አድባራተ ጥበብ

ሙዚቃ፣ ቱሪዝምና ኢኮኖሚ

ሙዚቃ፣ ቱሪዝምና ኢኮኖሚ በራሳቸው ታላላቅ የሆኑ ዘርፎች እንዴትና በምን ዓይነት መንገድ በአንድ ርእሰ-ጉዳይ ላይ ተገናኙ እንደምትሉ እገምታለሁ። እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ቢኖር አይገርምም። ምክንያቱ ደግሞ ግልፅ ነው። እኛ በተለምዶ ሦስቱንም (ሙዚቃ፣ ቱሪዝምና ኢኮኖሚን) በየራሳቸው ምሉዕ ሆነው ስለምናውቃቸው እና ስለለመድናቸው ነው። እንኳን እኛ በዚህ ዘርፍ ብዙ የሚቀረን ህዝቦች ይቅርና በአደጉት አገራትም ቢሆን ይህ ዓይነቱ ጥምር ግንኙነት ግንዛቤ ማግኘት የጀመረው በሃያኛው ክፍለ-ዘመን ማገባደጃ በነበሩት አሰርት ዓመታት አካባቢ ነውና፣ መጠየቁ አይገርምም። ስለ ሦስቱ ዘርፎች ትስስር ከማየታችን በፊት ግን፣ ስለእያንዳንዳቸው የነበረንን ግንዛቤ ቀድሞ መፈተሹ መልካም ነው።

ስለ ‹‹ቱሪዝም›› ያለንና የነበረን ግንዛቤ ምንድን ነው? አዎ! ግልፅ የሆነው ነገር፣ ቱሪዝም ሲነሳ ወደ አእምሯችን ቀድሞ የሚመጣው ታሪካዊ ቅርሶቻችንን በቦታው ተገኝቶ ስለመመልከት፣ አለፍ ሲልም የአምልኮ ሥፍራዎችን ስለመጎብኘት ሊሆን ይችላል። ለዚህም ነው በኢትዮጵያ ስለ ቱሪዝም በኤሌክትሮኒክስና በህትመት ሚድያ፣ በፖስተር፣ በበራሪ ወረቀት፣ በብሮሸር፣ በቱሪስት ጋይድ (book) በብዛት የምናስተውለው ስለ አክሱም ሃውልት፣ ስለ ላሊበላ ውቅር አብያተ-ክርስቲያናት፣ ስለ ጎንደርና ጀጎል ግንብ፣ ስለ ሶፍ ኦመር ዋሻ የምናየው። አዎ! እርግጥ ነው። እነዚህም ታላላቅ የቱሪስት መስህብ ቦታዎች ናቸው።

በአሁኑ ጊዜ ግን፣ ይሄ ግንዛቤ በፍጥነት እየተቀየረ ቱሪዝም ከላይ ከጠቀስናቸው ዘርፎች በተጨማሪ ብዙ እና በከፍተኛ ፍጥነት እያደጉ የሚገኙ ዘርፎችን እያበጀ እየጨመረ መሆኑን እየተረዳን ነው። በአሁኑ ሰዓት የሙዚቃ ቱሪዝም፣ የቱሪዝም አንድ ዘርፍ ነው ብቻ ተብሎ በቀላሉ የሚታለፍ ጉዳይ አልሆነም። የሙዚቃ ቱሪዝም በውስጡ ብዙ እና በጣም ጠቃሚ ንዑስ ዘርፎች ያሉት የቱሪዝም አንዱ አካል ሆኗል። ከዚህ ባለፈም በፍጥነት እያደገ እና እየተስፋፋ እየሄደ ያለ የቱሪዝም የስበት ማዕከል (Center of attraction) ሆኗል።

የሙዚቃ ቱሪዝም ዘርፍ ታሪካዊ አመጣጡ በአስራ ስድስተኛው እና በአስራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን የአውሮፓ ልሂቃን፣ የአውሮፓን ባህል፣ ቅርስ፣ ሥነ-ህንፃ፣ ሥነ-ጽሑፍና መልክዓ-ምድር ለማጥናት፣ ለመመራመርና ለመዳሰስ ከሚደረገውና ከሁለት እስከ አራት ዓመታት ይወስድ ከነበረ የጉዞ አካል ውስጥ መሠረቱን እንዳገኘ ጥናቶች ይጠቁማሉ። ጉዞ አድዋን እንደ ኢትዮጵያዊ አብነት መጥቀስ ይቻላል።

