አድባራተ ጥበብ

ፖለቲካዊ ባህላችንን ለማረቅ – ከደቂቀ እስጢፋኖስ እስከ ዘመነ ቴዎድሮስ

በዛሬ ዘመን አንዱ ከሌላው ጋር ተጋግዞ የሚኖርበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ እንደ ሀገር ወይም እንደ መንደርተኛ ዝቅ ብለን ካሰብን የራስን ጎጆ ለብቻ ቀይሶ መኖር ቢቻልም ተመራጭ ግን አይሆንም፡፡ የወደፊቱን መፃኢ ዘመን የሚተነብዩ እንደ ፍራንሲስ ፉኩያማ ያሉ ጠበብት (Futurologists) የታሪክን መጠናቀቅ (መጨረሻ) ቢያቀነቅኑም የዓለም መጨረሻነት በበርሊን ግንብ ወይም በሶቪየት ህብረት መፈራረስ አላበቃም፡፡ የመጻኢ ዘመን ተንባዮቹ የነሱ ዓለም በዲሞክራሲና በካፒታሊዝም ድል ባለቤትነት ላይ ብቻ እንደቆመ ሰብከዋል፡፡ አልፎ ተርፎም የካፒታሊዝም ድርጎ ተጠቃሚዎች የሆኑ የትላልቅ ኮርፖሬሽኖች ሥራ አስፈጻሚዎች የኩባንያቸውን ባህላዊ እሴቶች አጋነው አውርተዋል፡፡ ያወራሉም፡፡ ለምሳሌ ያህል የኮካ ኮላ ኩባንያ ሥራ አስፈጻሚዎችና አሻሻ ጮች ስለ ኮካኮላ ዓለማቀፋዊ አዲስ ባህል ፈጣሪነት ደረታቸውን ነፍተው አውርተዋል፡፡ አንድ አይነት ይዘት፣መልክና ቁመና ያለው ሸቀጣቸው በሁሉም ሀገር በሽሚያ ስለሚሸጥ ነው እንዲያ ያሉት፡፡ ቻይናዎች እንኳ ኮካን ‹በጠርሙስ የታሸገው ኢምፔሪያሊዝም እንዳላሉና ጥምብ እርኩሱን እንዳላወጡት ዛሬ ከዓለም ህዝብ ሁሉ ልቀው ኮካን በብዛት የሚገሽሩት እነሱ ሆነዋል፡፡

በሌላ መልኩ የሚዲያ ልሂቃን፣ በእያንዳንዱ ሰው ቤት ጎጆ ላይ የተጠመደውን የሳተላይት ሳህን በማሰብ ዓለማችን ወደ ዓለማቀፋዊ መንደርነት (Global village) እየተለወጠች መሆኗን ነግረውናል፡፡ ዛሬ ዓለም በቶማስ ፍሬድማን ቋንቋ እየተዋሃደች በመምጣቷ የራስን የግል ግድግዳ አልፎ ማየት ተጀምሯል፡፡ እግርኳስን የፈጠሩት ወግ አጥባቂዎቹ እንግሊዛውያን እንኳ አድማሳቸውን አስፍተው የስፔንን እግርኳስ ውድድር በጀርመን ቢራ እያወራረዱ መመልከታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ይህ ማለት እንኳንስ ለፖለቲካ፣ ለኳስም የአመለካከት አድማስን ማስፋት ይጠይቃል ለማለት ነው፡፡ ዳሩ፣ ባህላዊ ግድግዳዎች እየፈራረሱ ቢሆንም በአንድ በኩል፣ ውህድ የሆነ ባህላዊ ጥምረትን የሚደግፉ፤ በሌላ በኩል፣ ይህን ጥምረት የሚቃወሙና በመንደር አመለካከት የታጠሩ ሞልተዋል፡፡ እነዚህን መንደርተኞች አቅልሎ መመልከትም አይገባም፡፡

በተለይ በሀገራችን የሚታየውን የፖለቲካ ባህል (Political culture) ቅርጽ-አልባነትና አለመበልጸግ ከስር መሰረቱ በማጥናት ተገቢውን የፈውስ መንገድ መጠቆም ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሃላፊነት ደግሞ በተለይ የወደቀው በኢትዮጵያ ምሁራን ላይ ቢሆንም፣ የሀገሩን መልካምነት የሚፈልግ ሁሉም ዜጋ እንዲነጋገርበት ያስፈልጋል፡፡ የግድም ይላል፡፡ በዚህ መስክ እኛ የሀገሪቱ ዜጎች በግልጽ ተነጋግረናል ማለት አይቻልም፡፡

