አጭር ልብወለድ

የአሐድ ሐአ’ም ቀብር

(በቤንጃሚን ታሙዝ)

ትርጉም:- መኩሪያ መካሻ

አሐድ ሐአ’ም የሞተው ገና የሰባት ዓመት ልጅ እያለሁ ነው። ስለ አሐድ ሐአ’ም ምንም የማውቀው ነገር ባይኖረኝም፤ ስለ እሱ የሰማሁት ከባለ ግሮሰሪው ሞልቻድስኪ ነበር። አሐድ ሐአ’ም በሚኖርበት ሰፈር ፈረሶች፣ ጋሪዎችና አውቶብሶች እንዳያልፉ ታግደዋል፤ ምክንያቱም ድምፃቸውን መቋቋም የሚችል አልነበረምና። ምንም አይነት ትራፊክ በቤቱ ደጃፍ እንዲያልፍ አይፈቅዱም-ፖሊሶቹ። ይህ ሁኔታ እጅግ ስላስደመመኝ አሐድ ሐአ’ም ማን እንደሆነ መረጃ መሰብሰብ ገባሁ። በከተማው እጅግ የታወቀና የተከበረ ሰው መሆን አለበት አልኩኝ።

ሁሉም ጉዳይ እጅግ ቢያስደንቀኝም፤ ደግሞም በጥቂቱ ሳያሳስበኝ አልቀረም። ውስጠ- ምስጢሩን መመርመር ያዝኩ። ወላጆቼ ከፓሪስ ከሚመጣው የሩሲያኛ ፐስሌዲኒይ ኖቬስት ጋዜጣ በቀር ሌላ አያነቡም። ጋዜጣው ስለ አሐድ ሐአ’ም አንዲት ቃል እንኳ አስነብቦ አያውቅም። ዳሩ ግን እነሱም ቢሆኑ ወሬ የሚሰሙት ከሽማግሌው ሞልቻድስኪ ነው።

እሱ ከዋርሶ የሚመጣውን ሔይንት የተሰኘ ጋዜጣ ያገኛል። በዚያ ጋዜጣ ላይ ደግሞ የአሐድ ሐአ’ም ታሪክ፣ የፖሊስ እና ጋሪዎቹ እንዲሁም ሌሎች ታሪኮች ነበሩበት። ሰፈሩ ሁሉ በዚህ መንገድ ነው ስለ ታሪኩ የሚያውቀው እና በኋላም ወሬውን የሚጠርቀው። በእነዚያ ጊዚያት እንኖር የነበረው ኤፒሲ በተሰኘውና በእንግሊዝ-ፍልስጤም ዳርቻ መንደር ነው። ይህም አረቦች የሚኖሩበትን የማንሺየህ መንደር በሚያዋስነው ስፍራ ሲሆን አረቦቹ ስለ አሐድ ሐአ’ም ሰምተው አያውቁም።

ከአካባቢው መንደርተኛ እኔና ሞልቻድስኪ ብቻ ነን ስለዚህ ታሪክ የምናውቀው። የታሪኩን መጨረሻ ለማየት በይበልጥ የጓጓሁት ደግሞ እኔ ነኝ።

ሽማግሌውን ሞልቻድስኪን አልወደውም፤ ደግሞም እፈራዋለሁ። ከሱቅ አንድ ከረሜላ የሰጠኝ እንደሆን ከጉንጭ ላይ ሙዳ ስጋ ቆርሶ የመውሰድ ያህል ይቆናጠጣል። ሁሌም ድርጊቱ እንዲህ ነው። ከቃላት በቀር ምንም ነገር በዋዛ አሳልፎ አይሰጥም። ጠንካራ ጎኑ መለፍለፍ ነው፤ አንድ ነገር ከጠየቅኩት ሁሌም መልስ ይሰጠኛል። እናቴ ሁሌም ስራ ብዙ በመሆኗ አባቴም ከስራው በቀር በሌላ ነገር ውስጥ ጥልቅ ስለማይል ዝርዝር መልስ የሚሰጠኝ ሞልቻድስኪ ነው። ሆኖም የእሱ ነገር ስሜት ሰጥቶኝ አያውቅም። እንዲያውም አባቴ ነገሩ እርባና ቢስ ነው ብሎ ስላጣጣለብኝ እንጂ ስለ ሁሉም ጉዳይ ማለትም ስለ አሐድ ሐአ’ምና ስለ ፖሊስ ከእሱ አስቀድሜ ማወቅ እችል ነበር። ስለዚህ ሌላ ምርጫ ስለሌለኝ ወደ ሞልቻድስኪ ሄጄ በሔይንት ጋዜጣ ስለተፃፈው ነገር እጠይቀዋለሁ።