ይህ ታላቁ ጉዞ (grand tour) በመባል የሚታወቀው ጉዞ፣ የዘመናዊ ቱሪዝም የተጀመረበት ወቅትም ነው ይባላል። በተለይም ከእንግሊዝ አገር በመነሳት መላውን የአውሮፓ አኅጉር የሚዞር ነበር። ጉዞው ወይም ጉብኝቱ ትምህርታዊና አዝናኝም ነበር። ሙዚቃን ከዚህ ታላቅ ጉዞ ጋር ያገናኘው ምክንያት ደግሞ ግልፅ ነው። ተጓዦቹ በየተጓዙባቸው ወይም በጎበኟቸው አካባቢዎች በሚካሄዱ የሙዚቃ ዝግጅቶች ላይ እየተገኙ መመልከትን፣ መደነስን፣ አንዳንዴም መዝፈንን ያዘወትሩ ስለነበር ነው።

በዚህ እና በሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች፣ የባህር ዳርቻ ‹‹ሪዞርቶች››፣ ታላላቅ ሆቴሎች፣ የተለያዩ የሙዚቃ ዓይነቶችን በቋሚነት ያቀርቡ ጀመር። ቱሪስቶችም ከመዝናናት በተጨማሪ እነዚህን የሙዚቃ ድግሶችና ፌስቲቫሎች ለማየት ፕሮግራም እየያዙ መጎብኘትን ተያያዙት።

በ19ኛው ክፍለ-ዘመን ወደ አውሮፓ እና አሜሪካ ታላላቅ ከተሞች ቱሪስቶች ኦፔራን፣ ባሌት ዳንስን፣ ቴአትሮችን፣ የሙዚቃ ዝግጅቶችን በየመናፈሻ ቦታዎች ወታደራዊ ማርሽ-ባንዶች (March Band) የሚያቀርቧቸውን ሙዚቃዎችና ትርዒቶች እየመረጡ ለመጎብኘት ይጎርፉ ጀመረ።

በ1920ዎቹ ደግሞ የአሜሪካ እና የአውሮፓ ቱሪስቶች ወደ ፓሪስ (ፈረንሳይ) እንዲጎርፉ ያስገደዱ የምሽት ክበቦች፣ የቴአትር ቤቶች፣ የጃዝ ሙዚቃ የዳንስ አዳራሾች እና የተለያዩ ትርዒቶች ተስፋፉ። በዚህም ፓሪስ ‹‹የጥበባት ማዕከል›› የሚል ስያሜ ተሰጣት። በጥበብ ሰበብ ቱሪስት የሚጎርፍባት ከተማም ሆነች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በአውሮፓ በተከሰተው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሳቢያ፣ የቱሪዝም ዘርፍ በጣም ተዳክሞ የነበረ ቢሆንም፣ ከጦርነቱ ማግስት ወዲህ ደግሞ እንደገና ማንሰራራት ጀመረ። ለቱሪዝም በተለይም ለሙዚቃ ቱሪዝም ዘርፍ ማደግና መስፋፋት ዋና-ዋና ምክንያቶች ተብለው የሚጠቀሱት ደግሞ የሚከተሉት ናቸው።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ለጥቆ የመጣው የኢኮኖሚ ውድቀት፣ ሠራተኞች በአሰሪያቸው ደመወዝ እየተከፈላቸው ሆኖም ግን ሥራ ያልነበራቸው በመሆናቸው ምክንያት፣ እነዚያን ረዣዥም የእረፍት ቀናት በጉብኝትና በመዝናናት እንዲያሳልፉ ይገደዱ ስለነበር ነው።

