የታዛ ድምፆች

መውሊድና የመውሊድ ከበራ

‹‹መውሊድ›› የሚለው ቃል ምንጩ አረብኛ ሲሆን በቋንቋ ትርጉሙ ‹‹የመወለጃ ቦታ ወይም የመወለጃ እለት›› የሚል አለው። በመንፈሳዊ ትርጉሙ ደግሞ ነቢዩ ሙሐመድና የሱፊ ሸኾች የተወለዱበትን ወይም የሞቱበትን እለት ለማሰብ ለሚደረግ ከበራ የተሰጠ ስያሜ እንደሆነ ይታመናል። ‹‹መውሊድ›› የሚለው ቃል ለነቢዩ ሙሐመድና ለሱፊ ሸኾች የልደት ወይም የሞት መታሰቢያ ከበራ ስያሜ በመያዙ የነቢዩ ሙሐመድ ልደት ‹‹መውሊድ አን’ነቢ›› ተብሎ ይጠራል። የዚህ ጽሑፍ ትኩረትም በዚሁ ከነቢዩ ሙሐመድ ልደት ጋር የተያያዘው ይሆናል።

ሀሰን ታጁ እንደሚለው የመውሊድ ከበራ አጀማመርና የከበራው ባህሪ ላይ የተለያየ አመለካከት አለ። ለምሳሌ መውሊድ መከበር የጀመረው በራሳቸው በነቢዩ ሙሐመድ ሲሆን የከበራውም ባህሪ ነቢዩ የተወለዱበትን ቀን በመጾም ነው የሚል አመለካከት አለ። ሁለተኛው ወገን መውሊድ መከበር የጀመረው ነቢዩ ከዚህ አለም ከተለዩ በኋላ በአስራ ሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተጀመረ፣ አከባበሩም መካ ወደሚገኘው ነቢዩ ወደተወለዱበት ቤት ዚያራ/መንፈሳዊ ጉብኝት በማድረግ ነው የሚል አመለካከት አለ።

ሶስተኛው ወገን ሺኣ ፋጢምዮች በሚያስተዳድሯት ግብጽ እንደተጀመረ፣ አከባበሩም ከነቢዩ ሙሐመድ ልደት በተጨማሪ ከሺኣ ወልዮችና ከግዛቱ ኸሊፋዎች ወይም መሪዎች ልደት ማክበር ጋር የተያዘ ነው የሚል አመለካከት አለ። መውሊድ በሱኒ ሙስሊሞች ዘንድ ለመጀመሪያ ጊዜ ኦፊሴላዊና ህዝባዊ ሆኖ መከበር የጀመረው በአስራ ሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማብቂያ በኢራቅ ሰሜናዊ ክፍል በምትገኝ ኤርቤል በምትባል ከተማ ነው የሚል አመለካከትም አለ ይላል ሀሰን አህመድ።

የመውሊድ ከበራ በኢትዮጵያ

በአገራችን የመውሊድ ከበራ በአገሪቱ ከሱፊዝም መስፋፋት ጋር እንደሚያያዝ ይታመናል። ሱፊዎች መውሊድን የአምልኮ ተግባሮቻቸውና የመንፈሳዊ ንቃታቸው ማበልጸጊያ የአንድነታቸው ማጠናከሪያ መሳሪያ አድርገው ይገለገሉበታል። በዚህ አጠቃላይ መንፈስና በተለየ ሁኔታ በአገራችን የመውሊድ ከበራ በአስራ ስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ እንደተጀመረ ይታመናል። የዚህ መውሊድ መስራቹም ከ1734 – 1799 እንደኖሩ የሚነገርላቸው የወሎው ሸኽ ሙሐመድ ሻፊ መሆናቸው ይወሳል።

በሸኽ ሙሐመድ ሻፊ ስም የወጣላቸው አሊምና ሱፊይም እንዲሁ የተሀድሶ አራማጅ ነበሩ። መቀመጫቸውን ጀማ ንጉስ ካደረጉ በኋላ አመቱን በሶስት፣ ሀ) አራቱን ወር እስልምናን ለማስተማር ለ) አራቱን ወር ለዚክር ወይም ለተመስጦ መንፈሳዊ ጉዞ፣ ሐ) ቀሪውን አራት ወር ለጂሃድ – ከሙስሊም ጠላቶች ጋር የመከላከል ጦርነት ለማካሄድ ብለው ከፍለው፣ እስልምናን በማስተማርና ጠላቶቻቸውን በመከላከል ይታወቃሉ። የሸኽ ሙሐመድ ሻፊ ታሪክ ሰፊ በመሆኑ እዚህ ቦታ ከመውሊድ ጋር ባለው የታሪካቸው ክፍል እወሰናለሁ።