ቤንጃሚን ታሙዝ

ቤንጃሚን ታሙዝ

በመጀመሪያ ሰሞን ሁሉንም ነገር በዝርዝር ፃፉ። አሐድ ሐአ’ም መታመሙን፣ መልካም ሁኔታ ላይ እንዳልሆነ፣ ግን ደግሞ፤ ፍፁማዊ ፀጥታን እንደፈለገና ፖሊስም በዚሁ የተነሳ ክብካቤ እንደሚያደርግለት ሃተታ አቀረቡ። ስለዚህ ጉዳይ እንኳን አስቀድሜ ነግሬያችኋለሁ። በኋላ ደግሞ የጤናው ሁኔታ ይበልጥ መታወኩን እና ዕውነታውን ሁሉ ዘክዝከው ማውጣታቸውን ቀጠሉ።

አሐድ ሐአ’ም እውነተኛ ስሙ አሐድ ሐአ’ም ሳይሆን አቶ ጂንስበርግ መሆኑም ታወቀ። በሩሲያ ውስጥ ሕገ-ወጥ ጉዳዮችን አንስቶ ስለሚጽፍ እንዳይያዘ እና ራሱን ለመሰወር ሲል አሐድ ሐአ’ም ነኝ አለ። በመጨረሻም ወደ እንግሊዝ ለመሰደድ ተገደደ። እዚያም ማለፊያ ገቢ የሚያስገኝለትን የሻይ ንግድ በመነገድ ቆየ። ከዚያም ወደ ፍልስጥኤም በመምጣት ሔርዚሊያ ጅምናዚየም አጠገብ ቤት ተሰጠው። ወላጆቼ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን በመልካም ሁኔታ ካጠናቀቀሁ ወደ ሔርዚሊያ ጅምናዚየም እንደሚያስገቡኝ አበክረው ይነግሩኝ ነበር። ለዚህም ነው ስለ አሐድ ሐአ’ም ከመስማቴ በፊት ስሙን የማውቀው። ደግሞም አሐድ ሐአ’ም በሔርዚሊያ ጂምናዚየም አጠገብ ይኖር ነበር የሚለውን ወሬ ስሰማ አዲስ ዜና ያልሆነብኝ።

በመጨረሻም ከእነ ፎቶው ስለመሞቱ ጽፈው አወጡ። ሽማግሌው ሞልቻድስኪ ፎቶውን እንድመለከት ስላደረገኝ በሕይወቴ የምደመምበትን አንድ ነገር አገኘሁ። ሁሌም ስለ ፀሐፊዎች አስባለሁ። በተለይ ደግሞ ሕገ ወጥ ነገሮች የሚጽፉትን ፀጉራቸው ብዙ፣ ጺመ ቁጥቋጦዎች እና አይነ ፈጣጦች አድርጌ እገምታለሁ። ብዙ መፃፍ ምናልባትም አይንን ይጎለጉላል። ዳሩ ግን አሐድ ሐአ’ምን እንዴት ልግለፅላችሁ? ፊቱ ባለሦስት ማዕዘን ነው። ከወደላይ ግንባረ ሰፊና መላጣ፤ ከወደታች አገጨ ጠባብ እና ሹል ነው። ፎቶውን ከተመለከትኩ በኋላ ግን የነበረኝን አስተሳሰብ ለወጥኩ። ከሁሉም በላይ የጸሐፊዎቹ አዕምሮ ነው ዋናውና አስፈላጊው ነገር። ለዚህም ነው ጭንቅሎ ራስ እና ሾጣጣ የፊት ገጽ የያዘው። እንደ ማንኛውም የእሱ ዘመን ሰዎች መነጽር ያደረገ ሲሆን፣ የእሱ መነጽር ግን ወርቃማ ፍሬም የለውም። ደግሞም ጆሮው ላይ የሚያርፍ የመነፅር መደገፊያም አልነበረውም። እንዲህ አይነቱን መነጽር ቀደም ሲል አውቃለሁ። አባቴም ያለው ይህን መሰል መነጽር ነውና። ሌንሶቹ በጥብቅ ተጣጣፊ ስፕሪንግ የተያያዙ በመሆናቸው እና አፍንጫ ላይ ግጥም ስለሚሉ ቀይ ምልክት ያትማሉ። ለዚህ ነው ከአፍንጫ ላይ የማይወድቁት። የሚደሉ ባይሆንም መስህብነት አላቸው። ዳሩ እንዳይወድቁና እንዳይሰበሩ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።