ከዚህ በተጨማሪም የመኪና ፋብሪካዎች መስፋፋት፣ ብዙ ሰው የግል መኪና ባለ ንብረት መሆን፣ (1960) የተለያዩ የትራንስፖርት አውቶብሶች እና ርካሽ የአየር ትራንስፖርት መኖር፣ መንግስትም እነዚህን መልካም አጋጣሚዎች በመጠቀም አዳዲስ የቱሪዝም ዘርፎችን እያስተዋወቀ፣ ቱሪስቱ ትኩረት እንዲሰጣቸው ከፍተኛ ጥረት ያደርግ ስለነበር ነው።

ለመሆኑ የቱሪስቶች መስህብ የሆነው የሙዚቃ የቱሪዝም ዘርፍ ምን ዓይነት ነው? የሙዚቃ ቱሪዝም ዋናው ጉዳይ ወይንም አጀንዳ የጥንቱን ወይም የቀድሞውን ማሳየቱ ማስታወሱ ነው። ያለፈውን ናፍቆት (Nostalgia) የመወጣት መልክ ያለው ዘርፍ ነው። በድምፅ፣ በቃላት፣ በምስል ያለፈውን ትውስታ ወይንም ትዝታ፤ የስሜት ትስስር የመፍጠር አቅሙ ነው። ይህም ማለት ሙዚቃ በውስጡ የቀደምቱን የሚያስታውስ የቅርስ ብሎም የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ፈጥሯል ማለት ነው።

የቀድሞ ባህላዊ እና ሙዚቃዊ ሥራዎች ሂደቶች አሁን እንዲመስሉ፣ በሙዚየሞችና በድምፃውያን መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ባሉ ቁሳቁሶች ወይንም አልባሳትና ሥራዎች ዝነኛ ድምፃውያን ሙዚቃዎቻቸውን የሰሩባቸው ስቱድዮዎች በታወቁ ዘፈኖች በተጠቀሱ የቦታ ወይም የሀገር ስሞች ወዘተ… ለቱሪስት ክፍት ተደርገው ይዘከራሉ።

የገቢ እና የቱሪስት ፍሰት መጠን በብሪታኒያ

ስለ ገቢ እና ስለ ቱሪስት ፍሰት መጠን በ2015 በታላቋ ብሪታንያ (UK) ከተጠናው ጥናት በከፊል ለመጥቀስ ስንሞክር የሚከተለውን አኃዝ እናገኛለን። ሙዚቃን ማዕከል አድርጎ ከሙዚቃ ጋር የተገናኙ ቦታዎችን ወይም ትርዒቶችን ለመጎብኘት ከሀገር ውስጥና ከውጭ አገር የሚጎርፉ ቱሪስቶች ቁጥር በ2015 ዓ.ም. 9.5 ሚሊዮን ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ከነበረው አኃዝ በ38 በመቶ እድገት ማሳየቱን እና በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ቱሪስቱ የሚያወጣው ወጪ መጠን 1.9 ቢሊዮን ፓውንድ እንደሚገመትና ከአርባ ሺህ ያላነሰ የቋሚ ሠራተኛ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ጥናቶች ይጠቁማሉ። ይኼን እንደ መንደርደሪያ ካየን ዘንዳ፣ እግረ መንገዳችን ዝርዝር አብነቶችን ደግሞ እንጨምርበት።