‹ፖለቲካዊ ባህል› የተባለው የእውቀት ዘርፍ ተለይቶ ለምርምር የበቃው በ1950ዎቹ በጋብሬል አመንድ (Gabriel Almond) እና ሲድኒ ቬርባ (Sidney Verba) ነው፡፡ አሜሪካውያን የፖለቲካ ሊቆች ናቸው፡፡ የፖለቲካ ባህል በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ወይም በግለሰብ የተያዘ ሰፊ ትርጉም ያለው የፖለቲካ ባህርይን ሊገልፅ የሚችል ማእቀፍ ነው፡፡ አንድ ማህበረሰብ ታሪካዊ በሆኑ የተለያዩ መልኮች፣ በባህላዊ ተግባራትና በሰብአዊ ማህበራት ጉባኤዎች ይገለጻል፡፡ የፖለቲካ ባህል ከዲሞክራሲያዊና ከፖለቲካዊ ተቋማት ጋር ከተሳሰረ ልዕለ ሃሳብ፣ አመለካከቶችና ባህርያት ባለፈ ሊታይ የሚችል ነው፡፡ የፖለቲካ ባህል የሚጎለብተው በመነጋገርና በመተማመን፤ በማሳመን፤ ባህላዊ የጋራ መግባባትን በመፍጠርና ብዝሃነትን በመቀበል ነው፡፡ ይህ ፖለቲካዊ ባህል በለውጥ ውስጥ የሚዳብርና ለለውጥም እንቅፋት ያልሆነ ነው፡፡ የፖለቲካ ባህል ከፖለቲካዊ ርዕዮተዓለም የሰፋ ሲሆን፣ የተለያየ የፖለቲካ ርዕዮት የሚከተሉ ወገኖች በአንድ የፖለቲካ ባህል ውስጥ ራሳቸውን ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ ይህም ማለት ኢህአዴግ፣ ሰማያዊ ፓርቲ፣ አረና፣ ኢዴፓ ወይም የዲያስፖራዎቹ ተቃዋሚዎች ፖለቲካዊ አመለካከታቸውንና ርዕዮተዓለማቸውን እንደያዙ በፖለቲካዊ ባህል ምህዳር ውስጥ ሊከራከሩ፣ ሊፋተጉና የተሻለ ሀሳብ ሊያመነጩልን ይችላሉ፡፡ ይህም በሌላ አገላለጽ ልዩነትንና ሽንፈትን በጸጋ እስከ መቀበል ይደርሳል፡፡ በአንድ ወቅት አቶ መለስ ዜናዊ ‹መላጣየን እስካልነካ ድረስ ልንለያይና ልንከራከር እንችላለን› ያሉትን ያስታውሷል፡፡ በአጠቃላይ መልኩ ፖለቲካዊ ባህል የሚገለጸው ሰዎች ለፖለቲካዊ ባህርያቸው ትርጉም ሲሰጡትና ትርጉሙንም ሆነ ልዩነቱን እሰዬው ብለው ሲቀበሉት ነው፡፡