አሐድ ሐአ’ም ግን በእነዚህ ችግሮች የተጨነቀ አይመስልም። ከፎቶ ግራፉ እንደምመለከተው ሌላ የሚያስጨንቀው ነገር አለ። ፊቱ የተጨነቀና የተጠበበ ነው። ሞልቻድስኪ እንደነገረኝ ከሆነ ስለ አገራችን የወደፊት ዕድል የሚጨነቅ እና ለሁሉም ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት የሚኳትን ጸሓፊ ነበር። ለዚህም ነው እንዲህ ዕውቅ የሆነውና ፖሊሶችም ለእሱ ያላቸው እይታ እንዲያ የሆነው።

ቀብሩ የት እንደሆነና እዚያም መገኘት እንዳለብኝ በማሰብ ሞልቻድስኪን ጠየኩት። ሞልቻድስኪ ጋዜጣውን ተመልክቶ ማክሰኞ በዘጠኝ ሰዓት አስከሬኑ ከቤቱ እንደሚወጣና እንደሚቀበር ነገረኝ። ሲነግረኝ ያ ዕለት ሰኞ እና ባለቀ ረፋድ ሰዓት ነበር።

በዚያው ዕለት ምሽት ስለ ጉዳዩ ለወላጆቼ ነግሬ ቀብር ላይ መገኘት እንዳለብኝም ገለጽኩላቸው። አባቴ “እንቶ- ፈንቶ አታውራ” ብሎ ሲቆጣኝ፣ እናቴ ደግሞ “መጀመሪያ የቤት -ሥራህን በሰራህ” አለቺኝ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኜ በነጋታው ከቀኑ ስምንት ሰዓት ተኩል ሲሆን ከአሐድ ሐአ’ም መኖሪያ ቤት ፊት ለፊት ካለው የጽሕፈት እቃ መደብር እና ከግሮሰሪው አጠገብ ቆሜ ጠበቅሁ። ምንም ቢሆን ሁለት ሰዓት ያህል ከመዘግየት ግማሽ ሰዓት ቀድሞ መገኘት ይሻላል። በትዕግሥት ብጠብቅም በዚያ ስፍራ የተገኘሁት እኔ ብቻ መሆኔ ደግሞ ደነቀኝ። ከብዙ ሰዓታት በኋላ በትሩምፔልዩር ጎዳና ወደሚገኘው የመቃብር ስፍራ ለመሄድ ወሰንኩ።

ሥፍራው ፀጥ ያለና ሰላማዊ ሲሆን የተወሰኑ ሴቶች በብዙ መቃብሮች ላይ ሲያነቡ ተመለከትኩ። ሆኖም ግን አሐድ ሐአ’ም መቃብር ላይ ማንም አያለቅስም። መጠየቅ ደግሞ ተገቢ አልነበረም፤ ደግሞም ከማላውቀው ሰው ጋር አልነጋገርም። ስለዚህ ወደ አሌንባይ ጎዳና ተመልሼ ለመጓዝ ወሰንኩ። የቀብሩ ሥነ-ስርአት በዚያ ጎዳና ላይ ሊካሄድ ይችላል ብዬ ተስፋ በማድረግ ለቀስተኞቹን ልደርስባቸው ወደዛው አቀናሁ። አንድ ነገር ሳይከሰት አይቀርም መሰል መንገዱ ተዘጋግቷል።