አሜሪካ መምፈስ፤ የሙዚቃ ቱሪዝም ዘርፍ፣ የቱሪስት

የጉብኝት ሥፍራዎች እና አመታዊ የገቢ መጠን፤ _ መምፈስ የብሉስ አገር፣ የሮክ እና ሮል የትውልድ ሥፍራ

መምፈስ በአሜሪካ ደቡባዊ ምዕራብ ጥግ በቴኒሲ ክፍለ-ግዛት ሁለቱ የአሜሪካ ታላላቅ ወንዞች – ሚሲሲፒ እና ወልፍ – ከሚገኙበት በስተ ደቡብ በኩል ትገኛለች። በ1819 በጥቂት የአሜሪካ ባለፀጎች የተመሠረተችው መምፈስ ከቴኒሲ ክፍለ-ግዛት ዋና ከተማ ከናሽቪል ቀጥላ በህዝብ ብዛት እና በትልቅነቷ በሁለተኝነት ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ይህቺ በዓባይ ወንዝ (Nile) ዳርቻ ተቆርቁራ የጥንታዊት ግብፅ ዋና ከተማ ከነበረችው መምፈስ ስያሜዋን የተጎናፀፈች የሰሜን አሜሪካ ከተማ፣ በ2016 በተደረገው የህዝብ ቆጠራ 652‚757 ህዝብ እንደሚኖርባት ተረጋግጧል። በአንፃሩ በ2016 በተደረገው ሌላ የቱሪስት ፍሰት ጥናት በጎብኚ ከሚጨናነቁት ሰባት የአሜሪካ ከተሞች ተርታ ተመድባለች። የቱሪስት ፍሰቱ በዓመት ከ10.5 ሚሊዮን በላይ ደርሷል። በዓመት ከ3.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ከቱሪዝም ታገኛለች።

መምፈስ ብዙ እና የተለያዩ የቱሪስት መስህቦች አሏት። ያም ሆኖ የአብዛኛው ጎብኝዋ ትኩረት እና የጉብኝቱ ምክንያቶች ግን ሙዚቃ እና ከሙዚቃ ጋር ግንኙነት ያላቸው የቱሪስት መስህቦች ናቸው። የዓመታዊ ገቢ የአንበሳው ድርሻ የሚገኘውም ከዚሁ የሙዚቃ ቱሪዝም ዘርፍ ነው። ይኸውም ሰባት መቶ ሚሊዮን ዶላር ነው።

ከ2.1 ሚሊዮን በላይ ለሚቆጠሩት ጎብኝዎች እና ለሰባት መቶ ሚሊዮን ዶላር ዓመታዊ ገቢ ምክንያት የሆነው ከሙዚቃ ቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘው ገቢ ነው። ጉዳዩ እንዲህ ነው እንግዲህ። መምፈስ ከአሜሪካ የሙዚቃ ታሪክ እድገትና እንቅስቃሴ ጋር ስሟ አብሮ የሚነሳ ከተማ ናት። መምፈስ የሶል፣ የብሉስ ማዕከል እና መላው አሜሪካውያን በአንድ መንፈስና በእኩል ስሜት የኛ ነው የሚሉትን የ‹‹ሮክ እና ሮል›› ሙዚቃ ውልደት እና እድገት ያመጣች መዲና ናት። እንዲሁም ለዚህ የሙዚቃ ውልደት እና እድገት አቀንቃኝ እና ፊታውራሪ የነበሩት ኤልቪስ ፕሪስሊ፣ አሪታ ፍራንክሊን፣ ጄሪ ለዊስ፣ ዊልያም ቢል፣ ሳም ኤንድ ዴቭ እንዲሁም ቤቢ ኪንግ ሥራዎቻቸውን የጀመሩበት፣ ያስተዋወቁበት፣ ግማሾቹም የተወለዱባት፣ ያደጉባት እና በመጨረሻም የቀብር ሥፍራቸው ናት- መምፈስ።

መምፈስ ከላይ በተጠቀሱት ጥቂት አብነቶችም ምክንያት ስለ ሙዚቃ ለማወቅም ሆነ የሙዚቃ ቅርሶችን ለመጎብኘት የሚጎርፈው የቱሪስት ፍሰት ብዙ ነው። ስለዚህም ነው የሙዚቃ ቱሪዝም ዘርፍ ማሳያ አብነት የሆነችው።

በመምፈስ ከተማ ቱሪስቶችን ከሚስቡት ጥቂት የሙዚቃ ዘርፍ (የቱሪስት ስህበት ማዕከሎች) የሚከተሉት ይገኙበታል።

 

የፌስቲቫል ቱሪዝም _“መምፈስ በግንቦት ወር”

መምፈስ ብዙ ዓመታዊ ፌስቲቫሎች አሏት። የሙዚቃ፣ የቴአትር፣ የፊልም፣ የምግብ፣ የሥዕል ወዘተ… ፌስቲቫሎች ይገኛሉ። ከነዚህ መካከል ግን ለ30 ተከታታይ ቀናት የሚካሄደው እና ላለፉት 45 ተከታታይ ዓመታት በመካሄድ ላይ የሚገኘው መምፈስ በግንቦት ወር /Memphis in May/ የተሰኘው ፌስቲቫል ዝነኛው እና ትልቁ ነው።

