የታዛ ድምፆች

በኢትዮጵያ የሲኒማ ትምህርት አስፈላጊነትና ተግዳሮቱ

የሲኒማ ነገር በኢትዮጵያ መታወቅ የጀመረው ምናልባትም ከሰይጣን ቤት ታሪክ ጋር ታጣምሮ አለያም የኢጣሊያን ወረራ ታክኮ እንደሆነ ተደጋግሞ ሲነገር እናውቃለን። ወደዚህ ወደ ቅርቡ ዘመን ስንመጣ ደግሞ ስመ- ገናን ከሆኑት ከነ “ጉማ” እና “ሂሩት፣ አባቷ ማነው?” ጋር ኢትዮጵያውያን የሲኒማ ባለሙያዎች ታሪክም አብሮ መነሳት መጀመሩ የሚዘነጋ አይደለም። የሆነው ሆኖ ባለፉት ሁለት አሰርት ውስጥ ከዚህ ቀደም በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሲኒማን የመጻፍ፣ የመቅረጽ፣ የማቀናበር፣ የማሰራጨትና ለበርካታ ተመልካች የማሳየት ሙያዊ እንቅስቃሴ ተስፋፍቶ ተመልክተናል። ሲኒማ ሊሆኑ የሚችሉ ሞልተው የተረፉ ታሪኮች ቀድሞም የነበሩ ቢሆንም በስፋት በሲኒማ የመጠበብና በቢዝነስ/በኢንዱስትሪ ደረጃ የማደራጀት ድፍረቱና ሙከራው ግን ፈጽሞ አዲስ እርምጃ ነው ማለት ይቻላል።

በዚህ አጭር የስርጭት ዕድሜው እስከዛሬ ተቀርጸው ለተመልካች የቀረቡትን የሲኒማ ስራዎች እንኳ ስንመለከት ወደፊት የኢትዮጵያ ሊባል የሚበቃ የሲኒማ አሻራና የሲኒማ አምባ መፈጠሩ እንደማይቀር የሚያመላክት ተስፋ አብሮት ይታያል። በዚያው መጠን የጀማሪነት ህመሙን የሚያባብሱ እንከኖች ዛሬም ከዓመታት በኋላ ገና አልተላቀቁትም። የሲኒማን ሃያል ጥበባዊ ቋንቋ ከዘመነኛው ማህበራዊ ጥያቄ ጋር አገናዝቦ አቅም ያለው ኪነ-ጥበብ የመፍጠር ተግባር የሲኒማው ባህል ስር ባልሰደደበት ሀገር እንዲሁ በአቦ ሰጡኝ የሚሳካ የዋዛ የቤት ስራ አይደለም። ብዙ የሙከራ ዓመታት ብቻቸውን ሊፈቱት ያለመቻላቸው ምስጢርም የዚሁ ብርቱ የቤት ስራ ማመላከቻ ምስክር ነው።

በደረስንበት ሃያ አንደኛ ምዕታመት ላይ እንደየትኛውም የስነ-ጥበብ ዘርፍ ሲኒማን በዘልማድና በዝግ ሞቅታ ደጋግሞ የማምረት ጉዳይ ብቻውን ምኑንም ማንንም ወዴትም ሊያሳድግ ከቶ ዓይቻለውም። ዛሬ የጥበባትን ታሪክ ጨምሮ መላው የአፍሪቃ ታሪክ እንደገና በአፍሪቃውያን ተፈትኖ እየተጻፈ ያለበት ወቅት ላይ ደርሰናል። ከዚያም አልፎ የአፍሪቃውያን ፍልስፍናዎች፣ እምነቶችና አመለካከቶች ሁሉ መሰማትና ቀልብ መግዛት የጀመሩበት ዘመን ተፈጥሯል።

ዓለም ከደረሰበት ቴክኖሎጂ ጋር የኛ በሆነ ጥበብ የተጠመቁ ድምጾቻችን እንዴት ሆነው ሲኒማ ይሆናሉ? የሚለው ጥያቄነው እንግዲህ ዛሬ ጠንካራ መልስ ከሲኒማ ሰሪው የሚጠብቀው።