ሁሴን አህመድ እንደሚለው፣ ሸኽ ሙሐመድ ሻፊ በአንድ በኩል በሱፊ የማስተማር ስልት እስልምናን የማነጽና የማደስ፣ የሙስሊሞችን አንድነት የማጠናከር አቅሙ ውስን፣ ውጤቱ ትንሽ ሆኖ ስለታያቸው፤ በሌላ በኩል በውስጥና በውጭ የተነሳባቸው የጠላት ጫና እያየለ ስለመጣባቸው ጂሃድን እንደ አማራጭ ለመውሰድ ለዚህም ፈቃድና ምክር ለመቀበልና የሎጂስቲክ እርዳታ ለመጠየቅ ወደ ሂጃዝ ወይም መካ መንፈሳዊ ጉዞ ያደርጋሉ። ሸኹ በሂጃዝ ቆይታቸው ከመካው ሙፍቲ ጋር ተገናኝተው ሀሳባቸውን ያቀርባሉ። ሙፍቲውም ለጂሃድ ጊዜው እንዳይደለ፤ ከጂሃድ ይልቅ ህዝቡን የማሰባሰቢያ መንገድ ፈልጎ ማስተማሩ እንደሚሻል ይገልጹላቸዋል። ሸኹ ከሙፍቲው በተሰጣቸው መልስ ሳይረኩ የነቢዩ ሙሐመድን መቃብርና መስጊድ ለመዘየር ወደ መዲና ይሄዳሉ። በዚሁ መካከል ነቢዩ ሙሐመድ ተገልጠውላቸው አላማቸውን ለማሳካት ከጂሃድ ያልተናነሰ ሌላ መንገድ እንዳለ ያመላክቷቸዋል። ሸኹም ወደ አገራቸው ተመልሰው መውሊድን ህዝባዊ በሆነ መንገድ አቋቋሙ። ‹‹እናም መውሊድ ዐሊሞችን ከተራው ህዝብ የሚያገናኝና የድን ፍቅርን በሺዎች ልቦና ውስጥ የሚያቀጣጥል መድረክ ሆኖ በሀበሻ ታወጀ። ከዚያ በኋላ ላደረጓቸው የጂሃድ ፍልሚያዎች መውሊድን እንደ ግብአት ሳይጠቀሙበት አልቀረም›› ሲል ይገልፃል ሀሰን ታጁ።

በአገራችን የመውሊድ በአል ከአስራ ስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ አንስቶ ህዝባዊ ክብረ በአል ሆኖ ቢቀጥልም እስከ ደርግ ዘመን ድረስ የአገሪቱ ኦፊሴላዊ ክብረ በአል አልነበረም። ከ1967 ወዲህ ግን፣ በህዝበ ሙስሊሙ የቀደመና ተከታታይ ጥያቄ የአገሪቱ ኦፊሴላዊ በአል ሆኖ፣ በረቢየል አወል አስራ ሁለተኛው ቀን መከበር ጀምሯል።

• የመውሊድ ከበራ ቦታ፣ ጊዜና የከበራው ተሳታፊዎች

በአገራችን የመውሊድ ከበራን በሶስት ቦታዎችና ጊዜዎች የማክበር ልማድ አለ። ቦታን በሚመለከት መውሊድ በመኖሪያ ቤት፣ በመስጊድና በሱፊ ማእከሎች ይከበራል። የመውሊዱ ጊዜ ደግሞ ባብዛኛው ነቢዩ በተወለዱበት በረቢየል አወል ወር አስራ ሁለተኛው ቀን፣ ወይም በተወለዱበት ወር ውስጥ በሚገኝ ሰኞ፣ ወይም በማንኛውም ወር በሚገኝ ሰኞ ቀን፣ ወይም በማንኛውም ወርና ቀን ይከበራል።