በመሰረቱ ፖለቲካዊ ባህል፣ የፖለቲካ ሥርዓቱና የፖለቲካ ሥርዓቱ አባላት ውጤት እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ የባህሪያት፣ የእምነቶችና ፖለቲካዊ አስተሳሰቦች ቅንጅት ነው፡፡ በመንግሥትና በዜጎች ግንኙነት ይገለጻል፡፡ ለዚህም ነው በፖለቲካ ሥርዓቱ ውስጥ የዜጎችን የተለያዩ ፖለቲካዊ ባህሪያት የሚያስተሳስረው፡፡ ነፍጠኛው ከብዕረኛው፤ ግራ ቀደሙ ከቀኝ መንገደኛው፤ ለዘብተኛው ከአክራሪው ጋር አብረው ተቻችለው እንዲኖሩ ያስችላል፡፡ ሦስት መሰረታዊ አስተሳሰቦች እዚህ ላይ ያስፈልጉናል፡፡ እነሱም ልዩነትን ማክበር፤ መግባባትና በመጨረሻም የአንድ ሀገር ዜጋ መሆን ወይም ውህድነት (Homogeneity) ናቸው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ዝንተ አለማችንን የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል ኖሮን አያውቅም፡፡ በመተራረድ፣ በመበቃቀል፣ በመመቀኛኘት እናምናለን፡፡ ወንድም ለወንድሙ ጠላቱ ሁኖ ኖሯል፣ ቆይቷል፡፡ ዳግማዊ ኢያሱ በ1775 ዓ.ም. በቅርብ ዘመዱ ተመርዞ ነው የሞተው፡፡ ብዙዎቹን ንጉሳውያን የእግዜር በሽታ አይደለም የገደላቸው፡፡ ያልዳበረ ፖለቲካዊ ባህል (Parochial Culture) በመስፈኑ የተከተልነው መንገድ ራስን የመግደል ባህል ሁኖ ቆይቷል፡፡ ያሳዝናል፡፡ አሁን ያለውም ትውልድ አዲስ ፖለቲካዊ ባህል ገና አልገነባም፡፡ እስቲ የፖለቲካ ባህላችንን ለመዳሰስ ታሪካችንን ወደ ኋላ ተመልሰን እንመልከት፡፡ ትናንትን መመልከት ወደፊት ለመንደርደር ይጠቅማልና፡፡

‹ፅኑ ነብይ ሲነሳ ፅኑ ንጉሥ ያስነሳል›-እስጢፋኖስ ዘርአ ያዕቆብንና ደቂቀ እስጢፋኖሶችን እንውሰድ፡፡ ምስጋና ለፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ይሁንና ጥንታዊውን የፖለቲካ ባህላችንን ጨካኝነትና ቅርጽ አልባነት በደቂቀ እስጢፋኖስ መፅሀፋቸው ፍንትው አድርገው አሳይተውናል፡፡ የዛሬው ትውልድ ከዚያ መከራና እልቂት ትምህርት መውሰድ አለበት፡፡

የፕሮፌሰር ጌታቸውን “ደቂቀ እስጢፋኖስ” መጽሀፍ ያነበቡት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ደግሞ፣ በንጉስ ዘርአ ያዕቆብ የተፈጸመው ይህ ቀረህ የማይባል ግፍ አጥንታቸው ድረስ ዘልቆ እንደተሰማቸው ሲገልጹ “ከግዕዝ ወደ ዐማርኛ የተተረጎመው የደቂቀ እስጢፋኖስ ሰቆቃ ያስደነግጣል፣ ያሳዝናል፣ ያስቆጣል፣ የማናውቀው ራሳችንን እርቃናችንን ያሳየናል” ሲሉ አምርረው ገልጸዋል፡፡

ፕሮፌሰር ጌታቸው እንዳቀረቡት የደቂቀ እስጢፋኖሶች ሥርአታቸው ሌሎች አድባራት ትተውታል የሚሉት የድህነት፣ የስግደት፣ የጸሎት፣ የዝምተኝነት ኑሮ ሲሆን፣ ዕምነታቸው ለአብ፣ ለወልድ፣ ለመስቀል፣ ለንጉስ አንሰግድም፣ እራስን የሚያስጎነብስ እጅ አንነሳም፣ ከቤተ ክርስቲያን መጻህፍት ውጭ የሆኑትን አንቀበልም ነው፡፡ ንጉሱ ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያምና ለክቡር መስቀል ስለማይሰግዱ ነው ሰይፌን የመዘዝኩባቸው ይላል፡፡ በተቃራኒው [እስጢፋኖሶች] እንደሚሉት ደግሞ ይሄ ሰበብ ነው፣ ንጉሱ የሚያሳድዳቸው ለሱ ስላልሰገዱለት ነው፡፡

ንጉሥ፡- ለምንድነው በስግደት ራስክን ዝቅ የማታደርገው?

እስጢፋኖስ፡- ሕጉ የሚያዘን ለእግዚአብሔር እንድንሰግድ እንጂ በውስጡ አንተ እንደምትለው እንድንሰግድ ትእዛዝ የለበትም፡፡ ለማንኛውም ከኛ ስግደት አትፈልግ፣ ጸሎትና ቡራኬ ይበቃሃል፡፡

ንጉሥ፡- ለምንድን ነው ሁሌ አንተ የምትለኝ?