ከዚህ ጥያቄና መልስ ጀርባ ደግሞ የተሰደሩትን እነዚህን ማህበራዊ፣ ስነ-ውበታዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ለማገናዘብ ባንድ ወይም በሌላ ዘዴ አቅም ያለው ሲኒማ ሰሪ ካልተፈጠረ የሲኒማ የሙከራ ወይም የየዋህነት ዘመን ወደ ብስለት ሊሸጋገር አይችልም። አውቀንም ሆነ ሳናውቅ (ደረጃውን የጠበቀ) የምንላቸው ኪነ-ጥበባትም የሚገኙት ይህንኑ ማሟላት ሲችሉ ብቻ ነው። በሌላ በኩል የነዚህን ጥያቄዎች መልስ በሙሉ ካንድ ምንጭ በቀላሉ መቅዳት ይቻላል ማለትም ዘበት ነው። ምንጮቹ የትየለሌ ናቸው። አንዳንዴ ማስታወስ አንዳንዴም ከየት እንደተገኙ ማወቅ እስኪቸግር። ነገር ግን ወደ ምንጮቹ የሚያደርስ ኋላም ምንጭ የሚያደርግ ራሱ የዕውቀት ጉባዔ ነው። ዕውቀት ወይም በዘመናዊ ቀላል አጠራሩ መረጃ በርከት ያሉ ምንጮች እንዳሉት አይካድም። ይሁንና ሀገራችንን በመሰለ መደበኛ የሲኒማ ዕውቀት ባደባባይና በቀላሉ በማይገኝበት ስፍራ ከመደበኛ የዕውቀት ጉባኤ ባጭሩ ከትምህርት ቤት የተሻለ ምንጭ ማግኘት ብዙም የማይሞከር ነው። ከዚህኛው ሓያሲ፣ ከዚያኛው ሙዚየም፣ ወይም ከዚህኛው መጽሀፍ አንዳፍታ አመጣዋለሁ የሚባልለት አገራዊ አቅም ላይ ባለመድረሳችን አሁንም መደበኛ የትምህርት ገበታ ለሲኒማ መዘርጋቱ አማራጭ የሌለው የመፍትሄ አሳብ ነው።

እስካለፈው 2007 ዓ.ም. ድረስ በኢትዮጵያ ውስጥ ሲኒማን ለማስተማር የተቋቋመ አንዳችም መደበኛ ከፍተኛ የህዝብ ትምህርት ቤት አልነበረም። ከላይ እንደጠቃቀስኩት የዚሁ ትምህርት ቤት (መደበኛ ትምህርት) ጉባዔ ያለመኖር ነው የኢትዮጵያን ሲኒማ የብስለት ዘመን አላቃርብ ብሎ ያቆየው ዋነኛው ምክንያት።

በዘጠናዎቹ መጀመሪያ ወደ ኢትዮጵያ ብቅ ይል የነበረው ትልቁ የሲኒማ ምሁር ፕሮፌሰር ተሾመ ወ/ገብርኤል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ንግግር ካደረገ በኋላ ከዩኒቨርሲቲው ሀላፊዎች ጋር ስለ ሲኒማ ትምህርት ቤት መቋቋም ብዙ ብዙ ውይይት አድርገው እንደነበር አስታውሳለሁ። ከዚያም በኋላ ዩኒቨርሲቲው በውጭ ሀገር ከሚኖሩ ታዋቂ ኢትዮጵያውያን የሲኒማ ባለሙያዎችና መምህራን ጋርም እንዲሁ ትምህርት ቤቱን የማቋቋም ተደጋጋሚ ሙከራዎች አድርጎ እንደነበር አውቃለሁ። በዘጠናዎቹ ኢጋማሽ ግድምም በተለይ በጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት በኩል የተደረገ ብርቱ ጥረት እንዲሁ ዳር ያለመድረሱ አይዘነጋም። ለረዥም ዓመታት የሲኒማ ኮርሶችን በመምዘዝ ከተውኔት ትምህርቶች ጋር ይሰጥ የነበረው በዪኒቨርሲቲው የቴአትር ትምህርት ክፍል ነበር።