የመውሊድ ከበራ ተሳታፊዎች እንደ መውሊድ የከበራው ቦታና አቅም የሚወሰን ሆኖ አይነታቸውና መጠናቸው ብዙ ነው። በመኖሪያ ቤት ውስጥ በሚደረግ መውሊድ ቁጥራቸው አነስተኛ የሆኑ በአካባቢው የሚገኙ ሸኾችና ደረሶች፣ ሽማግሌዎች፣ ድሆች፣ ወዘተ. የመውሊድ ተካፋዮች ይሆናሉ። ብዙውን ጊዜ የመውሊዱ ታዳሚ በጥሪ የሚካፈል ነው።

በመስጊድ የሚደረግ መውሊድ በቅርብ ርቀት ለሚገኙ መስጊዶችና የአካባቢ ነዋሪዎች ክፍት ይሆናል። በቤት ውስጥ ከሚደረግ መውሊድ የሚበልጥ ሰው የመውሊዱ ተካፋይ ይሆናል። መውሊዱ መቼ እንደሚደረግ በሁሉም የመስጊድ ኢማሞች በኩል እንዲታወቅ ይደረጋል።

በሱፊ ማእከሎች በሚካሄድ መውሊድ ከሁለቱ የመውሊድ ከበራ ቦታዎች የሚበልጥ ሰው ይካፈላል። ከገጠርና ከከተማ፣ ከቅርብና ከሩቅ ለሚመጡ ሰዎች ሁሉ ክፍት ይሆናል። በእነዚህ ማእከሎች የሚካሄድ መውሊድ ጊዜው ስለሚታወቅ ብዙም ቀስቃሽና አስታዋሽ አያስፈልገውም። ሁሉም ተጠራርቶ በእለቱና በቦታው ይገኛል።

የሱፊ ማእከሎቹ መውሊድ ታዳሚ ቁጥር ብዙ ስለሚሆን፣ ታዳሚዎች በማእከሎቹ ቅጥር ግቢና አካባቢው አጥር ጥግና ዛፍ ስር ወይም ድንኳን ዘርግተው ይጠለላሉ። በአጠቃላይ መውሊድ ከበራ ለሁሉም የህብረተሰብ አይነት ክፍት ነው። አዛውንት፣ ወጣት፣ አዋቂ፣ ህጻን፣ ወንድ፣ ሴት፣ ከተሜ፣ ባላገር፣ የተማረ፣ ያልተማረ፣ ጤነኛ፣ የታመመ፣ ሀብታም፣ ድሃ፣ ባለ ማእረግ፣ ምንዝር፣ የቤት እመቤት፣ የቡና ቤት ሰራተኛ፣ ሙስሊም፣ ክርስቲያን ወዘተ. ሳይለይ ሁሉም  የህብረሰብ ክፍል መሳተፍ ይችላል።

የመውሊድ ከበራ ሂደት

የመውሊድ ከበራ በበርካታ ድርጊቶች ይደምቃል። ከእነዚህም መካከል የሰደቃ ወይም የምጽዋት፣ የጫት ቂምሃና የጀባታ፣ የተመረጡ የቁርአን ክፍሎችና የመውሊድ ምንባብ፣ የመንዙማ ፕሮግራሞች ይገኛሉ። በሰደቃው ወይም በምጽዋቱ ሃብታሞችና ባለ ስለቶች በሬ ወይም በግ፣ ፍየል ወይም ዶሮ አርደው፣ ሌሎች ከቤት ያዘጋጁትን ምግብና መጠጥ (ለምሳሌ፣ ወተት፣ ብርዝ፣ ወዘተ.) ለድሆች ያበላሉ፤ ያጠጣሉ።

በጫት ቂምሃና በጀባታ ክፍለ ጊዜ ሰዎች በቡድን በቡድን ተከፋፍለው ጫት እየተቃመ፣ ቡና እየተጠጣ፣ ጀባታ ወይም ስጦታ እየተሰጠ የታመመው እንዲሽር፣ የደኸየው እንዲከብር፣ መካኑ ልጅ እንዲያገኝ፣ የተራራቀው እንዲቀራረብ፣ የተበደለው እንዲካስ፣ አገር ሰላም እንዲሆን፣ መንግስት እንዲረጋጋና ለህዝብ የሚጠቅም ስራ እንዲሰራ፣ ወዘተ. በምረቃና በእርግማን ስልት ጸሎት ያደርጋሉ።