እስጢፋኖስ፡- ለምንድን ነው የማልልህ? አንድ ሰው አይደለህም እንዴ? በብሉይም፣ በሐዲስም የተፃፈው እንደዚሁ ነው፡፡ አንድን ሰው እንዳንድ ያናግሩታል፣ እንደ ብዙዎች አይደለም፡፡ እንኳን ሰውን እግዚአብሔርንም ‘አንተ አትጣለኝ ጌታ ሆይ፣ አምላኬ አንተ ከኔ አትራቅ፣ የመዳኔ አምላክ ጌታ ሆይ’ እያልን እንደዚህ ነው የምንጠራው፡፡

በአንድ ወቅት አቶ መለስ ዜናዊ ‹መላጣየን እስካልነካ ድረስ ልንለያይና ልንከራከር እንችላለን› ያሉትን ያስታውሷል፡፡

ይህ ከላይ የቀረበው ምሳሌ የሃሳብ ልዩነትን አለመቀበልና አለመቻቻል መሪዎችን ወደ ከፋ እርምጃ እንደወሰዳቸው ያሳያል፡፡ ታሪክ እንዳሳየው እስጢፋኖስ በ1437 አካበቢ ለፍርድ ቀረበ፤ በችሎቱ ላይ በተደጋጋሚ በድፍረት ተከራከረ፡፡ በዚህም ምክንያት በአደባባይ የተቀመጡት መነኩሴዎች ‘ሞት ይገባዋል፤ ምክንያቱም ሰንበት ሻሪ ነው፤ ለንጉሱ አይታዘዝም፤ ለክብሩም አይሰግድም’ ብለው ቢተቹም ንጉሡ ግን እንዲገረፍ ብቻ ትእዛዝ ሰጠ፡፡ እንግዲህ ይህ የመነኩሴዎች አቋም ከአድርባይ የምሁርነት ጠባይ ያለፈ አይደለም፡፡ ይህን ክፉ ባህርይ ደግሞ ዛሬም ድረስ የምንታዘበው ነው፡፡
ግፉ በዚህ አያበቃም፤ እንቀጥል፡፡

እግሩን አስረው 46 ጊዜ ገረፉት፡፡ የዚህ ዜና ትግራይ በደረሰ ጊዜ፣ በየገዳማቱና በየአድባራቱ የነበሩ መነኮሳት፣ ከባድ ጥቃት አደረሱባቸው፡፡ እስጢፋኖስና አንዳንድ ተከታዮቹም እንደገና ወደ ንጉሱ ችሎት ተጠሩ፤ እዚያም የቅጣትና የእስር ፍርድ ተፈረደባቸው:: በእስር ላይ እያሉም ከስቃዩ ብዛት አባ እስጢፋኖስ እ.ኤ.አ በ1444 ሞተ፡፡ መሪው ከሞተ በኋላ በደቂቀ እስጢፋኖሶች ላይ የሚደረገው ክትትል፣ ወከባና እንግልት ለተወሰኑ አመታት ጋብ ይላል፡፡ ሆኖም ከ1454 (እ.ኤ.አ) አካበቢ ጀምሮ ንጉሡ እነሱን ለማጥፋት ያቀደ ዘመቻ አውጆ ለብዙ ዓመታት ተንቀሳቀሰ። ብዙዎቹ የሰው ልጅ ይችለዋል ተብሎ የማይገመት ሥቃይ ተቀበሉ፤ በልዩ ልዩ አሰቃቂ መንገድ ተጨፈጨፉ፡፡ የበቀል ፖለቲካችን ማለቂያ የለውም፤ ይህ ሁኔታ የበቀል ፖለቲካችን እርሾ ሳይሆን ይቀራል?
የእስጢፋኖሶች ግፍና ስቃይ በዚህ አላበቃም፣ ዘርአ ያዕቆብን የተካው በእደማሪያምም ቀጠለበት፡፡ ያባቱን ፖሊሲ ገፋበት፡፡ ዞር ብሎ ‘አባቴ ምን አጥፍቶ ነበር?’ የማለት ጥያቄ አላቀረበም፡፡ ጨካኙን የመንግስቱን አቋም ለማሻሻል እንኳ አልጣረም፡፡ ልጅ ከአባቱ መሻል ሲኖርበት የባሰ ፖሊሲውን ቀጠለበት፡፡ አባ እስጢፋኖስ ‹ፅኑ ነብይ ሲነሳ ፅኑ ንጉሥ ያስነሳል› ያለው ተፈጸመ፡፡ ንጉሡም ሆነ መንግሥቱ የሚፈልጉት በተገዢዎች ዘንድ መወደድን ሳይሆን መፈራትን ነውና መፈራት የገዢዎች ሁነኛ ዘዴ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ዘርአ ያዕቆብ ፍፁማዊ ስልጣንን በመፍጠር የኢትዮጵያን የፖለቲካ ባህል ለዘለቄታው አዛንፎት አልፏል፡፡