በሁለት ሺህ ዓ.ም. መጀመሪያ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ክፍሎች እንደገና ሲዋቀሩ የስነ-ጥበብ፣ የሙዚቃና የቴአትር ትምህርት ቤቶች ባንድ ኮሌጅ ስር ተደራጅተው እንዲሰሩ መደረጉ የሲኒማን የትምህርት ገበታ የመዘርጋትን አስፈላጊነት እንደገና ቀሰቀሰው። በዚህ አጋጣሚ የሲኒማ ትምህርት ክፍልን ለማቋቋም የተደረጉ ሙከራዎች ሁሉ ከመክሸፍ ያለፈ የውጤት ታሪክ ስላልነበራቸው ማንም ተመልሶ በዚያ ውስጥ የመዳከር ሃላፊነትን መውሰድ የፈለገ አልነበረም።

በዚያ መካከል የስነ-ጥበብ ትምህርት ቤት አዲስ አበባ ውስጥ አይቢስ ይባል ከነበረ የካናዳ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ጋር ስምምነት ይፈራረማል። ይህም የአኒሜሽን ክፍለ-ትምህርት ለማቋቋም ያለመ ሲሆን በስምምነቱ መሰረት የትምህርት ቤቱ የጊዜው ሃላፊ የካናዳን ተቋማት ከጎበኘ በኋላ የስምምነት ፍላጎቱ ወደ ሲኒማ ትምህርት ደረጃ እንዲሸጋገር ምክንያት ሆነ። ምንም እንኳ ስምምነቱ እየተጓተተ ጉዳዩን አሰልቺ ቢያደርገውም በመጨረሻ ባንድ ጊዜ አምስት ወጣቶችን ለቴክኒካዊ ስልጠና ወደ ካናዳ ኪቤክ ለመላክ ተችሎ ነበር። የስምምነቱ ወደ ሲኒማ ደረጃ ማደግ መንስኤውም በኮሌጁ ስር ለሲኒማ ዋነኛ ግብአቶች የሚባሉት የድምጽ፣ የምስልና የንቅናቄ ትምህርት ቤቶችና ዲሲፕሊኖች በሙሉ ባንድ ስፍራ የመገኘታቸው አጋጣሚ ነበር። ይሁንና አላቋርጥ ያለው የሲኒማ ፈተና በዚህኛውም ዙር አልተላቀቀም ነበር። ይህም ወደ ውጭ ተልከው የነበሩት አምስቱም ወጣቶች በሙሉ እዚያው የመቅረታቸው ዜና ነበር። የስነ_ጥበብ ትምህርት ቤት ግን በሲኒማ ትምህርት ታሪክ ውስጥ ካልተሳካላቸው ተራ ላለመግባት ቆርጦ ስለነበር በአሜሪካን አገር ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሲኒማ ባለሙያዎችና ሀገርም ውስጥ ካሉ ጥቂት ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ጋር በመሆን አዲስ የአካዳሚክ ቅድመ-ዝግጅት ላይ በመስራት የትምህርት መርሀ-ግብሩን በዩኒቨርሲቲው እንዲጸድቅ አደረገ። ባገር ውስጥ ይመጥናሉ ብሎ ከመረጣቸው ለጊዜው ጥቂት የሲኒማ ባለሙያዎችና ከውጭ ሀገር ከቀጠራቸው ሁለት ባለሙያዎች ጋር አጠናክሮ የመጀመሪያውን የመንግስት ከፍተኛ የሲኒማ ትምህርት ቤት በመስከረም ወር 2007 ዓ.ም. ሊከፍት ችሏል። እንደሚታወቀው ከምንም የተጀመረው ይህ የትምህርት ክፍል በአሳማኝ ዓላማው የተነሳ በዪኒቨርሲቲው ማኔጅመንት እየተደረገለት የነበረው አስተዳደራዊ ድጋፍ ለስኬቱ አንዱ ድጋፍ ነበር። ይሁን እንጂ በሁለት እግሩ ለማቆም በሚደረግ ቀጣይ ትንንቅ ትምህርት ቤቱ ብቻውን መቅረቱ (በተለይ ላለፉት ሶስት ዓመታት ምንም መሳሪያ ለመግዛት ያለመቻሉ ወይም ያለመፈለጉ) አጀማመሩ ላይ የነበረውን ፍጥነት እንዲያጣ አድርጎ ወደፊትም ለመራመድ እግር ከወርች ያሰረው ችግር ሆኗል።