ወደ ኸርዚሊያ ጂምናዚየም ለመመለስ ስወስን የውሻ ድካም ተሰምቶኝ ነበር። ስለዚህ ከጄኡላ ጎዳና በተጓዳኝ ወዳለው ወደ አለንባይ ጎዳና አግዳሚ ወንበር ላይ እረፍት ለማድረግ ተቀመጥኩ። ከዚያ ሆኜ በድንጋይ የተገነባውንና አባቴ ፂሙንና ፀጉሩን የሚያስተካክልበትን ህንፃ እመለከታለሁ። ፀጉር አስተካካዩ እንደ ወላጆቼ ሁሉ ወደ ኤሬትዝ እስራኤል የመጣው በጀልባ ነው።

ለቀስተኞቹ በፒንስኬር ጎዳና አድርገው ወደ መቃብሩ ሲያልፉ ጠብቄ እነሱን ለማጀብ ነበር እዚያ መጠበቄ። አላማዬ እንደዚያ ቢሆንም ዕንቅልፍ ጣለኝ።

ምን ያህል ጊዜ እንደተኛሁ ባላውቅም አንድ ድንገተኛ እጅ ትከሻዬ ላይ አረፈ። ከዚያም በጨዋነትና በለዘበ ድምፅ “አንተ ልጅ በል ተነስ! አንተ ልጅ!” አለኝ።

በመጀመሪያ ጊዜው ድንግዝግዝ ያለና አየሩም ትንሽ ቀዝቀዝ የሚል ስሜት ተሰማኝ። በዝግታ ፊት ለፊቴ የቆመው ሰው ማን እንደሆን ለመለየት ቻልኩ። እንደ ሞልቻድስኪ ሽማግሌም ያልሆነ፤ እንደኔም ገና ጨቅላ ልጅ ያልነበረ በመሀል የዕድሜ ክልል የሚገመት-እንበልና አሥራ ስድስት ዓመት የሚሆነው ሰው ነበር። ከእንቅልፌ እንደ ነቃሁ መገመት ባልችልም በኋላ ግን ሃያ ሦስት ዓመቱ እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ።

“አዳምጥ” አለኝ። ቀጥሎም “እዚህ አካባቢ ነው የምኖረው፤ ከብዙ ሰዓታት በፊት አግዳሚ ወንበር ላይ ተቀምጠህ ተመልክቼሀለሁ።

አሁን መሽቷል። እዚህ ተጋድመህ ብትቀር ቤተሰቦችህ ሊጨነቁ ይችላሉ ብዬ አስባለሁ። ስለዚህ ተነስና ወደ ቤትህ ላድርስህ። የት ነው የምትኖረው?”

ተነስቼ ቆምኩ። ጉልበቴ እንደዛለ ተሰማኝ። እንደምንም ብዬ ቆምኩና ተመለከትኩት። መልካም ወጣት ነው። ንግግሩም ያማረ። እንዳይጨነቅ እና በራሴ መሄድ እንደምችል ነገርኩት። ዕውነታው ግን የጌዩላን ጎዳና ሙሉ ርዝመት፣ በሐይራኮን ጎዳና አድርጎ በሀሰን ቤክ መስጊድ በኩል ማለፍ እንዲህ ቀላል አይደለም። እኔ ስለምፈራ ሳይሆን በዚያ ጨለማ ምን መሆን እንደሚቻል ስለማይታወቅ ነው። ብቻዬን ለቆኝ እንደማይሄድ ተስፋ ያደረኩ ሲሆን እሱም ብቻዬን አለቀቀኝም። የተመላለስነው ቃል መልካም ቢሆንም ትእዛዛዊም ጭምር ስለነበር የሚለኝን ተቀበልኩት። እናም እጄን ሰጥቼው አብሬው በጌዩላ ጎዳና መጓዝ ጀመርን።