“መምፈስ በግንቦት ወር” የተሰኘው ፌስቲቫል አንድ መሪ ቃል አለው። ‹‹ዓለምን ወደ መምፈስ፣ መምፈስን ወደ ዓለም ማምጣት›› ‘bringing the world to Memphis and Memphis to the world’ የሚል ነው።

ከላይ እንደተጠቀሰው ይህ ፌስቲቫል በየአመቱ ለተከታታይ 30 ቀናት የሚካሄድ ሲሆን፣ በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ተከፍሏል።

የመክፈቻው፤

የቢል ጎዳና የሙዚቃ ፌስቲቫል / Beal street music festival/ ይሰኛል። ስለ ቢል ጎዳና የሙዚቃ ፌስቲቫል ከማቅረቤ በፊት ስለ ቢል ጎዳና እና ስለ ፌስቲቫሉ ታሪካዊ ስያሜ ባጭሩ ላስቀምጥ። በዚያውም ለምን የሙዚቃ ቱሪስት እንደሚጎርፍ ግልፅ ስለሚሆን። መምፈስ ከተማ የያዘችው የሙዚቃ፣ የባህልና የቅርስ ስሜቱን ጥልቀት ለመረዳት የፈለገ ሰው የሚጠበቅበት አንድ ነገር ብቻ ነው። ወደ ቢል ጎዳና ጎራ ማለት።

ቢል ጎዳና መምፈስ ከተማ መሐል ከሚሲሲፒ ወንዝ ወደ ምስራቅ በግምት ሦስት ኪሎ ሜትር ላይ የተዘረጋ መንገድ ነው። በዚህ ጎዳና ዳርና ዳር በሚገኘው የእግረኛ መንገድ ስሚንቶ ላይ በአሜሪካ የሙዚቃ ታሪክ እና እድገት ስማቸው ጎልቶ የሚታወቅ ሙዚቀኞች ስም ተቀርፆ እናገኛለን። w.c Handy, BB-king, Elvis Presly, Jerry Lewis, Sam and Dave እና ሌሎች ከ126 በላይ የሆኑ ስመ ጥር ሙዚቀኞች ስሞች ተጽፈው እናገኛለን። መምፈስ እነዚህ ስመጥር ሙዚቀኞች በሙሉ የተወለዱባት፣ ያደጉባት ብዙዎቹም ሞተው የተቀበሩባት ከተማ ናት።

ቢል ጎዳና ከብሉስ ሙዚቃ ውልደት እና እድገት ጋር በእጅጉ የተቆራኘም ቦታ ነው። የጥቁር ተጓዥ ሙዚቀኞች በዚህ ጎዳና መንገድ ዳር ሙዚቃ መጫወት ከጀመሩ ከ1860ዎቹ ወዲህ ቢል ጎዳና ሁሉን የሙዚቃ ዓይነቶች የሚገናኙባት ማዕከል ሆና ቆይታለች። በዚህም ምክንያት በ1940 በዋናው መንገድ ዳር እና ዳር የሚገኙ የብሉስ እና የጃዝ ሙዚቃ ክለቦች እንደ አሸን ፈሉ። ስለዚህም በ1977 ዓ.ም. የአሜሪካ ኮንግረስ ቢል ጎዳናን የብሉስ መኖሪያ (መፈጠሪያ) “home of the blues” ብሎ ሰየማት። በሜይ 23፣ 1966 ደግሞ National Historical Land Mark የሚል ተጨማሪ ሹመት አገኘች። ይኼ ጎዳና አሁን የመምፈስ በግንቦት ወር የመክፈቻው ፕሮግራም የሚካሄድበት ስያሜው የተወሰደበት ነው።