ኮሌጁን በማቋቋም ወቅት ከሶስቱም ትምህርት ቤቶች ዲሬክተሮቹ ወደአውሮፓና አሜሪካ ዘልቀው ልምድ ይዘው መመለሳቸው ኋላ ላይ ለተቋቋመው ለዚህ የሲኒማ ትምህርት ክፍል ከፍተኛ አስተዋጽዖ ሊያበረክት ችሏል። ለምሳሌ በኒው ዮርክ የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የፊልም ትምህርት ቤት የተስተዋለው ተማሪዎችን ከተለያየ የዕውቀት ምንጭ መውሰድ ወይም የተለያየ ትምህርት የገበዩ ተማሪዎችን መቀበል ሊናገሩ ያሰቡት ወይም ሊተርኩ የሚችሉት ታሪክ እስካላቸው ድረስ ምን ያህል ዘርፈ-ብዙ ጥቅም እንዳለው ለመረዳት ተችሏል። ኋላም በተግባራዊ ሙከራ ጥቅሙንም ለመጋራት ተችሏል።

ያም ሆነ ይህ የትልልቆቹ ጥያቄዎች መልስ መገኛ የሆነ ጉባዔ ለመፍጠር ግን ገና ብዙ መሟላት የሚገባቸው መዋቅሮች፣ ቁሳቁሶች፣ ባለሙያዎችና ዕውቀቶች አሉ። ባሁኑ ወቅት ከመላው ዓለም በባለሙያዎቹ ፍላጎትና በተቋማችንም ጥያቄ እየተጋበዙ ጥልቅ ልምዶቻቸውንና ዕውቀቶቻቸውን እያካፈሉ የሚመለሱ ዓለማቀፍ ባለሙያዎች አስተዋጽዖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በነዚሁ ባለሙያዎች አማካይነት ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በዓለማቀፍ መድረክ ሊያገኙ የሚችሉበትን የውጭም ሆነ የውስጥ የቤት ስራ ለመስራት ዕቅዱ አለ። ሌላውና ዋናው ነገር በመስኩ ላይ ያለው የሲኒማ ማህበረሰብ ከትምህርት ቤቱ ጋር የሚሰራበትን መንገድ ማመቻቸት ነው። በመተባበር የተሻለ ማደግ ስለሚቻልም ስለሚሻልም። ለዚህም አስቀድሞ መድረኩን የተመቻቸ ማድረግ ይጠበቃል። የዩኒቨርሲቲውም ሆነ የመንግስት ድጋፍ በዚህ በኩል ተወዳዳሪ የሌለው ነው። አያሌ እውቅ ተቋማት ከታላቅነት ጣሪያ የደረሱት ብዙዎቹ እንዲሁ ከምንም ወይም በጣም ከትንሽ ተነስተው ነው። ተሰጥዖና ዝንባሌ ያንንም አድናቂና ገዢ እስካለ ድረስ። የደረስንበት ዘመን በተለይ በሲኒማ ጥበብ፣ የሚተርከው ላለው ኢትዮጵያዊን ለመሰለ ባለታሪክ አያሌ የማደግና የመስፋፋት ዕድሎች ፈጥሮለታል። ዓለም የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ሌሎች ያለፉበትን ሂደት ማለፍ ሳይጠበቅበት ከቁንጮው መሳፈር የሚችልበት ዘመን ነው። ተሰጥዖ ደረጃውን ከጠበቀ ዕውቀት ጋር ተዳምሮ የራስን አሻራ በባለቤቱ ድምጽ ለዓለም ለማሰማት ከዓለም ፊት እኛም የምንለው አለን ለማለት ሲኒማን የሚያክል መሳሪያ ብዙ አይገኝም። በዘመኑ ደረጃ ተዘጋጅቶ ለመገኘት የሁሉም በተለይም የመንግስት ድርሻ አሁንም ገና ብዙ ሃላፊነት ያለበት ነው።

ከዚህኛው ሓያሲ፣ ከዚያኛው ሙዚየም፣ ወይም ከዚህኛው መጽሀፍ አንዳፍታ አመጣዋለሁ የሚባልለት አገራዊ አቅም ላይ ባለመድረሳችን አሁንም መደበኛ የትምህርት ገበታ ለሲኒማ መዘርጋቱ አማራጭ የሌለው የመፍትሄ አሳብ ነው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top