የሰፈሩ ትላልቅ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ስለተመለከቱት ስሙን ጠየቁት። እሱም የእኔን ስም በመጠየቁ ስሜ ኤልያኪም መሆኑን ነገርኩት። እሱም በተራው ስሙ ቪክተር መሆኑን ተናገረ። በመጀመሪያ የቁጩ መስሎኝ ነበር። በኋላ ግን አመንኩት። በደንብ መተዋወቅም ጀመርን።

ዕድሜዬን ጠየቀኝ፤ ሰባት መሆኑን ነገርኩት። የእሱ ዕድሜ ሃያ ሦስት መሆኑን ነገረኝ። ከዚያ በጌዩላ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እንደነበርኩ ስነግረው፤ እሱ ትምህርቱን ጨርሶ በእብራይስጥ፣ በአረብኛና በፈረንሳይኛ ቋንቋዎች እንደሚሰራ አብራራልኝ። በመጀመሪያ እዚህም ላይ የዋሸኝ መስሎኝ ነበር። ‘እንዴት ይህን ሁሉ ቋንቋ ያውቃል በሚል?’ ዳሩ ግን እንዳልዋሸኝ እርግጠኛ ነኝ።

ቀስ እያልን ነበር የምናዘግመው። ምክንያቱም በዚያ አሸዋማ መሬት ላይ በበረባሶ ጫማ በፍጥነት መጓዝ አስቸጋሪ ነው። በተለይ እኔን አሸዋው አስቸግሮኝ ስለነበር አንድ ቀልድ ነገረኝ። በቀልዱም እንዲህ ባለ በረሃ ውሰጥ የእስራኤል ልጆች ለአርባ አመታት ከምስር (ግብፅ) አገር ወደዚህ እንደተጓዙ። “እንዳንተ በረባሶ ጫማ አድርገው ቢሆን ኖሮ ግን ሰማኒያ ዓመት ይፈጅባቸው ነበር” አለኝ። ከዚያ ሁለታችንም ተያይዘን ሳቅን። ታሪኩን ካወቅሁ በኋላ በሚያስቅ መልኩ መልሼ መተረኩን አልቻልኩበትም። በትምህርት ቤት በኩል ሳልፍ የተማርኩበትን ትምህርት ቤት አሳየሁት። እሱም በተራው ስለትምህርት ወዳድነቴ ሲጠይቀኝ እንደነገሩ መሆኔን ነገርኩት።

ከዚያ ለምን በእንቅልፍ እንደወደቅሁ ጠየቀኝ። እኔም ስለ አሐድ ሐአ’ም ጉዳይ አንስቼ የቀድሞ ስሙ ጂንስበርግ ስለመሆኑ፣ በእንግሊዝ ስለነበረው የሻይ ንግድና ስለሁሉም የማውቀውን ያህል ነግሬው በቀብሩ ሽኝት ለመገኘት ስለመፈለጌ ተረኩለት።

በዚያን ጊዜ ቪክቶር በአግራሞት “ምን?!” ሲል ጮኸ። “በዚያ አግዳሚ ላይ አሥራ ሁለት ቀናት ተኛህ ማለት ነው?” አለኝ። እንዲህ አይነቱ ጥያቄ መቼም እብድ ያደርጋል። በዚያ አግዳሚ ላይ አሥራ ሁለት ቀናት መተኛቴ ወላጆቼም በእነዚያ ቀናት ሁሉ በእኔ ላይ ስለደረሰው አለማወቃቸው ከአዕምሮ በላይ ነው። ለግማሽ ቀን እንኳን በቤት ካልታየሁ እንዴት እንደሚያደርጋቸው አውቃለሁ። በዚህ ጊዜ ስለሆነው ነገር ምንም ላውቅ አልችልም። “አሥራ ሁለት ቀን ስትል ምን ማለትህ ነው?” አልኩት ቪክቶርን። ቪክቶርም በተራው “የገረመኝኮ ከአሥራ ሁለት ቀናት በፊት የአሐድ ሐአ’ምን ቀብር በመስኮቴ በኩል በዓይኔ በብረቱ መመልከቴ ነው”።