የቢል ጎዳና የሙዚቃ ፌስቲቫል በየአመቱ ግንቦት የመጀመሪያ ሰባት ቀናት የሚካሄድ ነው። ይኼም የመምፈስ በግንቦት ወር የዋናው ፕሮግራም የመክፈቻ ወይም እንደ መክፈቻ የሚቆጠር ዝግጅት ነው። ይኼ ፌስቲቫል በየአመቱ ከአንድ መቶ ሺህ በላይ ቱሪስቶች የሚስብ ሲሆን፣ ከፌስቲቫሉ ፕሮግራሞች ሁሉ አንጋፋው ነው። የአርባ አምስት ዓመታት እድሜ ጠገብ ፌስቲቫል ነው። በዚህ የሙዚቃ ዝግጅት ውስጥ በመላው አሜሪካ ከሚገኙ አንጋፋ ድምፃውያን ጀምሮ በከተማው ውስጥ እስከሚገኙት ታዳጊ ድምፃውያን ጭምር ይሳተፉበታል።

ዓለም አቀፍ ሳምንት

“መምፈስ በግንቦት ወር” ፌስቲቫልን አንድ ልዩ የሚያደርገው በየአመቱ ለአንድ ሀገር የሚሰጠው ስያሜ ነው። ፕሮግራሙ ለሰባት ቀናት ይካሄዳል። በስሙ የተሰየመለት ሀገር፣ ባህል፣ ሙዚቃ፣ ሥነ-ጥበብና የምግብ ዓይነት ይቀርባል።

ይኼ ፕሮግራም የመምፈስ ማኅበረ- ሰብ የሌሎችን ሀገሮች ባህሎች፣ የሥነ- ጥበብ ውጤቶች እና ሌላ ሌላ ልምድ እና ተሞክሮ የሚያገኝበት መልካም አጋጣሚ ነው።

በተለይም በከተማው ውስጥ የሚገኙ የግል እና የመንግሥት ትምህርት ቤቶች፣ የትምህርት ፕሮግራሞች አጋዥ ሆኖ ያገለግላል። ይኼ በየአመቱ የተለያዩ ሀገሮች ትርዒታቸውን በሚያሳይ ጊዜ፣ አንድ መምፈስ ውስጥ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ሁለተኛ ደረጃ የተማረ ተማሪ የአስራ ሁለት የተለያዩ ሀገራት ባህል፣ ሥነ-ጥበብ፣ ልምዶችን ይቀስማል ማለት ነው። ከዚህም አልፎ ስያሜ የተሰየመለት ሀገር፣ ባለ ሃብቶች፣ የንግድ ማኅበረ- ሰብ፣ ጎብኝዎች ከከተማው ታላላቅ ባለ ሃብቶች ጋር የሚደረገው ትውውቅ እና የሚመሰረተው የንግድ ግንኙነት ነው።

ይህ የዓለም አቀፍ ስያሜ እስከ አሁን ድረስ የሰላሳ ስምንት ሀገሮችን ስም ሰይሟል፤ አስተናግዷል። ጃፓን፣ ካናዳ፣ ስዊድን፣ ፈረንሳይ፣ ብራዚል፣ እስራኤል፤ ከአፍሪካ ደግሞ ኬንያ፣ ግብፅ፣ ሞሮኮ፣ ደቡብ አፍሪካ ጥቂቶቹ ናቸው።

የመዝጊያ፡- (ታላቁ ሩጫ)

ታላቁ የአሜሪካ የወንዝ ዳር ሩጫ በመባል የሚታወቀው ነው። ይኸው ከ30 የአሜሪካ ክፍለ-ግዛቶች የተውጣጡ 2000 ሯጮች የሚሳተፉበት ታላቅ ሩጫ፤ በሚሲሲፒ ወንዝ ዳርቻ የሚካሄድ ሲሆን፣ የግማሽ ማራቶንና የአምስት ሺ ሜትር ርቀት የሚሸፍን ነው።

 