በቁርአንና በመውሊድ ንባብ ክፍለ ጊዜ ከነቢዩ ሙሐመድ ጋር የተያያዙ ነቢዩ የዓለሙ እዝነትና መሪ፣ ለሰናዮች መልካሙን አብሳሪ፣ ለእኩይ ሰሪዎች አስፈራሪ፣ ለህዝባቸው ሀላልና ሀራሙን አስተማሪ ወዘተ. ሆነው የተላኩ መሆናቸውን በተለይ የሚመሰክሩ የቅዱስ ቁርአን ክፍሎች ይቀራሉ። ስለ ነቢዩ ሙሐመድ ውልደት፣ በህይወት በነበሩ ጊዜ ስለ ፈጸሟቸው ገድሎችና ተአምራት፣ ስለ ባህሪያቸው፣ ወዘተ. በቀደምት አሊሞች የተዘጋጁ እንደ ‹‹በርዘንጅ›› የመሳሰሉ የመውሊድ ኪታቦች መሳጭ በሆነ ስልት ይነበባሉ።

የመንዙማ ክፍል የመውሊዱን ከበራ ሰፊ ጊዜ ይወስዳል። መንዙማ የህዝበ ሙስሊሙ መንፈሳዊና ምድራዊ ህይወት የሚገለጽበት፣ ደግና ክፉው የሚተችበት፣ ድጋፍና ተቃውሞ የሚንጸባረቅበት፣ ትምህርት የሚሰጥበት፣ ቅስቀሳ የሚደረግበት፣ በአጠቃላይ መንፈሳዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ባህላዊ ገጽታዎቹ የሚነሱበት የቃል ግጥም ክፍል ነው። በዚህ የመውሊድ መንዙማ ውስጥም ከመውሊዱ አውድ ጋር የሚገኙ በርካታ ጉዳዮች ይነሳሉ። የመውሊድ መንዙማ ክዋኔ እንደ መውሊዱ ቦታና እንደተሳታፊው ባህሪ ልዩነት አለው። መውሊዱ በቤት ውስጥ ሲከናወን ወንዶችና ሴቶች ተቀላቅለው ወይም በመጋረጃ ተከፍለው የመንዙማ ከበራው ይካሄዳል።

መውሊዱ በመስጊድ ውስጥ ሲሆን ወንዶችና ሴቶች በመጋረጃ ተለይተው ወይም ወንዱም ሴቱም ለብቻ ቡድን ፈጥረው የመንዙማው ከበራ ይካሄዳል። የመውሊዱ ከበራ በሱፊ ማእከሎች ሲሆን ደግሞ ከሰው ብዛትና አይነት የተነሳ በርካታ የወንዶች፣ የሴቶች፣ የወንዶችና የሴቶች ቡድኖች ተፈጥረው ሁሉም በያሉበት የመንዙማውን ከበራ ያካሂዳሉ።

በሱፊ ማእከሎች የሚቀርበው የመውሊድ መንዙማ ከበራ ይዘቶች በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች የሚከፈሉ ናቸው። የመጀመሪያው የመንዙማ ይዘት የፈጣሪን ስጦታዎችና ችሮታዎች እያነሳ የሚያልቅ፤ ነቢዩ ሙሐመድን ገድላቸውን፣ ባህሪያቸውን፣ አካላቸውን በማውሳት የሚያወድስና የሚያሞግስ፣ አያይዘውም ቀደምት የውጭና የአገር ውስጥ ታላላቅ ሰብዕናዎችን የሚያስታውስ ወዘተ. አይነት ነው። ሁለተኛው የመንዙማ አይነት፣ ልዩ ልዩ ፍላጎቶችን ለመሟላት ሲባል የሚፈጸም በተለምዶ የዛር ከበራ የሚባለው አይነት ይዘት ያለው ነው። በዚህ አጭር የመንዙማ ዳሰሳ በመጀመሪያው የመንዙማ ይዘት፣ ከዚህም ከመውሊድ ጋር በተያያዘው ላይ ይወሰናል። የመንዙማ ግጥሞቹ ቋንቋ ከፍታና የዘይቤ አጠቃቀም ምጥቀቱ እራሱን የቻለ ጥናትና ትንታኔ ስለሚጠይቅ በዚህ ዳሰሳ ብዙም ትኩረት አልተደረገበትም።