“ታዲያ ቀብሩ ዛሬ ስለመሆኑ እንዴት አሰብኩ?” መልሼ ጠየኩት።

“ዛሬ መሆኑን ማን ነገረህ?” አለኝ ቪክቶር።

“ባለ ግሮሰሪው ሞልቻድስኪ ነው የነገረኝ” አልኩት።

“ይህን ፍሬ ከርስኪ ወሬ ከየት አመጣው?” ሲል በጥያቄ አፋጠጠኝ።

ከጋዜጣው አግኝቶ ነው” አልኩት።

“ከየትኛው ጋዜጣ?” ሲል ጠየቀኝ።

“ከሔይንት ጋዜጣ” መለስኩለት።

ዳሩ ግን ወላጆቼ የሚያነቡት “ፓስለድኒይ ኖቪስት” የተባለውን ጋዜጣ ቢሆንም እነሱ ግን ምንም ነገር አላሉኝም። እሱ ግን ከዋርሶ የሚመጣውንና መቶ በመቶ እርግጠኛ የሆነ ጋዜጣ እንደነበረው አስረዳሁት። በዚህ ጊዜ እንደ እብድ ሳቀ። ከውጭ የሚመጡት ጋዜጦች በፖስታ ቤት ስለሚገቡ አንዳንድ ጊዜ እስከ ሁለት ሳምንት ድረስ እንደሚፈጅባቸውና እኔ የተመለከትኩት የአሐድ ሐአ’ም ፎቶግራፍ ያለበት ጋዜጣም ሁለት ሳምንት ያህል የቆየ መሆኑን ዘርዝሮ አስረዳኝ። በትክክል ላገናዘበው ደግሞ ሁለት ሳምንት እና አሥራ ሁለት ቀናት ብዙም ልዩነት የላቸውም። ቪክቶር በሁኔታው ቢስቅም እኔ ግን ወይ ፍንክች! አለመሳቄን ሲመለከት ደግሞ “አትጨነቅ፣ ደግሞም አትዘን ኤልየኪም። ይህ ስህተት ባይከሰት ኖሮ መች እንዲህ ወዳጅ እንሆን ነበር?” ሲል አፅናናኝ።

እሱ ያለውን ሁሉ በጥሞና ባዳምጥም ምንም መልስ አልሰጠሁም። እንዲያውም ከበፊቱ ይልቅ አሁን ደስተኛ ነኝ። ከዚያም የባህሩን ሞገድ ድምፅ ስለመስማቴ ጠየቀኝና ወደ ባህሩ የመቃረባችን ምልክት መሆኑን ተናግሮ ወደ ሐይአርኮን ጎዳና እንደምንታጠፍ ገለፀልኝ። እኔ ግን ባህሩ ሩቅ በሆነና ለረጅም ጊዜ አብረን እንድንጓዝ መፈለጌን ነገርኩት። ቪክቶር በበኩሉ ጊዜ በሰዓት ሳይሆን በወዳጅነት እንደሚወሰንና መላው ሕይወታችን ከፊት ለፊታችን በመሆኑ ስለ ጊዜ መጨነቅ እንደማይኖርብን ነገረኝ።

በወቅቱ የተረዳሁት ስለመሆኔ አላውቅም፤ አሁን ግን እሱ ያለኝ ነገር ገብቶኛል። አብረን እንደተጓዝን “አዳምጥ፣ አንድ መዝሙር እዘምርልሃለሁ” ብሎኝ ነበር። እናም “ሁሉም ጀልባዎች የሰንበትን ብርሃን ያበራሉ” የሚለውን መዝሙር እስከመጨረሻው ዘመረልኝ። በተራዬ የምችለውን መዝሙር እንድዘምርለት ቢጠይቀኝም፤ እኔ ለመዘመር አፈርኩ። እሱ ግን በተጨማሪ “ኦ ምሽቱ፣ ኦ ምሽቱ፣ ኦ አባት አገር” የሚለውን ዘመረልኝ። ከዚያም ገጣሚያን በዓለም ያሉ ታላቅ ሰዎች ናቸው አለኝ።