ወደ ዘመነ መሳፍንት ደግሞ እንምጣና የመሳፍንቱን የፖለቲካ ባህል እንመልከት፡፡ የሚከተለው የሚገልጸው ይመስለኛል፡- ወቅቱ ከጎንደር ነገሥታት የመጨረሻው ከሆነው ከተክለጊዮርጊስ ዘመነ መንግሥት ፍጻሜ ከ1784 ጀምሮ እስከ 1855 የሚዘልቅ ሲሆን የንጉሰ ነገሥቱ ሥልጣን ተንኮታኩቶ መሳፍንትና ባላባቶች የየራሳቸውን የአገዛዝ ጎጆ የቀለሱበትን ጊዜ ያመለክታል፡፡

ይህን አሳዛኝ የሀገር መበታተን አደጋ የሚታደግ አንድ ፖለቲካዊ ኃይል በዳግማዊ ቴዎድሮስ ዕውን ሆነ፡፡ የያኔው ደጃዝማች ካሳ በቋራ ወረዳ በሻርጌ መንደር በ1818 ተወለደ፡፡ በኋላም በሽፍትነት ራሱን አደራጅቶ ከቆየ በኋላ ፈርጣማ ኃይል ሆኖ ወጣ፡፡ በኋላ ላይ አደገኛ ኃይል የሚሆንበትን ሸዋን ማንበርከክ ያስፈልገው ነበር፡፡ ሸዋን ካንበረከከ በኋላ ታላላቆቹን የኢትዮጵያ ግዛቶች አንድ አድርጎ በሥልጣኑ ስር አዋለ፡፡ እያንዳንዱ ባላባትም የንጉሠ-ነገሥቱን መሪነት በግዴታው ተቀበለ፡፡ ይህ በግዴታ የመጣው የፖለቲካ ሂደት የማታ ማታ ተቀናቃኝ መፍጠሩ የግድ ነውና ከፖለቲካ መረጋጋት ይልቅ የፖለቲካ ሽኩቻው ቀጠለ፡፡ ባርተኒስኪና ማንቴል-ኒየችኮ እንዳሰፈሩት ከ1855- 1857 ባለው ጊዜ 17 የግድያ ሙከራዎች በቴዎድሮስ ላይ ተደርገዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው ከፖለቲካ መቻቻል ይልቅ ስልጣንን ለመንጠቅ የፖለቲካ መሪን በመግደል (political assassination) ራስን ስልጣን ላይ ማቆናጠጥ ነው፡፡ ሁኔታው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ህይወት ውስጥ የተዛነፈ (formlessness) የፖለቲካ ባህል ቀድሞውኑ እንግዳ እንዳልነበር ያሳያል፡፡

