ታሪክ እና ባሕል

አቶ ሃብተስላሴ ታፈሰ አረፉ

የኢትዮጵያ ቱሪዝም አባት በመባል የሚታወቁት አቶ ሃብተ ስላሴ ታፈሰ በዘጠና አንድ ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ የቀብራቸው ሥነ ሥርዓትም ወዳጅ ዘመዶቻቸውና በርካታ አድናቂዎቻቸው በተገኙበት ነሃሴ 7 ቀን 2009 ዓ.ም በቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል። ከአባታቸው ከፊታውራሪ ታፈሰ ሃብተ ሚካኤልና ከእናታቸው ከወይዘሮ ሙላቷ በላይነህ በ1918 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የተወለዱት አቶ ሃብተ ስላሴ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአቴንስ ግሪክና በግብፅ አሌክሳንድሪያ ተከታትለዋል፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ደግሞ በአሜሪካው የሚኒሶታ ግዛት፣ ኖርዝ ፊልድ ውስጥ በሚገኘው የካርልተን ኮሌጅ በዓለማቀፍ ግንኙነት መስክ ተቀብለዋል፡፡ ከዚያ ወደ ሃገራቸው ተመልሰው በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሬስና ማስታወቂያ መምሪያ ሃላፊ ሆነው አገልግለዋል፡፡

ሆኖም ለቱሪዝም ምንም ትኩረት አለመሰጠቱና መስኩ ገና በጮርቃው መሆኑ ስላሳሰባቸው አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘን ድቀርበው አንድ ተቋም ሊመሠረት እንደሚገባ ያሳሰስባሉ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም በሃሳቡ ተስማምተው የማደራጀቱን ተግባር ራሳቸው አቶ ሃብተ ስላሴ ማከናወን እንዳለባቸው ያምናሉ፡፡ ስለዚህም ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ስር ወዳለ ቢሮ እንዲዛወሩ ሆነ፡፡ በዚህም መሠረት የቱሪዝምን ኢንዱስትሪ ከመወጠንና ከማሳደግ በተጨማሪ የኢትዮጵያ የቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅትን አቋቁመዋል፡፡

አቶ ሃብተ ስላሴ በምርጥ ፎቶግራፎቻቸው፣ ታሪካዊውን የኢትዮጵያ የጉዞ መስመር (The Historic Route) በማስተዋወቃቸው፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የአሥራ ሶሥት ወር ፀሐይ (Thirteen Months of Sunshine) የሚለውን ታዋቂ የቱሪዝም መፈክር በመፍጠራቸው ይታወቃሉ፡፡ ለዚህም በርካታ ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡ ደርግ ወደ ስልጣን ሲመጣ አቶ ሃብተ ስላሴን ያሰራቸው ሲሆን ከሰባት ዓመታት በኋላ ሲፈታቸው በቱሪዝም ዘርፍ አማካሪነት መድቧቸዋል፡፡ እስከ ሕይወታቸው ፍፃሜ ለኢትዮጵያ የቱሪዝም ዕድገት የደከሙት አቶ ሃብተ ስላሴ ከወይዘሮ ሙሉመቤት መስፍን ጋር ትዳር መስርተው ሁለት ወንዶችና አንዲት ሴት ልጆችን አፍርተዋል፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top