ነቢዩ ስለተወለዱበት ወር

መውሊድን ለሚያከብሩ ሰዎች ነቢዩ ሙሐመድ ለተወለዱበት ወር የተለየ ክብር አላቸው። ይህ ወር ‹‹ረቢእ›› ተብሎ ይጠራል። ወሩ የአለሙ መሪ ነቢዩ የተወለዱበት፣ ከፈጣሪ ወህይ መቀበል የጀመሩበት፣ ተልእኳቸውን አድርሰው፣ ለህዝባቸው አደራ ሰጥተው ያለፉበት ነው። እናም በመንዙማ ወሩን የነቢዩ ሙሐመድ ማወደሻ፣ ማስታወሻ አድርገው እንደሚከተለው ይገልጹበታል፡-

ረቢእ ተብለህ የምትጠራ፤

የወራት ጓል ንጉስ አውራ፣

ነቢ ባለ ሙሉ ሰብእና፣

እውድጥህ ፈለቁና፣

ሀሴት አዝለህ አስደሰትከን ተስፋ ወልደህ አደመከን፣

ቃል አደራህ ለኛ ከብዷል ውለታህ ክፋይን ገዷል።

 

ስለ መውሊድ

የመውሊድ ከበራ የነቢዩ ሙሐመድ ፍቅርና ውደታ መግለጫ ተገርጎ ይወሰዳል። ቀጥሎ ከዚህ ሀሳብ ጋር የተያያዙ ሁለት የመንዙማ ግጥሞች በምሳሌነት ቀርበዋል። የመጀመሪያው ‹‹ሀ›› የመንዙማ ግጥም የነቢዩን መውሊድ ማውጣት ለነቢዩ ፍቅር መገለጫ መሆኑን ይገልጻል። ሁለተኛው ‹‹ለ›› ምሳሌ ደግሞ መውሊድን በማንኛውም ጊዜ ማውጣት እንደሚቻል፣ በሰማይ ቤትም ትልቅ ምንዳና ደረጃ እንደሚገኝበት ይሰብካል።

ሀ) ሌላም መሪ የለው ነቢን ለሚወድ፣ ዘንበል ላላለ ተሀቁ መንገድ፣ ነቢ ሲዘከሩ ራህመቱ ሲወርድ፣ መሀባው ይመራል ማውጣቱ መውሊድ የዊላዳውን ወር ቀኑን መአዘሙ ሙስጠፋ ነቢ የሙላው ኢማሙ።

ለ) በማንም ቀን ቢሆን መውሊድ የሚያወጣ፣ አኼራ ያገኛል ምንዳውን አያጣ፣ ከጌታ ይሰጣል ምንዳ ትልቅ እጣ፣ እላይኛው ጀነት ይባላል ሂድ ውጣ፣ መውሊድ የሚያወጣ ትልቅ ነው መቃሙ፣ ሙስጠፋ ነቢ የሙላው ኢማሙ።

የነቢዩ አካላዊ ገጽታ

በመውሊድ መንዙማ የነቢዩ ሙሐመድ አካላዊ ገጽታ እየተነሳ ይታወሱበታል። ለምሳሌ ቀጥሎ በቀረበው የመንዙማ ግጥም የነቢዩ ሙሐመድን አይን፣ ፊት፣ ጸጉር ይገልጻል። አይናቸው በኑር (በብርሃን) እንደተኳለ፣ ፊታቸው የጨረቃ ብርሃንን እንደሚያስንቅ፣ ጸጉራቸው የሀር ጉንጉን እንደሚመስል፣ ስእላዊ በሆነ ጥበብ ተስሎ እናያለን።

የመድናውን ባየነው አይኑን

በኑር አረንጓዴ የተኳለውን

ፊቱ ከጨረቃ የሚያበራውን

ፀጉሩ የሚመስለው የሀር ጉንጉን

ብሎ ያወደሰው ጦሀው ያስኔ።

ታሪካዊ ቦታቸው

ከነቢዩ ሙሐመድ ውልደትና መንፈሳዊ ጉዞ ጋር በተያያዙ ታሪካዊ ቦታዎችና ድርጊቶች እየተነሱ ነቢዩ የሚታወሱባቸው የመንዙማ ክፍሎች አሉ።

የጌታ ሚነኑ የጌታ ከረሙ

ራህመት ይውረድብሁ አህመድ

ሙከረሙ የተወለድኩበት እንዴት ነው ሀረሙ?