ቴዎድሮስ ለዘብተኛ የፖለቲካ አቋም በመውሰድ ‹ገበሬ ይረስ፣ ነጋዴ ይነግድ፣ እያንዳንዱ ሰው በየስራው ይሠማራ› በማለት የሀገሪቱ ሕዝብ በሙሉ ሥራ እንዲሰራ የሚያደርግ አዋጅ በማውጣትም ይታወቃል፡፡ ከዚህ አዋጅ ጋር በወቅቱ የተፈጸመ አንድ አጋጣሚ የፖለቲካ አካሄዱን እንዴት እንደለወጠ ስለሚያሳይ ቢጠቀስ መልካም ይመስለኛል፡፡ እንዲህ ነው፣ ጥቂት ሰዎች ወደ ንጉሱ ግቢ መጥተው የሀገሪቱ ነዋሪዎች ሁሉ በሥራ እንዲሰማሩ የሚለውን ንጉሣዊ መመሪያ ለመከተል ይከብደናል ሲሉ ተናገሩ፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ በዝርፊያና በቅሚያ ይኖሩ ስለ ነበር ምንም ልዩ ሙያ የሌላቸው መሆኑን አስረዱ፡፡ ቴዎድሮስም ዝም ብሎ ካዳመጣቸው በኋላ ‘የቀረውን ዘራፊ ሁላ አሰባስባችሁ ትመጣላችሁ፣ የሚሆናችሁ ሥራ ይሰጣችኋል’ ብሎ አሰናበታቸው፡፡ ወንበዴዎቹ ከሄዱ በኋላ የቴዎድሮስ አማካሪዎች በበኩላቸው ንጉሥ እንዴት ከወንበዴዎች ጋር ይደራደራል ብለው ሳቁ፣ አሽሟጠጡ፡፡ ሽፍቶቹ ከሩቅ ሀገር ያሉት ሁላ ተጠራርተው ተሰብስበው እንደ ተነገራቸው ተመልሰው ሲመጡ ንጉሱ ዘቦቹን አዝዞ አንድም ሰው ሳይቀር እንዲገደሉ አደረገ፡፡ ትውፊቱ እንደሚለው ከዚያን ጊዜ አንስቶ በቴዎድሮስ ግቢ ሳቅና ጨዋታ ቀረ፡፡ በእርግጥ ይህ ከላይ የቀረበው ድርጊት ለህዝቡ ሰላማዊ እፎይታን የሰጠ ቢሆንም በአጠቃላይ በፖለቲካ ባህሉ ውስጥ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣቱን ይጠቁማል፡፡ ‹ሳቅና ጨዋታ በቴዎድሮስ ግቢ ቀረ!› የሚለው አባባል የስርአቱ የፖለቲካ አስተሳሰብ በፍርሃትና በማንበርከክ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያሳያል፡፡

‹ፅኑ ነብይ ሲነሳ ፅኑ ንጉሥ ያስነሳል›- እስጢፋኖስ ሦስት መሰረታዊ አስተሳሰቦች እዚህ ላይ ያስፈልጉናል፡፡ እነሱም ልዩነትን ማክበር፤ መግባባትና በመጨረሻም የአንድ ሀገር ዜጋ መሆን ወይም ውህድነት (Homogeneity) ናቸው፡፡

ለቴዎድሮስ የመጨረሻ ውድቀትና ሞት የቅርብ ምክንያት ሆኖ የሚወሰደው የእንግሊዞች መምጣት ነው ቢባልም በሀገሪቱ ውስጥ የነበረው የኃይል አሰላለፍ ወሳኝ ሚና እንደነበረው መካድ አይቻልም፡፡ ቴዎድሮስ በእንግሊዞች የተሸነፈው ከትግሬው በዝብዝ ካሳ፣ ከላስቴው ዋግሹም ጎበዜና እንደ ሳህለ ማሪያም ካሉት ህጋዊ ባላጋራዎቹ ጋር ታግሎ የማሸነፍ ፖለቲካዊ ብቃት ስላልነበረው ነው፡፡
እነዚህ ከላይ በጥቂቱም ቢሆን የቀረቡት ማሳያዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲካዊ ባህላችን ያልዳበረና በዛሬውም ዘመን ጠንክሮ እንዳይወጣ የራሳቸውን አፍራሽ ሚና መጫወታቸውን ይመሰክራሉ፡፡ የፖለቲካ ባህል ሊዳብርና የጋራ ሊሆን የሚችለው የተለያዩ ፖለቲካዊ እምነቶቻችንን የሚያስተናግድና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ መፈቃቀድ ሲኖር፣ ነጻ የኢኮኖሚ አስተሳሰብ በሁሉም ክልሎች ሲፈጠር፣ ለህግ የበላይነት በጋራ መቆም ሲቻልና መልካም የሆኑ የዜጎች ግንኙነቶች ዳብረው ህብራዊነት ሲደምቅ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ጭራና ከአስተሳሰብ ተራ የወጡ የዘውጌነት ፍላጎቶችን ብቻ ይዞ ገመድ ከመጓተት በመለስ በኢትዮጵያዊ (ኢትዮጵያዊ አይደለንም የሚሉትን ጨምሮ) አጀንዳ ላይ መከራከር ይኖርብናል፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top