ታሪክ እና ባሕል

ያጣነው የሁላችን አባት

የሁላችን አባት የሆኑት ተስፋዬ ሳህሉ ሀምሌ 24፣2009 ዓ.ም ”ደህና ሁኑ ልጆች” ብለው እስከ ወዲያኛው አሸለቡ። ተስፋዬ ሳህሉ የሙያ ሀብት ባለቤት ነበሩ። ከተረት አጫዋችነት አንስቶ የአስማት ትርኢት አቅራቢ፣ተዋናይ፣የሙዚቃ ተጫዋችና ደራሲ ናቸው። በዕውቁ የኦቴሎ ቴአትር ኢያጎን ሆነው የሰሩ የመድረክ አድባር ነበሩ። ከመድረክ አልፈው ወደ ጦር ሜዳ ዘምተዋል። በ1944 ዓ.ም በኮርያ አገር በ50 አለቃነት ማዕረግ ክራር ይዘው ሠራዊቱ ለድል እንዲበቃ እያዝናኑ ሀገራቸውን በአለም መድረክ አስተዋውቀዋል። ሰኔ 20 ቀን 1915 ዓ.ም በባሌ ክፍለ-ሀገር ከዱ ተወለዱ። በ1957 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲቋቋም ጀምሮ የልጆች ጊዜ ፕሮግራም በማዘጋጀት ከኢቴቪ እስከ ተለያዩበት 1998 ዓ.ም ድረስ ለ41 ዓመታት ልጆችን በተረትና በጨዋታ ሲኮተኩቱ ኖረዋል።

አባባ ተስፋዬ (ተስፋዬ ሳህሉ) ከግማሽ ምዕተ-ዓመት በላይ ወገናቸውንና አገራቸውን በትጋት ሲያገለግሉ ኖረዋል። ጌታቸው ደባልቄ “ተስፋዬ ብዙ ሰው ነው” ብሏል። በመድረክ ላይ ሁሉን ለውጦ ሲታይ እጅግ የሚያስደንቅ ችሎታ ነበረው” ያለው ደግሞ ፕሮፌሰር ተሰፋዬ ገሠሠ ነው።

ከሁሉም የትወና ህይወት ተሰፋዬን ልዩ የሚያደርጋቸው ሴት ተዋንያን በሌሉበት ዘመን ሻሽ በማሰርና ፂማቸውን ሙልጭ አድርገው በመላጨት ለአራት ዓመታት እንደ ሴት ሆነው በየመድረኩ ታዳሚያቸውን አስደስተዋል። ‘የአርበኛው ሚስት’ ለዚህ ተጠቃሽ ሲሆን፤አፋጀሽኝ ፣የደም ድምፅ፣ ጎንደሬው ገብረ ማርያም፣መቀነቷን ከፍታ፣አርበኞችና ኢትዮጵያ የተሰኙት ቴአትሮች ይገኙበታል።

ከአጼ ኃይለ-ሥላሴ እጅ ሦስት ጊዜ የወርቅ ሰአት ተሸላሚ ሲሆኑ፤ የኢትዮጵያ የስነ-ጥበባትና የመገናኛ ብዙሃን ሽልማት ድርጅት በ1991 ዓ.ም በተዋናይነት የህይወት ዘመን ተሸላሚ ሲያደርጋቸው ከዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ሀምሌ 22፣ 2009 ዓ.ም የክብር ዶክትሬት ዲግሪ እንደተቀዳጁ ይታወሳል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top