መቀመጡ ነው፤ ምናለበት ትዕግስት ቢያደርግ› በሚል ትዝብት ገረመምነው።

ወጠምሻው አስተናጋጇ ስትቀርበው የኮረዳዋን ምርጫ እንኳን ሳይጠይቅ ‹‹አንድ የፆም በየአይነቱ እና አንድ ፓስታ በእንጀራ… ዳቦም ጨምሪበት›› አለ። አስተናጋጇ ሳትዘገይ በትልቅ ትሪ ላይ የታዘዘችውን ምግብ ጎን ለጎን አድርጋ ከፊታቸው አስቀመጠች። ከዚህ በኋላ ነበር እስከ ዛሬ ባስታወስኩት ቁጥር ስሜቴን የሚፈታተነውን ድርጊት መታዘብ  የቻልኩት።

ወጠምሻው የፓስታውን ሰሀን በማንሳት ቁልቁል እንጀራው ላይ ዘርግፎ ሲያበቃ አብሮ በቀረበለት ማንኪያ ማሰል ማሰል አድርጎ ወደ ጎን ወረወረው። ከዚያም ሩብ እንጀራ የሚያህል በላዩ ጣለበት። የፓስታውን ሰፊ ክፍል ቦድሶ ካነሳለት በኋላም እግረመንዱን በየዓይነቱ ከቀረበው ወጥ እየጠራረገ ሄደና አለመጠን ወደከፈተው አፉ ላከው። ሸክሙን አራግፎ ሲያበቃ በግራ እጁ የያዘውን የተሰነገ ቃሪያ ጭራውን አስቀርቶ እንዳለ ዶለበት።

ኮረዳዋ የወጠምሻው አበላል ሳያስደነግጣት አልቀረም፤ ዙሪያዋን በሀፍረት እየቃኘች ለኮፍ ለኮፍ ታደርጋለች። እሱ እቴ ምን ገዶት… እንኳን በዙሪያው ያለውን ሰው ቀርቶ ከፊቱ የተቀመጠችውንም ዘንግቷል። አጎንብሶ ክምሩን እየናደ ወደ አፉ ይልክና በጭንቅ ተይዞ ዓይኑን እያጉረጠረጠ ይሰለቅጠዋል። አበላሉ ኮረዳዋን ከመቆንጠርም አግዷት በትዝብት ትመለከተው ጀመር። ወጠምሻው አስፈሪ አበላሉን ቀጥሏል።

ወዳጄ በእኔ ሁኔታ ተስቦ የትርዒቱ ታዳሚ ከሆነ በኋላ በእግሩ ጎሸም አደረገኝና ‹‹ብላ እንጂ›› አለኝ።

ለካስ በዚህ ወጠምሻ አስፈሪ ድርጊት ቀልቤ ተወስዶ ኖሮ፣ መመገቤን ዘንግቼዋለሁ። በዚህ ዓይነት ሰቅጣጭ ትይንት ውስጥ መመገብ አስጠላኝ፤ ወይም ዘጋኝ። የወዳጄ ስጋት ግን ገብቶኝ ነበር። ምናልባት ወጠምሻው በድንገት ቢዞርና የሚሰራውን እንደማየው ቢያውቅ ለጠብ ሊጋበዝ እንደሚችል ገምቶ ነው። እኔ ግን በትዝብት መመልከቴን አላቋረጥኩም። ካልተሳሳትኩ ስድስት ያህል ክምሩን ወደ አፉ እንደላከ ትሪው ላይ የወዳደቁ የሩዝ ፍሬዎችና ብጥስጣሽ የእንጀራ ቅሪቶች ብቻ ቀሩ። ኮረዳዋ ምንተፍረቷን አንዷን ብጣሽ እንጀራ አንስታ የሩዙን ፍሬዎች ጠርጋ ስትጎርስ ወጠምሻው ውሃ የሞላ ብርጭቆውን አንስቶ ገጠመና አንዴ አገሳ። አስከትሎም በፈገግታ፡-

‹‹እንዴት ነው፤ ይጨመር እንዴ!?›› ሲል ጠየቃት። በአንገቷ ንቅናቄ አጅባ

‹‹በቃኝ›› አለችው።

ወጠምሻው ተነስቶ ወደ መታጠቢያ ክፍል ሲያመራ አልተከተለችውም። በሀፍረት ስሜት አሊያም በግራ መጋባት ተይዛ መሰለኝ ጣቶቿን አቀርቅራ እያፍተለተለች ጠበቀችው። ምናልባት ከዚህ ወጠምሻ ጋር ትዳር ብትመሰርት የሚያደርስባትን መከራም እያሰላሰለች ይሆናል። እንዲህ ማሰቧ ልክ ነች። ‹‹ዛሬ›› ለአንድ ጉርሻ ትዝ ያላለችውን ሴት ቢያገባትማ በረሃብ መሞቷም አይደል? እናም ይህቺ ኮረዳ ማስተዋል ቢኖራት ዛሬ ‹‹በቃኝ›› ያለችው ምግቡን ሳይሆን ወጠምሻውን መሆኑን መረዳት አለባት ስል አሰብኩ። 

ወዳጄ በፈገግታ እየተመለከተኝ፡ – ‹‹ትርዒቱ አብቅቷል፤ ወደ ምግብህ ተመለስ›› አለኝ።

‹‹በቃኝ›› አልኩት። የወጠምሻው ዘግናኝ አበላልና የልጅቷ አሳዛኝ ሁኔታ ረብሾኝ ነበር።

ኧረ እየተስተዋለ! አሁን አንድ ጉርሻ ማንን ገደለ? ክፋትእንጂ!