የኤልቪስ ፕሪስሊ መኖሪያ ቤት

ግሬስላንድ

የሙዚቃ ቱሪዝም ሌላው ዘርፍ የስመ- ጥሩ ድምፃውያን እና የስነ-ጥበብ ሙያተኞች መኖሪያ ቤቶች የሚጎበኙበት የቱሪዝም መዳረሻ ነው። ለዚህ እንደ ጥሩ ምሳሌ የሚጠቀሰው የኤልቪስ ፕሪስሊ መኖሪያ ቤት ነው። ግሬስላንድ በመባል ይታወቃል። በአሁኑ ሰዓት ወደ ሙዚየምነት ተቀይሮ በማገልገል ላይ ይገኛል። ይኼ ሙዚየም እ.ኤ.አ. ጁን 1982 ለህዝብ እይታ የተፈቀደ በአሜሪካ የታሪካዊ መዝገብ ማኅደር ተመዝግቦ በማርች 27 ደግሞ ብሔራዊ የታሪክ አምድ ተብሎ በሕግ ተሰይሟል።

ግሬስላንድ በታሪካዊ መኖሪያ ቤቶች ጎብኚ ብዛት ከነጩ ቤተ-መንግሥት (White House) ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ይገኛል። በዓመት ከ670,000 በላይ ቱሪስት ይጎበኘዋል። ጉብኝቱ ከመኖሪያ ቤቱ መግቢያ በር ላይ ከሚገኘው መቃብሩ ጀምሮ፣ ሁለቱ የግል አውሮፕላኖቹ፣ ሞተር ብስክሌቱ፣ ካዲላክ መኪናው፣ በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ ለሙዚቃ ስራ የተጠቀመባቸው የሙዚቃ መሣሪያዎች፡- ፒያኖ፣ ጊታር፣ በእረፍት ጊዜ ከጓደኞቹ ጋር የሚዝናናበት የፑል (ካራንቡላ) መጫወቻ፣ አልባሳቱ፣ ሽልማቶቹ፣ የሙዚቃ አልበሞቹ፣ ከተለያዩ ሚድያዎች ጋር ያካሄዳቸው ቃለ-መጠይቆች ወዘተ… ይገኙበታል።

በመኖሪያ ቤቱ አጠገብም ትልቅ የገበያ አዳራሽ ተገንብቷል። ፖስት ካርዶች፣ ቲሸርቶች፣ ኮፍያዎች፣ በቅርፃ-ቅርፅ የተሰሩ ምስሎች፣ የሙዚቃ ስራዎቹ የሚሸጡበት የገበያ ማዕከል …

ሳን ስቱድዮ _ የሮክ እና ሮል ሙዚቃ የትውልድ ስፍራ

ሳን ስቱድዮ የመጀመሪያው የሮክ እና ሮል ሙዚቃ ነጠላ ዜማ የተሰራበት በመላው ዓለም እስከ አሁንም ዝናው የናኘው የታላቁ ድምፃዊ የኤልቪስ ፕሪስሊ የሙያ ማህፀን እናት ስቱድዮ ነው።

ሳን ስቱድዮ ስለ ሙዚቃ እና ስለ ሙዚቃ ስቱድዮ ብዙ እውቀት ባልነበረው ነገር ግን ፍላጎቱ እና የመስራት ፍቅሩ በታደለው በራዲዮ ኢንጂነሩ ሳም ፍሊፕስ እ.አ.አ. በ1950 ዓ.ም ተመሠረተ።

ሳም ከብዙ ትዕግስትና ምኞት በኋላ ህልሙን በማሳካቱ የተሰማው ስሜት ወደር አልነበረውም። በተመሠረተ ማግስት ግን ችግሩም የምስረታው ያህል የነበረው ደስታ መጠን እኩል ነበር። ይኼም የስቱድዮውን ወጪ ለመሸፈን የሚያስችል ገቢ ማግኝት አልቻለም። ስለዚህ የሙዚቃ አልበም ገበያ ላይ ዋጋ አጣ። ከአራት መቶ ኮፒ በላይ መሸጥ አልቻለም። ሆኖም በዚህ ተስፋ ቆርጦ እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም። ስቱድዮው ከተመሠረተበት ዓላማ ውጪ ገቢ ወደሚያስገኝበት ሥራ ተሰማራ። ስለዚህም በመጀመሪያዎቹ አመታት ሳም ስብሰባዎችን፣ ሰርጎችን፣ መዝሙሮችን፣ የቀብር ሥነ-ስርዓቶችን መቅረፁን ተያያዘው። በተጨማሪም በክፍት በር ፖሊሲ (open door policy) የሚል መርህ በመከተል ማንም ድምፁን መቅረፅ የፈለገ ሰው ትንሽ ክፍያ እየከፈለ ይቀርፅ ነበር። “ቦታም ጊዜም ሳይገድበን ሁሉንም ዓይነት ቀረፃዎች እናካሂዳለን” የሚልም መሪ መፈክር ይዞ ታገለ። እንዲያም ታግሎ አልተሳካለትም።