እንዴት ነው አረፋው እንዴት ነው ዘምዘሙ?

ሶፍዋው እና መርዋው መሽዓረል ሀረሙ፣

ሁሉ እሚያለቅስበት ብሎ ዋኔ ዋኔ!

በዚህ የመንዙማ ግጥም የአረብኛ ቃሎች ይገኛሉ። ቃሎቹ በግጥሙ አውድ ‹‹ሚነን›› ከፈጣሪ የሚሰጥ ጸጋ፣ ‹‹ከረም›› ከፈጣሪ የሚሰጥ ችሮታ፣ ‹‹ሙከረም›› የተከበረ ወይም ክብር የሚሉ ትርጓሜ አላቸው። እነዚህ ቃሎች ነቢዩ የፈጣሪ ጸጋ፣ የፈጣሪ ችሮታ፣ ተደርገው የተገለጹባቸው ናቸው። ‹‹አረፋ››፣ ‹‹ሶፋና መረዋ››፣ ‹‹ዘምዘም›› የሚባሉት ደግሞ የቦታ ስሞች ሲሆኑ፣ የእስልምና መሰረቶች ከሆኑት መካከል የሀጅ ስርዓት የሚፈጸምባቸው ናቸው።

የነቢዩ ባህሪ

በመውሊድ መንዙማ ነቢዩ ሙሐመድ በባህሪያቸው ይታወሳሉ። ቀጥሎ በቀረቡት የመንዙማ ግጥሞች ነቢዩ በታጋሽነታቸው፣ በቀጥተኛነታቸው፣ ከራሳቸው በላይ ለሌላው ቅድሚያ የሚሰጡ በመሆናቸው፣ በቀብር ወቅት ለተከታዮቻቸው አማላጅ የሚቆሙ በመሆናቸው ይወደሳሉ፣ ይታወሳሉ።

ከሁለመናውም ሶብረኛ ነበሩ

ዘንበልም አይሉ ምንም ቢቸገሩ

እራትዎን ሰጥተው ጦምዎን የሚያድሩ

ለነብስዎ ትተው ለሰው የሚጥሩ

ሰይድ ያሲን ኑሩ ጅውሀሩ ጅውሀሩ።

ጥንፍፉ ሙስጦፋ ሙሀመድ አራጋው፣

አለ ነቢ ማነው ሽብር የሚያራጋው፣

ተወደድኩ ብሎ ሌት ቀን ያልዘነጋው፣

የጥሜቱን ሌሊት ዊላዳው ያነጋው።

ያላህ አፈ ንጉስ ያላህ ቢትወደድ፣

ኧረ የት ይገኛል እንደ ሙሐመድ፣

ወዳጅ የሚረዳው ሲገቡ በለህድ።

የነቢዩ ፍቅር

በመውሊድ መንዙማ ለነቢዩ ፍቅር የሚገለጽበት አይነት ወይም መንገድ ይዘረዘራል። በሚከተለው የመንዙማ ግጥም ሰባት አይነት የነቢዩ ፍቅር መግለጫዎች እናገኛለን።