የምግብ ቤቶችን አዘውታሪ ሰው አይደለሁም። እንዲያውም የግድ ካልሆነብኝ በስተቀር በቤቴ ከቤተሰቤ ጋር መመገብ የምመርጥ ሰው ነኝ። ይሁንና በሥራ ውሎ አሊያም በሌላ አጋጣሚ ወደ ምግብ ቤቶች ጎራ ባልኩባቸው ጊዜያት ስሜቴን የሚያጨፈግግ ወይም የሚያስገርም ገጠመኝ አያጣኝም። ከትዝብት ማስታወሻዬ ሌላውን ደግሞ እነሆ!

በወዳጄ ጋባዥነት ጀሞ አካባቢ ታዋቂ ከሆነ አንድ ሬስቶራንት በምሽት ተገኝቻለሁ። ከጥቂት ቆይታ በኋላ ሁለት ጎረምሶች ወደ ሬስቶራንቱ በመዝለቅ ወንበር ይዘው ተቀመጡ። አስተናጋጁ ሜኑውን አስቀድሞ በማቅረብ ትዕዛዛቸውን መጠባበቅ ጀመረ። ጎረምሶቹ የሚያዙትን ምግብ ተመካክረው መረጡና አንዱ ተናገረ፡- ‹‹አንድ ጥብስ ፍርፍር፣ አንድ ቋንጣ ፍርፍር…››

ፍርፍር ከፍርፍር ጋር መታዘዙ ለአስተናጋጁ የተዋጠለት አይመስልም፡ –

‹‹አንዱን ሌላ አታደርጉትም? ወይም አንዱን መጀመሪያ ሞክሩት… እንዳይበዛባችሁ ብዬ ነው…›› አለ። ጎረምሶቹ ‹በምን አገባው› አተያይ ከገላመጡት በኋላ የታዘዘውን እንዲያመጣ በአንድ ድምፅ ነገሩት።

አስተናጋጁ የታዘዘውን አሰርቶ ሲመለስ ብዛቱ አስደንጋጭ ነበር። ጠረጴዛውን ሞልቶ አስቀምጦ ሲያበቃ ተመልሶ ሄደ። ከዚያ በኋላ ነበር በትዝብት ማስታወሻዬ ላይ ሥፍራ ለማግኘት የበቃውን ትዕይንት ያስተዋልኩት።

የመጀመሪያው ጎረምሣ በፍጥነት የተጠቀለለውን እንጀራ ተርትሮ ሲያበቃ ከጥብስ ፍርፍሩ ሩቡን፣ ከቋንጣውም ፍርፍር እንዲሁ ሩቡን የሚያህለውን ካነሳለት በኋላ፣ አፉን አለቅጥ ከፍቶ ሲልከው ጓደኛውም ተከትሎ እንዲሁ አደረገ። የመጀመሪያው ጎረምሣ ሁለት ጉንጮቹ ሞልተው ከአፉ ውጭ የተረፈውን እንጀራ በሌባ ጣቱ ወደ ውስጥ እየገፋ የታነቀ ሰው መስሎ ዓይኑን እያጉረጠረጠ ለሌላ ጉርሻ መንደርደር ሲጀምር ጓደኛውም ተከተለው።

በአበላላቸው ውድድር የያዙ ይመስሉ ነበር። ሁለተኛውን ‹‹ጉርሻ›› አስከትለው በጣታቸው ወደ ውስጥ መጠቅጠቅ ሲጀምሩ አንዱ አየር እንዳጠረው በአፍንጫው ከሚያወጣው አተነፋፈስ ያስታውቅ ጀመር። እንደ እኔው የጎረምሶቹን ነውረኛ ድርጊት በድንጋጤ ሲያስተውል የቆየው ወዳጄ በአግራሞት፡-

‹‹እንዴ!›› የሚል ድምፅ ቢያወጣ ሁለቱም ዞረው ገረመሙትና ግድ እንዳልሰጣቸው በትከሻቸው ንቅናቄ አሳይተውት ወደ ውድድራቸው ተመለሱ።

ጎረምሶቹ ከፊታቸው የቀረበውን እህል እያፈሱ አፋቸው ውስጥ በመሞጀርና ሲተርፍም በጣታቸው በመጠቅጠቅ ትሪውን በደቂቃ ውስጥ እርቃኑን አስቀሩትና የወንበሩ መደገፊያ ላይ ወደ ኋላቸው ተለጥጠው በእርካታ አገሱ።

ኧረ ጎበዝ ምንድን ነው ነገሩ? አበው ‹‹አፍ የሚጎርሰውን እጅ ይመጥነዋል›› ይሉ ነበር። አጎራረሳችን የብዙ ነገር ማሳያ መሆኑን እግረመንገድ እየነገሩን እኮ ነው። ሰዎች ከሚያሳዩን እንደ ስግብግብነት፣ ንፉግነት፣ ከርሳምነት፣ … ወዘተ ዓይነቶቹ አጓጉል ባህርያት የተነሣ ደንግጠን ብንርቃቸው አሊያም ብንፈራቸው የሚገርም ላይሆን ይችላል። በአበላላቸው መደንገጥ ከጀመርን ግን አደገኛ ነው፤ የድርጊቱ አስፈሪነት ከትዝብትም በላይ  ነውና!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top