ብዙ ሙከራዎች ሞክሮ ከከሸፈበት በኋላ ተስፋ ቆርጦ ወደ መጠጥና ስካር ገባ። ከዚያም አልፎ ወደ አእምሮ ህሙማን ማገገሚያ ገብቶ የኤሌክትሪክ ህክምና / electric shock treatmenet/ ያገኝ ጀመር። ከብዙ ጥረትና ድካም በኋላም አገገመና ወደ ስቱድዮ ሥራው ተመለሰ። በ1953 ዓ.ም. የመጀመሪያውን የተሳካ አልበም ሠራ። ይህ በገበያ ላይ ከፍተኛ ተደማጭነት ያገኘ ሥራው ደግሞ ሌላ መዘዝ ይዞበት መጣ። የቅጅ መብት ጥሰት አካሂደሃል ተብሎ በመከሰሱ እና ጥፋተኛ ተብሎ ስለተፈረደበት እንደገና ወደ ከፍተኛ ዕዳ ገባ። በዚህ ሰዓት ተስፋ ሳይቆርጥ የተለያዩ ስራዎችን በመስራት እዳውን መክፈል ተያያዘው።

ይሄን ሁሉ ቃኝተን እዚህ ላይ ስንደርስ ስለሙዚቃ የነበረንን ግንዛቤ መፈተሽ የሚገባን ሆኖ እናገኘዋለን። ስለነበረን ግንዛቤ ብቻ ሳይሆን፣ ይህ ከላይ የተገለፀው በእኛም ሀገር እንዲሆን ማን ምን ድርሻ መወጣት ይገባዋል የሚለውን ጭምር መፈተሽ ይጠበቅብናል። እንዲህ ሊሆን የቻለው በዕድልና ባጋጣሚ ስላልሆነ። የሚመለከተው ሁሉ የበኩሉንና የአቅሙን መወጣት ሲችል ነው። እዚህ ጽሑፍ ውስጥ የቀረበው ሀሳብ የሙዚቃ ቱሪዝም ዘርፍ ሊያበረክት ከሚገባው በጣም ትንሹ ነው። ከዚህ በላይ ብዙ እና ተዝቆ የማያልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ብዙ ምሳሌዎችን ማቅረብ ይቻላል።

ሀገራችን በሙዚቃ ቱሪዝም ዘርፍ ብዙ ሊጠቅሟት የሚችሉ መልካም አጋጣሚዎች እያሉ አልተጠቀመችባቸውም። ለምሳሌ የኢትዮጵያ የዜማና የቅኔ አባት የሆነው ቅዱስ ያሬድና የመድረኩ ንጉስ ጥላሁን ገሠሠ የሚዘከሩባቸውን ፌስቲቫሎች ማዘጋጀት ይቻላል። በአርባ ምንጭ ተጀምሮ የነበረው የሺህ ኮከቦች ዓመታዊ የሙዚቃ ፌስቲቫል፣ አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና እና የዓለም ሦስተኛዋ የዲፕሎማቲክ ከተማ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ሊዘጋጅ ስለሚችል አኅጉራዊ ወይም ዓለም አቀፋዊ የሙዚቃ ፌስቲቫል፣ የአድዋ ድል የአፍሪካውያንና የመላው ጥቁር ህዝቦች ድል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሊዘጋጅ የሚገባው የሙዚቃ ፌስቲቫል እና ሌሎች የሙዚቃ ቱሪዝም አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል። ግን አልተጠቀምንበትም። 

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top