አሐድ ሐአ’ምን ይበልጣሉን?” ብዬ ስጠይው “አዎን በትክክል” የሚል ፈርጣማ መልስ ሰጠኝ። በአባባሉ ብደነቅም በሃሳቡ ግን አልተስማማሁም። ድንገት ቤታችን መቃረባችንንና ከሞልቻድስኪ ግሮሰሪ መድረሳችንን ተመለከትኩ። ማልቀስ ዳዳኝ። ሁኔታው ግራ ፈትል ቢሆንብኝም ጨለማ በመሆኑ ግን ተደሰትኩ።

እራሴን ለመቆጣጠር እየታገልኩ ግሮሰሪውን አሳየሁት። እርሱም “ነገ ጠዋት ለባለ ግሮሰሪው የእብራይስጥ ጋዜጣ ማንበብ እንዲጀምር ንገረው አለኝ” ፈርጠም ብሎ “ንገረው” አለኝ ቪክቶር አሁንም። “እብራይስጣዊ-እብራይስጥኛ ይናገር”።

አብሮኝ ደረጃውን ወጥቶ በሩን ራሱ አንኳኳ። ወደ ቤት ዘለቅን። ስለ ሁኔታው ከማስረዳቱ በፊት አባቴ ቶሎ ብሎ ሲዳብሰኝ እናቴ ጩኸቷን አቅልጣ አቀፈቺኝ። ቪክቶርም ወዲያው ደህና ሁኑ ብሎ ተሰናበተ።

ከእናቴ ዕቅፍ እንደተላቀቅሁ ወደ ባልኮኒው ወጥቼ ቪክቶር ቤታችንን ለቆ ወደቀኝ መታጠፉን ተመለከትኩ። ባለ በሌለ ጉልበቴም “ቪክቶር መልካም ሰው ነህ፣ እወድሃለሁ!” ስል ጮኽኩ። ወዲያው ደግሞ ማን እንዲህ እንዳለው እንዳያውቅ በባልኮኒው መከለያ ስር ተደበቅሁ። እዚያው እንዳጎነበስኩ አገጬ በመመታቱ ከንፈሬ ተሰንጥቆ መድማቱ ታወቀኝ።

በሁኔታው ወላጆቼ ተደናገጡ። ወዲያው በቁስል ማድረቂያ አዮዲን እና ሌላም ተጨማሪ የህክምና እርዳታ እያደረጉልኝ በመሀሉ ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ወሰደኝ። እንዲያው ስለደከመኝ ሳይሆን ብቻዬን መሆን ስለፈለኩ። ማለትም ከቪክቶር ጋር ዳግም የመገናኘት ምኞት ጣለኝ።

በዚያ ምሽት ስለ ቪክቶር ማለም አልቻልኩም። በሌላ ጊዜ ግን አድርጌዋለሁ። እስከ ዛሬም ድረስ እንዲያ ነው። ***

ማስታወሻ ፦ አሐድ ሐአ’ም በብዕር ስሙ (Nom-deplume) የታወቀ የእብራይስጥ ደራሲ አሸር ሒርች ጂንስበርግ ሲሆን ከ1856-1927) የኖረ ነው።

እሱ ከዋርሶ የሚመጣውን ሔይንት የተሰኘ ጋዜጣ ያገኛል። በዚያ ጋዜጣ ላይ ደግሞ የአሐድ ሐአ’ም ታሪክ፣ የፖሊስ እና ጋሪዎቹ እንዲሁም ሌሎች ታሪኮች ነበሩበት። ሰፈሩ ሁሉ በዚህ መንገድ ነው ስለ ታሪኩ የሚያውቀው እና በኋላም ወሬውን የሚጠርቀው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top