ውደታ ያደባው ቋንቋው ብዙ ነው፣

በዕዱ ነቢ ነቢ በዕዱ ሳኪት ነው፣

በዕዱ ሱንይ ነው በዕዱ ዛኪር ነው፣

እኩሌታው በጦም ኡምሩን ገፊ ነው፣

በዕዱ ሌት ቀን ሶላት እረፍት የለው፣

በዕዱ ሰው ጋር ሆኖ ውስጡን ኸሪብ ነው።

ያረሱሊሂ በዝቷሌ ናፋቂው፣

እጅግ ሰው ተጎዳ ቧግቶ እሚበላው፣

እሚያለቅሰው በዝቷል ቸግሮት መላው፣

ውሰዱት ነቢ በሀድራ መኪና።

በመንዙማው የተዘረዘሩ የነቢዩ የፍቅር መግለጫዎች የሚከተለውን ይመስላሉ።

1) በዕዱ/እኩሉ ‹‹ነቢ ነቢ›› እያለ ሌት ቀን ስማቸውን የሚጠራ፤

2) በዕዱ/እኩሉ ሳኪት ወይም ዝምተኛ፣

3) በዕዱ/እኩሉ ‹‹ሱንይ›› የሳቸውን መንገድ ተከትሎ የሚኖር፤

4) በዕዱ/እኩሉ ዛኪር ወይም አወዳሽ፣

5) በዕዱ/እኩሉ ጾም አዘውታሪ፣

6) በዕዱ/እኩሉ ሌሊቱን በስግደት የሚያሳልፍ፣

7) በዕዱ/እኩሉ ‹‹ኸሪብ›› በአካል ከሰው ጋር ሆኖ ውስጡ ወይም ልቡ ወደእሳቸው የሸፈተ ባህሪ ያላቸው አይነቶች ናቸው።

የመውሊድ ፋይዳው ምንድነው?

የመውሊድን ፋይዳ በተለያየ መንገድ ከፍሎ መመልከት ይቻላል። የመጀመሪያው፣ መንፈሳዊ ፋይዳው ነው። ከዚህ ቀደም እንደተገለጸው በአገራችን መውሊድ ሲቋቋም ህዝበ ሙስሊሙን በማሰባሰብ እምነቱን እንዲያውቅና ሃይሉን እንዲያጠናክር ተብሎ ነበር። ዛሬም ለዚሁ ተግባር ለማዋልና ለማስቀጠል የሚያስችለው ሁኔታ እንዳለ የሚያምኑ አሉ።

የመውሊድን ፋይዳ ከማህበራዊ ግንኙነት ጋር የሚያያይዙትም አሉ። በመውሊድ ከበራ ሰደቃ ይካሄድበታል፤ በዚህም ሀብታምና ድሃ ይገናኙበታል፣ ያለው ለሌለው የፈጣሪውን ውደታ ፍለጋ ምጽዋእት ይሰጥበታል ይላሉ። ከዚህም በተጨማሪ የማህበራዊ ግንኙነትና ትስስር ይጠናከርበታል የሚሉ ወገኖች አሉ።

የመውሊድ ከበራ ባህላዊ ፋይዳ እንዳለውም ይታመናል። በመውሊድ ላይ የሚቀርቡ ልዩ ልዩ መንዙማዎች በአንድ በኩል ፈጠራዎች ሲሆኑ እንዲህ አይነቱ ፈጠራ እንዲበለጽግ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ይላሉ። በሌላ በኩል መንዙማዎቹ በዜማና በአጀብ የሚፈጸሙ በመሆናቸው የተዝናኖትና የፍስሀ አገልግሎት ይገኝበታል ይላሉ።

መውሊድ በአግባቡ ከተያዘ ወደ ሃላል ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ማደግ እንደሚችል የሚያምኑ አሉ። በዚህም አገርንና የአካባቢውን ህብረተሰብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ወደሚሆኑበት ደረጃ ማሸጋገር ይቻላል።

በመውሊድ ላይ የነበረና ያለ አመለካከት

በተቀረው ዓለምም ሆነ በአገራችን ሙስሊሙ ልሂቃን መካከል መውሊድን በሚመለከት አራት አመለካከቶች ይገኛሉ። እዚህ ላይ የሁሉንም የመከራከሪያ ሀቲቶች (discourses) ለማቅረብ አልሞክርም። ይሁንና ጥቅል ሀሳቦቻቸው በሚከተሉት ይዘቶች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ናቸው።

ሀ) መውሊድ ከጊዜ በኋላ የተፈጠረና ከእስልምና አስተምህሮ ውጭ ነው የሚል አመለካከት አለ።

ለ) መውሊድ በነቢዩ ሙሐመድ የተጀመረና እስላማዊ መሰረት ነው የሚል አመለካከት አለ።

ሐ) መውሊድ በልማድ የተፈጠረ፣ ፈጠራውም የተቀደሰ ፈጠራ ‹‹ሱና ሀሰና›› ነው የሚል አመለካከት።

መ) መውሊድ በልማድ የተፈጠረና የተወደደ ከመሆኑ ጋር በሂደት ከእስልምና አስተምህሮ የወጡና ያፈነገጡ ድርጊቶችና እምነቶች የተቀላቀሉበት ስለሆነ መታደስ ይኖርበታል የሚል አመለካከት ይስተዋላል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top